ሕይወቱን አስይዞ በሚታገል የሕዝብ ኃይል አትነግዱ (ጌታቸው ሽፈራው)

ተቋም መሰረትኩ ከሚለው መካከል ሚዲያ ላይ አቅርቡኝ ብሎ የማይወተውት የለም። ሰው አላማውን ለማሳካት ሚዲያ ላይ የሚቀርብባቸው ሌሎች መንገዶች አሉ። የሆነ ሆኖ ሚዲያውም ሰው ከማቅረቡ በፊት ማን ነው? እነማን ናቸው? ምን ይጠቅማሉ ብሎ መመዘን አለበት። ድርጅት ሲሆን ደግሞ የበለጠ ማጣራት ያስፈልጋል። ኢትዮ 360 ምንም ሳይመዝን ነው ያቀረበው። ትክክል አይደለም። ለሕዝብ በርካታ መዘዝ አለው። ሚዲያ ለሕዝብ ድምፅ ሆኖ ከጥቃት እንደሚያድነው ሁሉ ጠላትም ጎትቶ አምጥቶ ያስጎዳዋል።

በአማራ ሕዝብ ስም በርካታ ማሕበራት አሉ። አብዛኛዎቹ በሕዝብ ስም ይነግዳሉ እንጅ አይሰሩም። ይህኛው ደግሞ የባሰው ነው። የባሰ የሚያደርገው ከባሕሪው ነው። በፋኖ ስም ነው የመጣው። በገንዘብ የሚነገድበት፣ በፖለቲካው ብዙ ችግር የሚያመጣ ነው። የፀጥታ ጉዳይ ላይ ነው ከውጭ ሆነው እጃቸውን የሰደዱት።

በነገራችን ላይ በአማራ ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀር የተሰነጠቁት በውጭ በሚፈጠሩ ቡድኖች ነው። እንደ አሁኑ ማሕበራዊ ሚዲያ ሳይስፋፋ የቅንጅት አባል ፓርቲዎች መካከል ችግሩ የባሰው በውጭ ደጋፊዎች ነው። የዳያስፖራው ትልቁ ችግር ሚናውን አለመለየቱ ብቻ አይደለም። በአቅሙም አለመሰማራቱ ነው። ፖለቲካውን የሚያውቁት ጭቃ መቃባት መስሏቸው ሲተውት፣ አንዳንዱ ደግሞ ምንም አይነት ነባራዊ ሁኔታውን ሳይረዳ መከራውን ያያል፣ በእርግጥ የሕዝብ መከራም ጭምር ነው የሚያባብሰው። ይህ ሰውዬ መሰረትኩት ስላለው ድረጅት አላማ ከእሱ ይልቅ ሀብታሙ ሊያብራራለት ይሞክራል። ያው ቢጨንቀው መሰለኝ!

ዋናው ነገር “ዓለም አቀፍ የፋኖ ማሕበር” ተብሎ የቀረበው ምንም እንኳ ባይጠቅም ጉዳት ስለሚኖረው ነው የምፅፈው። እንጅ ዝም ብሎ በአማራ ሕዝብ ስም ሳያሰላ ድርጅት መሰረትኩ ከሚለው ጋር መጨቃጨቅ ሱስ ኑሮብኝ አይደለም። አድካሚ ነው ደግሞ።

1) ፋኖ የፀጥታ ኃይል ነው። እንደ ልዩ ኃይል፣ እንደመከላከያ ነው። የልዩ ኃይልም የመከላከያም ዓለም አቀፍ ማሕበር የለውም። በእርግጥ ሊቀመንበር ነኝ ብሎ በ360 የቀረበው ሰውዬ ፋኖን፣አማራ ልዩ ኃይልንና ሚሊሻውን ለማቀራረብ ምናምን እንሰራለን ይላል። አለማፈር። የፋኖ፣ የሚሊሻና የልዩ ኃይል የጋራ ማህበር፣ ወይስ ሸር ካምፓኒ ሊመሰርት ነው?

2) ከስሙ ስንነሳ የተፃፈውና የሚናገሩት ራሱ የተለያየ ነው። ፋኖ ዓለም አቀፍ ማሕበር ይሉታል፣ ፋኖ ዓለም አቀፍ መረዳጃ ማሕበር ይሉታል። ሁለቱም ችግር ያለበት ነው። ሰውዬው አሜሪካ ውስጥ የተወሰኑ ግዛቶች ቅርንጫፍ እንዳሉት ነው የሚናገረው። እሱም እውነት አይደለም። የአሜሪካ ግዛቶች ላይ ሁለት ሶስት ሰዎችን ሰብስቦ ዓለም አቀፍ ማኅበር አይባልም። መረዳጃነቱም ቢሆን ተመሳሳይ ነው። አርማጭሆና ቋሪት ያለ ፋኖ ኢትዮጵያ ውስጥ እንጅ ሲያትል ምናምን ላይ ምን ያደርጋል? በአሜሪካ ጫካ ገብተህ የአሜሪካ ኤምባሲ ያሉ የኢትዮጵያ ሰዎችን ልትታገል ነው? ወይንስ የአሜሪካ መንግስትን? መረዳጃ የሚለውም ተመሳሳይ ነው። ለፋኖ የሕዝብ ስንቅ በቂ ነው። ሕዝብ አላማውን ካመነበት ለፋኖ ቀርቶ ለሌላውም ሆኗል።

3) የአባልነቱ ጉዳይም አስቂኝ ነው። ሶስት ሰዎች ሆነን ነው የጀመርነው ይላል። አንድ የሰፈር ፋኖ ራሱንና ሁለት ጀሌ (መሳርያ ያልያዘ) ይዞ መንቀሳቀስ ይችላልኮ። ከሰፈር ፋኖ የማይሻል ስብስብ የፋኖንም፣ የአማራንም ችግር እንፈታለን ብሎ በዓለም አቀፍ ስም ይቀልዳል። ከዚህ ባለፈ ፋኖ የተመዘገቡ ሰዎች ስብስብ አይደለም። ገበሬው ሁሉ ፋኖ ነው። ለዚህ ማሕበርም መረዳጃም አያስፈልገውም። ቢያስፈልገው እንኳ ሀገር ቤት ያሉት ታዋቂ መሪዎች በኩል ማስተባበር ይቻላል እንጅ ከውጭ ሆኖ አይመራም።

4) ገንዘብ የሚያስፈልግበት ጊዜ አለ። ለፋኖም ሆነ ለሌላ አደረጃጀት ገንዘብ በሚያስፈልግበት ጊዜ ለማድረስ ማሕበር መመስረት የግድ አይደለም። በርካቶች በግልም በማሕበርም አድርሰናል ይላሉ። በእርግጥ ፓስተር ነን ብለው ከሚያጭበረብሩት ቀጥሎ እንደ ፋኖ ገንዘብ የተበላበት የለም። ኦዲት አይደረግም። ተቋማዊ አወቃቀር የለውም። ለተወሰኑ ሰዎች ሊደርስ ይችላል። አንዱ በሜሴንጀር ድምፁን አሰምቶ ደርሶናል ይላል። አለቀ። እንዲያወም ትልቁ ችግር ገንዘብ ልኬ አልደረሰህም፣ እንትና በላብህ፣ እንትና ሳያካፍልህ…… እየተባሉ እርስ በእርስ ማናቆር ነው መጨረሻው። ጭራሽ እርስ በእርስ!

በነገራችን ላይ ዋናዎቹ ፋኖዎች በማሕበራዊ ሚዲያ አይገኙም። መሳርያቸውን ይዘው እንጅ ስማርት ስልክ ይዘው አይውሉም። ፋኖ ነኝ የሚለውም አደርሳለሁ የሚለውም በፋኖ ስም የሚነግደው ነው። በቅርቡ ደግሞ ገዥዎቹ ፋኖን ለመምታት ያቋቋሙት አውደልዳይ ነበር። ከተማ ውስጥ ይውላል። ፋኖን እየሰለለ፣ በማህበራዊ ሚዲያ ደግሞ ከእኔ ውጭ ፋኖ የለም ሲል ይውላል። ይህ ኃይል የመጀመርያ በፋኖ ስም የሚያጭበረብር፣ ከዳያስፖራው ጋር ሲፃፃፍ የሚውል ነው። ለዚህ ከሆነ ማሕበር የሚቋቋመው ገዥዎቹ ለሰላይነት የሚከፍሉትን መደጎሚያ መሆኑ ነው።

5) ሌላኛው ችግር ከዳያስፖራው የሚመነጭ ነው። ብዙው ዳያስፖራው በሜሴንጀር ሲጠዛጠዝ የሚውል፣ አሉባልታን ሰበር ዜናው ያደረገ ነው። የጎጥ ትልቁ ሰንኮፍ ያለው ዳያስፖራው ጋርም ነው። ይህ ኃይል ጭራሽ የታጠቀ ኃይልን አንቀሳቅሳለሁ ካለ ትልቅ እብደት ነው። እብደት! ከገንዘብ ያለፈ አላማ ኖሮት መሰል ማሕበር ቢያቋቁም የሚጠላቸውንም ካላስገደልኩ ይላል፣ ፋኖዎችንም እርስ በእርስ ያጫርሳል። የታጠቀን ኃይል ከዳያስፖራ ቀርቶ ሀገር ቤት ተገኝቶም መምራት ይከብዳል። የታጠቀን ኀይል በሜሴንጀርና በዋትሳፕ ቀርቶ በአካል ከጎኑ ሆኖ መምራት ከባድ ነው። ኤርትራ ሄደው ታጣቂያቸውን የሚጎበኙ፣ በአንድ እዝ ያደረጉ እንኳን ብዙ ነግደውበታል። መምራትም አልቻሉም።

እውነቱን ለመናገር እነዚህ ሰዎች አላማውም፣ ነባራዊ ሁኔታውን የሚያገናዝቡበት የፖለቲካ አረዳድም አላቸው ለማለት አልደፍርም። የፖለቲካ ፍላጎት ቢኖራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ፋኖ ይልቅ በሚኖሩበት ሀገር ያለ ኤምባሲና የሰብአዊ መብት ተቋም ይቀርባቸው ነበር። በእርግጥ የኢንተርኔት አገልግሎት ከሌለበት ሸለቆ ውስጥ ከሚውል ፋኖ ይልቅ የትም የሚገኙ የዓለም አቀፍ ማሕበረሰብ አባላትን በኢሜል ማግኘት ይችሉ ነበር። ከፋኖ ዓለም አቀፍ ማሕበር ይልቅ አማራውን ይጠቅመው የነበረው ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ መድረስ ነበር። ግን አላማው ባይኖር፣ አሊያም ሚናን መወጣት ባይችሉ አሊያም የገንዘብ ፍለጎት ቢኖር ነው።

6) ሊቀመንበር ነኝ ባዩ በመሃል የማሕበሩን ጉዳይ ትቶ ሌላ ፖለቲካ ነው የሚያወራው። እንደዛ ከሆነ ለአማራ ከውጭ የሚመጣም፣ ሌላም የተቃዋሚ ፓርቲ አያስፈልግም እንጅ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢመሰርቱ ይሻል ነበር። አይ ካሉ ደግሞ በዚህ አቋማቸው የማያዛልቅ ቢሆንም ሲቪክ ማኅበረሰብ በመሰረተ። ትንሽ አላማ አለን ካሉ ደግሞ የአብን ወይም የሌላ ድርጅት የድጋፍ ሰጭ ሆነው በመጡ። አይ ሚናችን ለይተናል ካሉ ደግሞ ትምህርት ቤት፣ የሕክምና ተቋምና መሰል ነገር ባሰሩ። ለፋኖም ለተፈናቀለ ወገንም ድጋፍ ሲያስፈልግ በሰጡ። የግድ ለፋኖ ነው ካሉ ደግሞ ፋኖዎች ይቋቋሙ ሲባሉ ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር ሆነው ገንዘብ አሰባስበው ቢልኩ በቂ ነበር፣ ማሕበር ሳያስፈልጋቸው። እንዲያው ይሄ ሁላ ባይሆንላቸው፣ የገንዘብ ፍላጎት ካላቸው አጀንዳና አላማም ባይዙበት እየተሳደቡም፣ እየዘለፉ፣ እየቀጠፉም ቢሆን ገንዘብ የሚሰበስቡትን ዩቱዩበሮች በተቀላቀሉ። ለአማራ ሕዝብ እረፍት ነዋ። ቢያንስ እንደተሳዳቢ ታይተው ይታለፋሉ። ከዚህ ሁሉ ደግሞ የአማራን ሕዝብ ሰበብ ፈልገው ችግር ውስጥ ከሚያስገቡት አርፈው ቢቀመጡ ትልቅ ውለታ ነበር። እባካችሁ የማታውቁ ሰዎች ንገሯቸው! እባካችሁ በሏቸው! እባካችሁ! እባካችሁ።

ሕይወቱን አስይዞ በሚታገል ኃይል ሕይወት መቀለድ ነውር ነው። ሚዲያዎቹም ያልሆኑ አካላትን እያመጣችሁ አማራ ሕዝብ አናት ላይ አታውጡ። ገንዘብ ስጡን የምትባሉም ለሕዝብ ለማይጠቅም መሰል ስብስብ ባትከስሩ፣ አባል ሁኑ ተብላችሁ በቅንነት የምታዩት ባትገቡ ይመረጣል።

(ለፈገግታ ያህል ይህን ያህል አላማ ያለው ድርጅትን በሊቀመንበርነት እመራለሁ የሚለው ሰውዬ በፌስቡኩ የሚለጥፈውን ተመልከቱ። ይችን መከረኛ ቤተ ክርስትያንም መጠለያ አድርገዋታል ይመስለኛል። እንደዚህ አይነት ሰዎች መተከል ላይ በሚታረዱት ወገኖች ሳይቀር ለመነገድ ወደኋላ የሚሉ አይመስለኝም።)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *