“የአማራን ህዝብ ትግል ከባዶ ሜዳ እየመጡ ልምራም አይባልም። ነውር ነው።” ለኤርሚያስ ለገሰ የተሰጠ ምላሽ
By: Date: December 8, 2020 Categories: ትንታኔ

ኤርሚያስ ለገሰ የተባለው ሰው አደብ እንዲገዛ የምትቀርቡት ሰዎች ንገሩት። የአማራ ልዩ ኃይል ትግራይ ውስጥ የገባው ለውድድር አይደለም በሉት። ለጦርነት ነው። ጦርነቱንም ምድር ጠበበችን ብሎ ያመጣው አይደለም። ይልቁንሥ ጦር ጠማኝ ያሉ ሠዎች የፈፀሙበትን የቀጥታ ወረራን ለመመከት እንጅ።

ኤርሚያስ የተባለው ሰው ከ20 ቀናት በፊት ጦርነቱ ወያኔን ሳይሆን ትግራይን ለማንበርከክ ነው እያለ ሲለፈልፍ ነበር። ታዲያ ትግራይን ለማንበርከክ ነው ባለበት አፉ የአማራን ልዩ ኃይል እንዴት ሊያሞግስ ቻለ? ያውም ከኦሮሚያ ልዩ ኃይል ጋር በማነፃፀር።

አደገኛው አካሄድ እዚህ ጋር ነው ያለው። “አንድ የአማራ ልዩ ኃይል ከ100 የኦሮሞ ልዩ ኃይል ይበልጣል” ነው ያለው። አንድ ለማሰብ የደረሰ ሠው ይህን ቀደዳ እንዴት ሊያምንልኝ ይችላል ብሎ እንዳወራው ራሱ ነው የሚያውቀው። የ3 ዓመት ልጀ ይህን ንግግር ብትሰማ ሳቅ ብላ ነው የምታልፈው። የሰው ልጅ በዚህ ደረጃ ሁለት ትልልቅ ብሔሮችን ለማጋጨት ይህን ያክል ርቀት መሄድህ እንዴት ይቻለዋል?

ኤርሚያስ የአማራ ኃይልን ልፍስፍስ፣ ተላላኪ፣ እንኩቶ እያለ ሲያበሻቅጥ ከርሞ ድንገት ደጋፊ መስሎ መከሰቱ በራሱ አስተዛዛቢ ነው። የአማራን ህዝብ ትግል ከባዶ ሜዳ እየመጡ ልምራም አይባልም። ነውር ነው። የአማራ ትግል የራሱ መሪዎች አሉት። የሚታወቁ፣ ፖለቲካንም በደንብ የሚያውቁ መሪዎች። አማራው እንደ ኤርሚያስ አይነት ትናንት የተናገሩትን ዛሬ የማይደግሙ መሪዎችን አይፈልግም።

አማራው “ጨው በአፉ የማይሟሟ” የሚለው አባባል አለው። ምን ማለቱ መሰለህ። ለቃሉ የሚያድር፣ በቃሉ የሚገኝ፣ ጨው አፉ ላይ አድርገህ አደራ ብትሰጠው እንኳን ባለበት ጠብቆ የሚያስረክብ ማለቱ ነው። እነዚህን መሳይ መሪዎችን ነው አማራው የሚፈልገው። አቶ ኤርሚያስ በዚህ መመዘኛ ጨው በአፍህ ሳታሟሟ የምታስረክብ ነህ ወይ? የሚለውን መልስ ራስህ መልሰው

ሌላው እና አንገብጋቢው ነገር ሰሞነኛው ጭቅጭቅ ነው። የአማራ እና የኦሮሞ በጎ ግንኙነት ወያኔን ከአራት ኪሎ ነቅሏል። ደጋፊዎቿንም አዕምሯቸው እንዲነቅል አድርጓል። ይህ በጎ ጥምረት ወያኔን ከመቀሌ አባሮ ሙትና ተንከራታች አድርጓል። ይህን በጎ ጥምረት መረበሽ አገራችን የምትገኝበትን መልካም መንገድ መረበሽ ነው። የመንግስት አመራሮችም ሰከን በሉ። ክርክሩና ጭቅጭቁ ከአዳራሽ አይለፍ።

በአደባባይ የምታደርጉት ሙግት ወሬ ለቅመው ለሚሮጡት ሲሳይ እንዳይሆን ተጠንቀቁ። በተረፈ መላው ኢትዮጵያ ወያኔን ለመቅበር ያሳዬውን በጎ ትብብር ወደ ላቀ አንድነት አሳድጎ የተሻለች ዲሞክራሲያዊት ሀገር ለመገንባት መረባረቡ ጠቃሚ ይሆናል። ወያኔን ለመታደግ ሲጋጋጥ የከረመው ሁሉ በወያኔ መንገድ ሄዶ እርስ በርስ እንዳያናክሰን እንጠንቀቅ። ሁለንተናዊ ድል ለሀገሬ! (ጋሻው መርሻ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *