በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያዊነት ጎራ መገኘት እጅግ አደገኛ ሆኗል (ፕሮዲዩሰርና ተዋናይት መቅደስ ጸጋዬ) 9

ወዳጆቼ በአሁኑ ጊዜ እጅግ ከባድ ሆኖ የተገኘው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያዊነት ነው፡፡ ከባዱን ሁኔታ መሸከም ካልፈለጋቹ ሦስት ክፍሎች አሉ። እነሱም #አንድ ዘረኛ ሆኖ የአንዱን ብሔር መርጦ በዛ ውስጥ መኖር፣ #ሁለተኛው ፖለቲከኛ ሆኖ የመንግስትን አላማ እያሰፈፀሙ መራመድ፣ #ሦስተኛው በእነዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ ውስጥ ምን አስገባኝ፤ ለምንስ ህዝብ ይጥላኝ ብሎ ዝም ብሎ አርፎ መቀመጥ ናቸው።

አይ! እነዚህ እኔን አይወክሉኝም ዘረኛ አይደለሁም፣ በአንድ ፓርቲ አመለካከት ውስጥ የምወሰን ፓለቲከኛም አይደለሁም፣ ዝምታን ደግሞ ህሊናዬ አይፈቅድልኝም፤ በገባኝ፣ አቅምና ጊዜዬ በሚፈቅድልኝ መጠን ስለህዝቤ መብትና ሰላም እሠራለሁ/እናገራለሁ ብለን ስንወስን ደግሞ ወደ #አራተኛው እርሱም ኢትዮጵያዊነት ወደሚባለው ጎራ ትቀላቀላላችሁ። በአሁኑ ጊዜ በዚህ ጎራ ውስጥ መገኘት እጅግ አደገኛ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት በተለይ በብሔርተኝነት በሽታ ለተያዙ ሰዎች በፍጹም የማያስደስት ጎራ ሆኖባቸዋል።

እኔ አራተኛውን ጎራ መርጨ በተከበበልኝ ክበብ ወስጥ ባለመገኘቴ፤ ዛሬ አንዱ ሲደሰትብኝ፣ ነገ አንዱ ሲከፋብኝ፣ ከአንዱ ጥግ ወደሌላው ጥግ ሀሳቤ እንደኳስ እየተላጋና እየተቀባበሉት እስካሁን አለሁ፡፡ ኢትዮጵያን መምረጥ በዛሬው ጊዜ ውጤቱ ይኼ ነው፡፡ ምላሹ የተለያየ ቢሆንም ባለፉት ጊዜያቶችም ይኼንን አቋሜን በተለያዩ አጋጣሚዎች አንፀባርቄያለሁ።

በሰሞኑ ተሰርቶ የተለቀቀው “የሀገር ልጅ የማር እጅ” የተሰኘው ማስታወቂያ ላይ መሳተፌም በሀገራችን በተለያዩ ችግሮች ለተፈናቀሉ ወገኖችና አሁን በጦርነቱ ለተፈናቀሉ ወገኖች መርጃ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነበር። በደሰታ ወገኔን ለመርዳት ጥሪውን ተቀብዬ ተሳተፍኩኝ። ምክንያቱም ከላይ እንደገለፅኩት የኔ ምረጫ አራተኛው ኢትዮጵያዊነት በመሆኑ!!

በመጨረሻ ግን….
በግራም በቀኝም እየፈሰሰ ያለውን የወገኖቼን ደም እግዚአብሔር ይመልከት!! ብሔር በሚባል በሽታ ምንም የማያውቁትን የምስኪን ወገኖቼን ደም ያፈሰሱትን እግዚአብሔር ፍርዱን ይስጣቸው!!! እመኑኝ ቀላል ሊመስል ይችላል ከሰው ግን የእግዚአብሔር ፍርድ ይበልጣል!! ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!! ዘረኝነት ይውደም!! ጌታ ሆይ ሀገራችንን በምህረትህ ጎብኝልን!!..

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *