የተስፋዬ ገ/አብ ተረትና የህወሀት የማንነት ተኮር ሰለባ የሆኑ ሁለቱ ጀነራሎች

ጄ/ል አበባው ታደሰና ጄ/ል ባጫ ደበሌ የእናት አገራቸውን ጥሪ ተቀብለው ከሰራዊቱ ጋር እየጻፉት ላለው አኩሪ ታሪክ አድናቆት አለኝ። ጄ/ል አበባው በማንነቱ ምክንያት ጥቃት የደረሰበት መኮንን ነው። ይህ መኮንን ዛሬ ሳይሆን የዛሬ 5 ዓመት ገደማ የነጻነት ታጋዮችን ተቀላቅሎ ህወሃትን የመፋለም ፍላጎት እንደነበረው በቅርብ አውቃለሁ። በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ያሳበው ሳይሳከለት ቢቀርም እነሆ ዛሬ እድሉን አግኝቶ የዚያን ክፉ ስርዓት መሪዎች እጅ ይዞ ለፍርድ ለማቅረብ ከፊት ተሰልፏል።

ቆፍጣናው ወታደር ባጫ ደበሌ ደግሞ የተስፋዬ ገ/አብ ተረቶች ሰለባ ነው። ባጫን ዳንስ እንጅ ውትድርና የማያውቅ ሰው አድርገን ስንስለው ኖረናል። ይቅር ይበለን። አሁን ላይ ለእናት አገሩ እየከፈለ ላለው ውለታ ባርኔጣዬን ከፍ አድርጌ አነሳለሁ። በስም ያልጠቅስኳችሁ ሌሎች የፈተና ወቅት መኮንኖችም እንዲሁ ክብር ይድረሳችሁ።

በነገራችን ላይ በታቀደለት መሰረት ሲፈጸም ያየሁት ጦርነት ይህ ጦርነት ነው። ጦርነት በታቀደው መሰረት ላይሄድ ይችላል። ሎጂኩ ቀላል ነው። ጠላትም ልክ እንዳንተ ያቅዳል። ስለጠላትህ ትክክለኛና በቂ መረጃ ከሌለህ አንድ ሺ ጊዜ ብታቅድ አንዱንም ላታሳካ ትችላለህ ብቻ ሳይሆን ለሽንፈትም ልትዳረግ ትችላለህ ። አንድን ወረዳ በዚህ ቀን እይዛለሁ ብለህ አቅደህ በአመቱም ላትይዘው ትችላለህ። መለስ ዜናዊ አልሸባብን በሁለት ሳምንት ውስጥ ደምስሰን ከሶማሊያ እንወጣለን ብሎ እነሆ ከ 14 ዓመታት በሁዋላ ጦራችን አሁንም እዛው ነው።

ዶ/ር አብይ “በአጭር ጊዜ ጦርነቱን እናጠናቅቃለን” ብሎ ሲናገር “ይህ ሰው ለምን የጊዜ ገደብ አስቀመጠ” እያልኩ እራሴን እጠይቅ ነበር። ያውም በትግራይ ምድር፤ ያውም ለዓመታት ሲደራጅና ሲያከማች ከኖረ ሃይል ጋር ለሚደረግ ፍልሚያ፣ የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ በእውነት የማይታሰብ ነው። ጦርነቱን ቀደም ብለህ ተዘጋጅተህ፣ ራስህ በመረጥከው ጊዜና ቦታ፣ ብታደርገው “ይሁን” ልትል ትችላለህ። ነገር ግን ጠላትህ በመረጠው ቦታና ጊዜ ውስጥ ሆኖ የጦርነት ማጠናቀቂያ እቅድ አውጥቶ መንቀሳቀስ በእውነት ተአምር ነው። የአብይ መንግስት ግንባታ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በጦርነትም ላይ አቅዶ መንቀሳቀስ እንደሚችል አስመስክሯል። ይህ ግን የማቀድ ውጤት ብቻ አይመስለኝም፤ የሆነ እድል ወይም የሆነ ነገርማ ሳይጨመርበት አይቀርም። (ጋዜጠኛ ፋሲል የኔአለም)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *