የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ማንም መግባት የለበትም ማለታቸው ተገለጸ

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያ መንግሥት በሕወሓት ሕገወጥ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን ሕግ የማስበር ዕርምጃ አጠናክሮ እንዲቀጥል መግለጻቸውንና በውስጥ ጉዳይዋ ማንም ጣልቃ መግባት እንደሌለበት መናገራቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ዓርብ ኅዳር 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመራ ልዑክ፣ በምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጉብኝት ስኬታማ የዲፕሎማሲያዊ ክንውን መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡ ልዑኩ ከኬንያ፣ ከሩዋንዳ፣ ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና ከኡጋንዳ ፕሬዚዳንቶችና ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝቶ ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መምከሩንም አምባሳደሩ አክለዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን የአገሪቱ አካባቢ እየወሰደ ያለው ሕግ የማስከበር ዘመቻ መነሻና ዓላማውን ሚኒስትሩ ለመሪዎቹ መግለጻቸውን እንዳስረዱም ጠቁመዋል፡፡ ሕወሓት አገራዊ ሪፎርሙን በመቃወም፣ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የሽብር አካላትን ሲደግፍ፣ የሕግ ጥሰቶችን ሲፈጽምና በመጨረሻም የአገር ሉአላዊነት ቀይ መስመርን በማለፉ መንግሥት ሕግ የማስከበር ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን እንዳስረዱም አምባሳደሩ ተናገረዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት እያደረገ ያለው እርስ በርስ ጦርነት ሳይሆን ሕግ የማስከበር ዕርምጃ መሆኑን በማስረዳት የአገሮቹ መሪዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸው መደረጉንም አክለዋል፡፡

መሪዎቹም የኢትዮጵያ የሰላም ደኅንነት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም መሠረት መሆኑን በመግለጽ፣ ሕግ የማስከበር ዕርምጃ የአገር ውስጥ ጉዳይ መሆኑን በመጠቆም፣ ማንም ጣልቃ የሚገባበት ጉዳይ አለመሆኑን ለልዑኩ መናገራቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተጨማሪ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውም በጂቡቲና በሱዳን በመገኘት ተመሳሳይ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን ማከናወናቸውንም አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በፓስፊክ አገሮች ያሉ የኢትዮጵያ አምባሳደሮችና ቆንስላዎች፣ ለአገሪቱ መሪዎችና መገናኝ ብዙኃን ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ገለጻ ማድረጋቸውን ዲና (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡ ሪፖርተር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *