ህግን ለማስከበር በራያ አላማጣ ግንባር የተሰማራው መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌ በቅርብ እርቀት ላይ እንደሚገኝ ተገለጸ

በራያ አላማጣ ግንባር ህግን ለማስከበር የተሰማራው መከላከያ ሰራዊት መሆኒ አካባቢ የሚገኘውን እና ጁንታው የተመካበትን ምሽግ ደረማምሶ ወደ ፊት በመገስገስ ከመቀሌ በቅርብ እርቀት ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡

የግንባሩ የሰው ሀብትና ሚዲያ ስራዎች አስተባባሪ ኮሎኔል ደጀኔ ፀጋየ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጀግናው መከላከያ ሰራዊት ትናንት ማታ በሰነዘረው ጥቃት ጁንታው ሲመካበት የነበረውንና ከሰሜን እዝ ዘርፎ የታጠቃቸውን ከባድ መሳሪዎች ያሰለፈበት ምሽግ ተደረማምሷል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ከመቀሌ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ በመሆኑ የጁንታው ግብዓተ መሬት ተቃርቧል ብለዋል፡፡ በቦታው ሲዋጋ የነበረውን የጁንታውን ታጣቂዎችና የጦር መሳሪያዎች በመደምሰስ ሰራዊቱ ከፍተኛ ድል ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ሰራዊቱ ፍጹም ወኔና ጀግንነትን በመላበስ እራሳቸውን እንደጀግና እና ጦረኛ አድርገው የሚያዩ ትዕቢተኞችን የውርደት ሸማ ያከናነበትን ድል ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡ የጁንታው አመራሮች ምንም የማያውቁ ህጻናትን ከፊት አሰልፈው እንዳያፈገፍጉም እጃቸውን እንዳይሠጡም ከኋላ ሆነው ርምጃ በመውሰድ ወደ እሳት ውስጥ እየማገዷቸው ነው ብለዋል፡፡

ሰራዊቱ ለሀገሩ፣ ለባንዲራው፣ ለአንድነቱና ለመለዮው ታማኝ መሆኑንና መስዋዕትነት ለመክፈል የማያቅማማ መሆኑን እንዲሁም ሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ጀግና መሆኑን ያስመሰከረበት ድል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ተጋድሎ ላይ እጅ ለእጅ በመተናነቅ መሳሪያ ነጥቆ ጠላትን በራሱ መሳሪያ የደመሰሰ ጀግና የታየበት የጦር ውሎ እንደነበርም ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው መልክአምድር ተራማማ መሆኑና ጠላት አስቀድሞ የመሸገበት መሆኑ ሲታይ ከብዙ ክፍለ ጦር ጋር እንደመዋጋት ነው ያሉት ኮለኔሉ ያም ቢሆን ያለምንም ኪሳራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠላትን በመደምሰስ ቦታውን መቆጣጠር ተችሏል ብለዋል፡፡

ይህ አስቸጋሪ ቦታ ከታለፈ ወደ መቀሌ የሚደረገው ቀጣዩ ግስጋሴ እብዛም ፈታኝ እይሆንም ነው ያሉት፡፡ ሰራዊቱ የተራራ ውጊያዎችን ጨርሶ ቁልቁል የሚወርድበት የውጊያ ምዕራፍ ላይ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *