እኛ ኢትዮጵያን ስለምንወዳት ኢትዮጵያዊ ስለሆንክ ዘር ሳንመርጥ ደገፍንህ አንተ ግን ከሀገር የጥፋት ቡድን መረጥክ

የዶክተር ቴዎድሮስን ጉዳይ ከሀሜት አልፎ አየሁት፡፡ በፌስ ቡክ ገጻቸው ያቀረቡት የሰላም ጥሪ ቢያንስ የወገኑለትን ቡድን ለመገሰጽ አልደፈረም፡፡ እሳቸው ቡድንን በሀገር ልክ ሰፈሩ፤ እኛ ቀድሞ እንዲህ ላለው ክብር ሲበቁ ከዘርና ከቋንቋ በላይ ኢትዮጵያዊነታቸው ዋጋ አለው ብለን ከጎናቸው ቆምን፡፡

ትራምፕ ዓለም አጥፊ ሴረኛ አድርገው በኮነኗቸው ጊዜ ከዳር ዳር ለጥቁርም ለኢትዮጵያዊነታቸውም ስንል ድጋፍ ሰጠን፡፡ በዚህ አልጸጸትም፤ ለኢትዮጵያ ሲባል ኢትዮጵያዊን መደገፍ ነውር የሌለው ልክ ተግባር ነው፡፡ በተቃራኒው ለቡድን ሲባል ሀገርን አቅልሎ መመልከት ግን ጸያፍ ነው፡፡

ዶክተር ቴዎድሮስ ለኢትዮጵያዊነታቸው ዘርና ሰፈርን ንቀን የሰጠነውን ዋጋ በጥፋት ቡድን ክብር ቀይረውታል፡፡ ቀና ብለው የማይሄዱበትን ውሳኔ በመወሳናቸው እኛ የቀድሞ ደጋፊዎቻቸው አናፍርም፡፡ ቀድሞም ቢሆን ክብርና ቦታ የሰጠናቸው በኢትዮጵያዊነት ስሜት ነበርና፡፡

የዶክተሩ የሰላም ጥሪ አድር ባይ ነው፡፡ ህጻናትን ለጦርነት ስለሚመለምለው ጁንታ ቡንድ አንድም ትንፍሽ አላለም፡፡ ዓጋመው ዶክተር ቴዎድሮስ በጁንታው ዘንድ የወረደ ቦታ ነበራቸው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እዚህ ግባ የማይሏቸው ሰው ነበሩ፡፡

ውጪ ጉዳይ ሆነው የጁንታው ቡድን አባላት ፖፑሊስት ነህ ብለው ቁም ስቅላቸውን ያሳዩዋቸው ሰው ቢሆኑም ከሀገር የጥፋት ጁንታው በስንት ጠአሙ ብለዋል፡፡ ለመሆኑ የሰላም ጥሪ ጥያቄያቸው ቤተክርስቲያን መሽጎ፤ ህዝብ መሃል ተሰግስጎ፣ ድልድይ እያፈረሰ ሀገር የሚያምስ 100 ሰው ታረሙ ለማለት ለምን ከበደው?

ከአንድ ሉዓላዊት ሀገር መንግስት የሚጠበቀው ሀገር ስትፈርስ ከዱርዬ ሽማግሌ ጋር መደራደር ወይስ ሀገርን የማዳን ዘመቻ ማወጅ፡፡ የዶክተሩ ዓለም አቀፋዊ ሰውነት ለትግራይ ህዝብ መድረስ ካለበት ህወሃትን ተው በማለት ሊተገበር ይገባ ነበር፡፡ ሮኬት አስወንጭፎ ኤርትራን መተንኮስ ውጤቱ ጠፍቷቸው ነው መሰደድን ብቻ የኮነኑት?

ለስደት በሚዳርግ ትንኮሳ የተጠመደውን ጁንታ ከመንግስት እኩል መቁጠርና የሁለት ወገን ጦርነት ማድረግ ቤተሰቡን ይዞ ሌላ ዓለም ለሚኖር ሰው ቀላል ሊመስለው ይችላል፤ እውነቱ ግን ሌላ ነው፡፡ ጁንታው የትግራይም የኢትዮጵያም ጠላት ነው፡፡

ባህር ዳር በሮኬት መደብደቧን ያልሰሙት ዶክተር ቴዎድሮስ በትግራይ በንጹሃን ላይ የአየር ድብደባ ተፈጽሟል ብለው የጁንታውን ክስ በሰላም ጥሪ ስም አስተጋቡ፡፡ ሁሉም ያልፋል፡፡ ኢትዮጵያም በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች፡፡ የትግራይም ልጆች በስማቸው ስለነገዱ እንጂ ለነፍሳቸው ስላልተጨነቁ አጥፊና በስማቸው የሚነግዱ ጁንታዎች ታሪክ ይማራሉ፡፡ (ስናፍቅሽ አዲስ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *