እስቲ እንሞትለታለን ለምትሉት የትግራይ ህዝብ ታሰሩለት፡፡
By: Date: November 14, 2020 Categories: የግል እይታ Tags:

(ከስናፍቅሽ አዲስ) የትግራይን ህዝብ እንወደዋለን ብላችሁናል፤ ደደቢት ወርደን ወጣትነታችንን ጭምር ለጭቁኑ ህዝባችን የሰጠን ነን በሚልም አርባ አመት ነግራችሁታል፡፡ ትናንት በሬዲዮ አንድ ውይይት ላይ አንድ ሀሳብ ሲሰነዘር ሰማሁ፡፡

ሰዎቹ የትግራይን ህዝብ የሚወዱት ከሆነ ለምን እጃቸውን አይሰጡም፡፡ የሚል፤ የትግራይን እናት የሚወዷት ከሆነ ይሄንን ማድረግ ውርደት አይደለም፡፡ እኛ በማናምንበት ጉዳይ ለህግ ከምንቀርብ የትግራይ ህዝብ ከጫንቃው ያሽቀነጠረውን የጦርነት ሰቆቃ ዳግም ቢገባበት ይመረጣል ካሉ ግን ጥያቄው ግለኝነት ነው፡፡

አሁን የሚሆነው መሆኑ አይቀርም፤ ህግ እጅ መግባታቸው ሩቅ ስለማይሆን እድላቸውን ታገልንለት ባሉት ህዝብ ህይወት መሞከር የለባቸውም፡፡ ለህግ ይቀርባሉ ጥፋት ካለባቸው ይጠየቃሉ፤ ወንጀል ከሌለባቸውና የፖለቲካ ቂም ከሆነ እንኳን በህይወታችን ለሰላሙ ዋጋ እንከፍልለታለን ለሚሉት ህዝብ እንደታሰሩለትና መስዋዕት እንደሆኑ ያምናሉ፡፡

ግን አያደርጉትም ስልጣን ከምለቅ ያቺ ለጋብቻ እንኳን አልደረሰችም የምትባል የምታሳሳ ወጣት ሴት የጥይት አረር ቢበላት ይሻላል ባይ ናቸው፡፡ ውጤቱን መገመት ከባድ አይሆንም ቢሸነፉም ቢያሸንፉም ተሸንፈዋል፡፡

ጦርነት የገቡት የተዘረፈ ገንዘብ እፎይ ብሎ ለመብላት ያልቻሉ ቡድኖች ኩርፊያን ተከትሎ ነው፡፡ የዚህ ጦርነት ውጤት ምንም ቢሆን መሳሪያ ያማዘዛቸውን ስኬት ዳግም አያገኙትም፤ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ይህ ምስኪን ህዝብ ለምን ዋጋ ይከፍላል፡፡ እናቱን ለስልጣን ቁማሩ ዳግም ስቆቃ ውስጥ የሚከት ህዝባዊነትስ ጥያቄ ውስጥ አይገባምን?

አስር ሺህዎች የተሰውበት ህወሃት ውስጥ መሽገው ዳግም ለመቶ ሺህዎች የሚተርፍ የሰላም እጦት ስቆቃን የደገሱት ቡድኖች ጸሐይ አልጠለቀችባቸውም፡፡ ጦርነቱን በደቂቃ የማስቆም ሃይል ያላቸው ብቸኛ መፍትሔ ናቸው፡፡ ጥይት እንዳይሰማ ማድረግ በእጃቸው ነው፤ ያም እጃቸውን ለህግ መስጠት ነው፡፡ ያኔ ሰላም ይሆናል፡፡

በትግራይ ህዝብ ላይ ጠላት አልመጣም፡፡ የትግራይን ህዝብ የሚያፍን ወይም የሚያጠፋ አገዛዝም አልተፈጠረም፡፡ የህግ ማስከበር ዘመቻው የሚፈልጋቸውን ሰዎች ይፋ አድርጓል፡፡ ቁጥራቸው ሺህ አይሞላም፡፡

ሺህ ለማይሞላ ተጠያቂ ራስን ከህግ ለማስመለጥ ሚሊዮኖች ዋጋ እንዲከፍሉ የጦርነት ድግስ ደግሶ ክተት ማለት ለህወሃት የማምለጫ እድልን መሞከር ቢሆንም ለትግራይ ህዝብ ግን አይበጅም፡፡

መልካም ሆነው ለህዝብ ካሰቡ እጃቸውን ይስጡ፤ ይህንን ለአንተ ስንል ባይነታቸውን መጠቀም ካልቻሉ ደግሞ የትግራይ ህዝብ እያሳየ እንዳለው አጋርነት መከላከያን አይዞህ እያለ እጃቸውን ለህግ ይሰጣቸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *