የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ግንኙነት ፈቀቅ ያላለው ለምንድነው?

የኢትዮጵያና የኤርትራ የ20 ዓመታት የጦርነትም ሆነ ሰላም አልባ ቆይታ አዲስ ምዕራፍ ያስይዛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የሰላም ግንኙነት ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ተሻገረ፡፡ ሐምሌ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ድንገት በኤርትራ ዋና ከተማ አስመራ የተገኙት በዚያው ዓመት መጋቢት ወር ውስጥ ወደ ጠቅላይ ሚኒስተርነት የመጡት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በዕለተ ሲመታቸው በፓርላማ ባደረጉት ንግግር የገቡትን ቃል ማስፈጸሚያ የሚሆነውን ጅምር አንድ ብለው ጀመሩ፡፡ እስከዚያ ድረስ በቃል ፍላጎትን ከመግለጽ ባለፈ በአንድም ኢትዮጵያዊ መሪ ተደርጎ የማያውቀውን ጉዞ ማድረጋቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሁለቱ አገሮች ችግር መፈታት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያመላከተ እንደሆነ የተነገረለት ድርጊት ነበር፡፡ በተለይ ችግሩን የመፍታት ሒደት በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ መከናወኑ፣ ዕርቁ ትርጉም ያለውና ቀጣይ ይሆናል የሚል ተስፋ እንዲዘራም አድርጎ ነበር፡፡

በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ባሳዩት ቁርጠኝነት ልክ የዛሬ ዓመት ገደማ 100ኛውን የሰላም የኖቤል ሽልማት ያሸነፉ ሲሆን፣ በርካታ ዓለም አቀፍ አድናቆትንና ሙገሳን ያገኙበት ክስተት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ይኼንንም የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአስመራ ጉብኝት ተከትሎ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኡስማን ሳህልህና በኤርትራ ፕሬዚዳንት የፖለቲካ አማካሪ የማነ ገብረ አብ የተመራ ልዑክ አዲስ አበባ መጥቶ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ በኋላም የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከ20 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያን ምድር ለመጀመርያ ጊዜ የረገጡ ሲሆን፣ የአገሮቹን ግንኙነት በተመለከተም ወደፊት አንድ ላይ እንገሰግሳለን ሲሉ አውጀዋል፡፡

እነዚህ የጉብኝት ልውውጦችን ተከትሎም ሁለቱ መሪዎች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ያስችላል የተባለለትንና በኢትዮጵያ ወገን በድብቅ የተያዘውን ስምምነት በአስመራና በሳዑዲ ዓረቢያ ጅዳ የተፈራረሙ ሲሆን፣ ሁለቱን አገሮች የሚያገናኙ የየብስ መንገዶች እንዲከፈቱ፣ ሳምንታዊ የአውሮፕላን በረራ እንዲጀመር፣ እንዲሁም ተቋርጦ የነበረው የስልክ ግንኙነት በድጋሚ እንዲጀመር ተደርጓል፡፡ በሁለቱ አገሮች በድምቀት የሚከበረው በኤርትራ ወገን ቅዱስ ዮሐንስ በኢትዮጵያ ወገን ደግሞ የአዲስ ዓመት ጅማሮ መስከረም 1 ቀን 2011 ዓ.ም.፣ በድንበር ከተማ ዛላምበሳ ሰዎች ከሁለቱም ወገኖች ተምመው እየተቃቀፉና እየተሳሳሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሬዚዳንቱ ባሉበት በጋራ ተከብሯል፡፡ ከዚህ በኋላ ሁለቱም መሪዎች ከአንዱ አገር ወደ ሌላው የጉብኝት ልውውጦችን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን፣ በሁለቱም መሪዎች የተደረጉ ጉብኝቶች በሙሉ ከጉብኝቶቹ በኋላ ወይም አንዱ መሪ ከሌላው አገር ሲደርስ ብቻ ይፋ የሚደረጉ ነበሩ፡፡

ከእነዚህ ጉብኝቶች አንዱ የሆነው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰሞኑ የኢትዮጵያ ጉብኝት ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ ፕሬዚዳቱም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ጋር በመሆን በጅማ የቡና እርሻን፣ የጅማ ዩኒቨርሲቲን፣ የኮይሻን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብን፣ እንዲሁም የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጎብኝተዋል፡፡ ይሁንና በሁለቱም ወገኖች የተሰጡ ቅንጭብ የጉብኝት መዳረሻዎች መግለጫ በስተቀር በእንጥልጥል የቀሩ የሁለቱ አገሮች ግንኙነትን የተመለከቱ ውይይቶች እየተደረጉ ስለመሆኑ ምንም ማመላከቻ አልተሰጠም፡፡ እስካሁን የተደረጉ ስምምነቶችንም ሆነ ሰላሙን ሕጋዊ መሠረት የማስያዝና ግንኙነቱ ተቋማዊ እንዲሆን የማድረግ ጅማሮ ከምን እንደደረሰ ተገምግሞም ከሆነ አልተነገረም፡፡ ሙሉውን ትንታኔ ለመመልከት ይህን ሊንክ ይጫኑ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *