ኮሮናቫይረስ ፡ በአፍሪካ ከሚደረገው የኮቪድ-19 ክትባት ምርምር ጀርባ ያለችው ኢትዮጵያዊት
By: Date: September 22, 2020 Categories: ጤና Tags:

ምህረት አማረ ሱዳን ውስጥ ተወልዳ እድገቷ አሜሪካ ሲሆን፤ አሁን በሥራዋ አማካኝነት አፍሪካ ውስጥ መሥራቷ እንደሚያስደስታት ትናገራለች። ምህረት አማረ ለአሥር ዓመታት በቁስልና በቆዳ ሪጄነሬሽን [ማገገም] የህክምና ላይ በመሰማራት ትሠራ የነበረ ሲሆን አሁን ግን በኮቪድ-19 ክትባት ምርምር ላይ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች።

በባዮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ተመርቃ በጥናትና ምርምር ላይ አትኩራ እየሠማራች ያለችው ለተለያዩ በሽታዎች መፍትሔ ለማግኘት ካላት ፍላጎት እንደነበር ትገልፃለች። ምህረት ለ10 ዓመታት በጥናትና ምርምር ዘርፍ ላይ ከሠራች በኋላ ፍላጎቷን ሰፋ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚከሰቱና አሳሳቢ ለሆኑ የጤና እክሎች መፍትሔ ለማግኘት ጥረት ወደሚደረግበት ዘርፍ መዘዋወርን መረጠች።

ይህንንም ተከትሎ ወደ ትምህርት ዓለም በመመለስ ሁለተኛ ዲግሪዋን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን በማጠናቀቅ ወደ ጥናትና ምርምር ፖሊሲ ማኔጅመንት ተዘዋወረች። በምርምር ተቋሙ ውስጥም ምክትል ዳይሬክተር ሆና በምዕራብ አፍሪካ ውስጥ በኮቪድ-19 ዙሪያ በአህጉሪቱ ውስጥ በመሥራቷ ኩራት እንዲሰማት ከማድረጉ በላይ አፍሪካዊት በመሆኗ ደግሞ ትልቅ ትርጉም እንደሚሰጣት ትናገራለች።

“እንዲህ ዓይነት ሥራ ላይ ስንሰማራ ባህልን መመልከት ያስፈልጋል” የምትለው ምህረት የምታከናው ተግባራ የተሳካ እንዲሆን አፍሪካዊ መሆኗ በጣም እንደሚጠቅማት ታምናለች። በዚህም አሁን እየሰራችበት ያለው የሄንሪ ጃክሰን ፋውንዴሽንም ሆነ “ለአህጉሪቱ ጥሩ ነገር እያበረከትኩ እንደሆነ ነው የሚሰማኝ” ስትል ምህረት ትናገራለች።

ዋልተር ሪድ አርሚ ኢንስቲትዩት ኦፍ ሪሰርች ወይም ውሬይር በመባል የሚታወቀው ድርጅት በአፍሪካ ውስጥ ከተሰማራ 50 ዓመት የሆነው ሲሆን ምህረት የምትሰራበት ድርጅት ደግሞ ይህንኑ የምርምር ተቋም የሚያግዝ ፋውንዴሽን ነው።

በእዚህ ውስጥ የምህረት የሥራ ድርሻ የሚደረጉ የጥናት ፕሮግራሞችን በበላይነት መቆጣጠር ሲሆን፤ በአሁን ሰዓት ለኮቪድ-19 ክትባት ለማግኘት ጥናትና ምርምር የሚደረገውን ሩጫ በቅርብ የመከታተል ኃላፊነት አላት።

“ሥራችን በላይቤሪያ፣ በጋና እና በናይጄሪያ ላይ የሚያተኩር ነው” የምትለው ምህረት ከ6 ዓመታት በፊት ብዙ ሰዎች ለሞት የዳረገውን የኢቦላ በሽታ በቅርበት በመመልከት ወረርሽኙ አጥቅቷቸው የነበሩ አገራት ውስጥ ያሉትን የጤና ተቋማትን የማጠናከር አስፈላጊነት መረዳታቸውን ትገልፃለች። ይህ በተለይ በመካከለኛው እና ምዕራብ አፍሪካ በሚገኙ አገራት ውስጥ ከተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ ብዙ ልምድና ትምህርት መወሰድ መቻሉንም ምህረት ትናገራለች።

በዚህም ምክንያት “በአፍሪካ ውስጥ በተለይ በምዕራብ አፍሪካ የኢቦላ ወረርሽኝ ጉዳት ከፍተኛ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ተሞክሮውን እንደ ልምድ በመውሰድ ለኮቪድ-19 እየጠቀመን ነው” ትላለች።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተስፋፋ ጀምሮ የምህረት ሥራ ለኮቪድ-19 ክትባት ጥናት የሚያስፈልገውን እርዳታ ከማበርከትም በተጨማሪ ለህክምና ባለሙያዎች የሚያስፈልጉ የመከላከያ አልባሳትን (ፒፒኢ) እና ጭምብሎችን የመሳሰሉ መገልገያዎችን ለተለያዩ ማዕከላት እንደሚያበረክቱና ሥልጠናዎችንም እንደሚሰጡ ትናገራለች።ቢቢሲ

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *