እቴጌ ጣይቱ ብጡል ብርሀን ዘ ኢትዮጵያ
By: Date: August 19, 2020 Categories: ታሪክ Tags:

«ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» በሚል ቅፅል ስም የታወቁት እቴጌ ጣይቱ ከአባታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም እና ከእናታቸው ወይዘሮ የውብ ዳር ነሐሴ ፲፪ ቀን ፲፰፻፴፪ ዓ/ም በጌምድር ውስጥ ደብረ ታቦር ከተማ ተወለዱ። በየኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስርዓት መሠረት በተወለዱ በ ፹ ቀናቸው ጥቅምት ፳፯ ቀን ፲፰፻፴፫ ዓ/ም በደብረ ታቦር ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ክርስትና ተነሡ። በልጅነት ዘመናቸው በዚሁ ደብር ውስጥ ዳዊትን ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ በጊዜው ይሰጡ የነበሩትን ሌሎች የሃይማኖት ትምህርቶች በየታላላቁ አድባራት በመዘዋወር ያጠናቀቁ ስለመሆናቸው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ። የተማሩባቸውም መፃሕፍት ተጽፈው ይገኙ የነበረበትን የግዕዝ ቋንቋ አጣርተው ያውቁ ነበር።

እናታቸው ወይዘሮ የውብዳር ከባለቤታቸው ደጃዝማች ብጡል ኃይለ ማርያም ከሞቱ በኋላ በጅሮንድ መዩ የተባሉትን የዓፄ ቴዎድሮስን ባለሟል አግብተው ነበር። እሳቸውም ጣይቱ ብጡል ትምህርት እንዲቀስሙ ለማድረግ ልዩ መምህር ቀጥረውላቸው እንደነበር ይታወቃል። እቴጌ ጣይቱ በማኅደረ ማርያም ሆነው ሲማሩና መፃሕፍትን ይቀጽሉ በነበሩበት ጊዜ ለቤተክርስቲያን መጋረጃ መሥሪያ በትርፍ ጊዜያቸው ፈትል እየፈተሉ ያቀርቡ ነበር። በበገና ቅኝትና ድርደራም በኩል የታወቁ ባለሙያ እንደነበሩ ይተረክላቸዋል።ንጉሡ «አፄ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ» የሚለውን ስም በተቀዳጁ በማግሥቱ ጥቅምት ፳፯ ቀን ፲፰፻፹፪ አ/ም ወይዘሮ ጣይቱ ብጡል እቴጌ ተብለው ተሰየሙ።

የስርዓተ ዘውዱ አፈፃፀም በከፍተኛ መሰናዶ የተጠናቀቀ በመሆኑ እጅግ ደማቅ እንደነበር ከተፃፉ ፅሁፎች ለማወቅ ይቻላል። እቴጌ ጣይቱም ጳጳሱ አቡነ ማቴዎስ ከንጉሠ ነገሥቱ እጅ የተቀበሉትን ዘውድ ደፉላቸው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በታወቁበት «እቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘ ኢትዮጵያ» በሚል የክብር ስም ማኅተም ተቀረፀላቸው። እነዚሁ ታሪካዊ ሂደቶች እቴጌይቱን በኢትዮጵያ ዱኛዊ፣ ወታደራዊና ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ከፍተኛና ብሩህ ሚና ለመጫወት የቻሉ አድርጓቸዋል

እቴጌ ጣይቱ በዱኛ አስተዳደር አንፃር የነበራቸው ችሎታና ተግባራዊ እንቅስቃሴ በታሪክ አዋቂዎች ዘንድ ተደናቂነትን አትርፎላቸዋል። በየጊዜው ይነሱ በነበሩ የሀገር ጉዳዮች ላይ ይይዙት የነበረው አቋም፣ ይሰጡት የነበረው ውሳኔና ያስተላልፉት የነበረው ትዕዛዝ ተሰሚነትና ተቀባይነት እያገኘ እንደመሄዱ መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይሄድ ለነበረው የዱኛ ሥልጣናቸው ዓይነተኛ ምክንያት ነበር።

እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ዱኛ ተሳትፏቸው የገነነውና በአገር አስተዳደርም ውስጥ ከፍተኛ ሚና መጫወት የጀመሩት ኢትዮጵያ ሚያዝያ ፳፭ ቀን ፲፰፻፹፩ ዓ/ም በውጫሌ ላይ ከኢጣሊያ ጋር በተፈራረመችው ውል ውስጥ በጣልያንኛው ትርጉም ሀገሪቷን ነፃነት እንደሌላት ጥገኛ በማስመሰል ዓላማ ላይ የተመረኮዘ ውንብድና መኖሩ ከታወቀ ወዲህ ነው።

ይህ ለአድዋ ጦርነት መነሳት ምክንያትና ዋነኛ መንስዔ የሆነው ጉዳይ ሊታወቅ የቻለው እቴጌ ጣይቱ የውጫሌው ውል አንቀፅ ፲፯ ላይ ዓለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ የተባሉት ቋንቋ አዋቂ ዓፄ ምኒልክ በሰጧቸው ትዕዛዝ መሠረት የውሉን ሰነድ በመመርመር የውሉ አስራ ሰባተኛው አንቀፅ የያዘውን የትርጉም መዛባት በመግለፅ ጉዳዮ ኢትዮጵያ የምትጐዳበት ስለመለሆኑ ጭምር በማስረዳት በሰጡት ቃል ሲሆን እቴጌ በዚህ ወቅት ነገሮችን በጥንቃቄ የሚከታተሉ ስለነበር ዓፄ ምኒልክ በመጀመሪያ ሳይረዱ ዓለቃ ዓፅመ ጊዮርጊስ እንዲታሰሩ ቢያደርጉም እቴጌ ጣይቱ ግን እኒህ ሰው ትክክለኛ የኢትዮጵያ ወዳጅ መሆናቸውን ለዓፄ ምኒልክ በማስረዳት ከሦስት ዓመታት እስራት በኋላ ማስፈታቸው ይታወቃል። በዚህ በኩል ሲታይ እቴጌ ጣይቱ የምኒልክ የቅርብ አማካሪ በመሆን በፖለቲካ ተግባሮች ምን ያህል አስተዋፅኦ እንዳበረከቱ መገንዘብ ይቻላል። እቴጌ እንደተናገሩትም «ዓፅመ ጊዮርጊስ ቢታሰር ቢፈታም ለሀገሩ የሚገባውን ሠርቶ ነው።

ኧረ ለመሆኑ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለው ዮሴፍ፣ ጣሊያኖች በተንኮል ገብተው በማታለል ይህን የመሰለ ሥራ ሲሠሩ አነጋጋሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ሳይስጠነቅቅዎ ቀረ?» በማለት የእቴጌ ጣይቱ የቁጣ መዓት ወደ ዮሴፍ ዞረ። ከዚያም ጨምረው «ከእንግዲህ ወዲህ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚነካ፣ ሥር የሚነቅል፣ መሠረት የሚያፈርስ ጉዳዮን ሁሉ እኔ ሳላየው እንዳያልፍ ይፍቀዱልኝ» ብለው ለንጉሡ ባመለከቱት መሠረት ይኸው አንቺ ሳታይው ሳትመረምሪው አያልፍም በማለት ፈቀዱላቸው፣ ይህ እንደሚያመለክተው እቴጌ ጣይቱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸውን ተገቢ ቦታ የሚያመለክት ነው። ውሉንም ለማስተካከል ዓፄ ምኒልክ ያደረጉት የዲፕሎማቲክ ጥረት ውጤታማ ሊሆን ባለመቻሉ ሚኒስትሮች የጦር አለቆችና መኳንንት የሚገኙበት ጉባዔ እንዲጠራ አደረጉ።

እያንዳንዱ ሰው ስለተነሳው ችግር ያለውን አስተያየት ሀገር ፍቅር በተሞላበት አንደበትና የጋለ መንፈስ ሲገለፅ ቆየ። እቴጌ ጣይቱም በበኩላቸው «እኔ ሴት ነኝ ጦርነት አልወድም። ሆኖም ይህን ኢትዮጵያን የኢጣሊያ ጥገኛ የሚያድርግ ውል ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» ብለው በታሪክ ቅርስነቱ በማንኛውም የሀገሪቱ ትውልድ ትተውት ያለፉት አባባል ዘመን ተለውጦ ዘመን እየተተካ በሄደ ቁጥር የሚነገር በመሆኑ የእቴጌን ጀግንነት የቁርጠኛ ኢትዮጵያዊ ልጅ ለመሆናቸው ሌላ ማረጋገጫ ማቅረብ አያስፈልግም። እቴጌ ጣይቱ ወንድማቸው ራስ ወሌን አተኩረው በማየት በታወቀው ጀግና አንደበታቸው የተሰበሰበውን ሕዝብ ስሜት ለመቀስቀስ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ማድረጋቸው ይነገራል። እሳቸውም፦ «መልኩ ከመልካችን የማይመሳሰል እግዚአብሔር በባህር ከልሎ የሰጠንን አገራችንን የሚቀማ ጠላት መጥቶ እንዴት ዝም እንላለን እንዋጋለን እንጂ» በማለት የሀገሪቱን ቁንጅና ልምላሜ የምታፈራውን የእህልና የከብት ዓይነት እየጠቃቀሱ በማንሳት «ኧረ ለመሆኑ ተራራው ሸለቆው ወንዛወዙ ጨፌው ሜዳው ማነው ቢሉት የማነው ብሎ ሊመልስ ነው እንገጥመዋለን እንጂ!» በማለት የተሰበሰበውን ሕዝብ ልብ የሚነካና ወኔውን የሚቀሰቅስ ንግግር በማድረግ የተዋጣ የቅስቀሳ ችሎታቸው በአገኙት መድረክና አጋጣሚ የሚጠቀሙ አንደበተ ርቱዕ ነበሩ።

ስለ እቴጌ ጣይቱ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በምሳሌነት ሊቀርብ የሚችል ሌላ ዓይነተኛ ታሪክ ዓፄ ዮሐንስ በሞቱ በአንድ ዓመታቸው በመጋቢት ፲፰፻፹፪ ዓ/ም ዓፄ ምኒልክ አገሩን ለማረጋጋት ሲሉ መሃል ትግሬን ለመጐብኘት በሄዱ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ ለሸዋም፣ ለወሎም፣ ለበጌምድርም፣ ለየጁም መካከል በሆነችው ደሴ ከተማ ሆነው አገሩን እንዲጠብቁ በማለት ትተዋቸው እንደሄዱ እዚያ ሆነው ያከናወኑት ተግባር የረጋ አስተዋይና የተዋጣላቸው ዲፕሎማት አሰኝቷቸዋል። በተለይም በሁለት የጦር አበጋዞች መሃል የሚፈጠር አለመግባባትን አግባብቶ በመፍታት በኩል ተወዳዳሪ አልነበራቸውም።

እቴጌ ጣይቱ ከሕዝቡ ጋር በነበራቸው ግንኙነት በተለይም ያሳዩት በነበረው ርህራሄና ልግስና በጣም የተወደዱና የተመሰገኑ በመሆናቸው በሚያውቋቸው ዘንድ በሰፊው ይወራላቸዋል። ግልፅ የሆነው የፖለቲካ አስተያየታቸውና ጽኑ የሆነው ተግባራዊ ውሳኔያቸው፣ ዘዴንና ሥልጣንን እንዲሁም ምክርን ኃይልን ምን ጊዜ በእንዴት ያለ መጠን መጠቀም እንዳለባቸው በትክክል የመገመት ችሎታቸው ሲታይ በዓለም ከታወቁት የፖለቲካ አርበኞች ውስጥ ሊወሳ የሚገባ ታሪካዊ ስፍራ እንዳላቸው አጠራጣሪ አይሆንም። ስመ ጥሩነታቸውን ለማትረፍ ካስቻላቸው ጉዳዮች ጽኑ በሆነ መንፈሳዊ ኑሮአቸው አኳያ የሚታየው የልግስናና የቤተ ክርስቲያን ነፃ ተግባሮች አንዱና ዓይነተኛው ነው። ይህ ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ልዩ ግንኙነት ለመመስረት ያስቻላቸው ከመሆኑም በላይ የፖለቲካ ሥልጣናቸውን ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳደረገ ከሌሎች ታላላቅ የፖለቲካ ሰዎች ታሪካዊ አነሳስ ለመገንዘብ ይቻላል።

በዚህ በኩልም እቴጌ ጣይቱ ብጡል በማህበራዊ ህይወት ሲያደርጉ የነበሩት በጐ ተግባር በመንፈሳዊ ኑሮአቸው በእምነቱ ተከታዮች ያላቸው ተቀባይነትም እጅግ የጐላ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለየካ ቅዱስ ሚካኤል ሠላሳ ጋሻ መሬት፣ ለሐመረ ኖህ ኪዳነ ምሕረት አሥራ ስድስት ጋሻ መሬት የሰጡት ለአብነት ያህል የሚጠቀሱ ናቸው።

እቴጌ ጣይቱ ለኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች መረጋጋት የሚያረጋግጥ የሀገር ግንባታ ተግባሮች በማከናወን ረገድና የአዲስ አበባ ከተማ መቆርቆር በእቴጌ ጣይቱ ከተጠናቀቁት የግንባታ ተግባሮች አንዱ ነው። በመሆኑም የአዲስ አበባ ስም በተጠራ ጊዜ እቴጌ ትዝ የሚሉን ሲሆን በዚሁ በአዲስ አበባ በከፍተኛ ቀበሌ ፲፪/ፒያሳ/ አካባቢ የሚገኘው የከተማዋ የመጀመሪያው ሆቴል «ጣይቱ ሆቴል» የቅርብ ትዝታችን ነው። ምንም እንኳን እቴጌ ጣይቱ የተቀረፀላቸው ሐውልትና ለትውልድ የሚተላለፍ ስማቸውን የሚያስጠራ ልጅ ባለመውለዳቸው /መሐን/ ቢሆኑም የዓፄ ምኒልክን ልጆች አክብሮታዊ ፍቅር ሳይለያቸው ቤተሰባዊ ፍቅርን የተላበሱ እንደነበረ ከተለያዩ መፃህፍት ለመረዳት ይቻላል። ምንጭ እቴጌ ጣይቱ ብርሀን ዘ ኢትዩጲያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *