የመጽሐፍ ዳሰሳ – ሰሞኑን በንባብ የዳሰስኳቸው መጽሐፍ ውስጥ አንዱን ላቅርብላችሁ።
By: Date: July 29, 2020 Categories: ታሪክ Tags:

ርእስ ” የኢትዮጵያ ታሪክ በአስራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን” ጸሐፊ ክቡር ይልማ ዴሬሳ የተጻፈበት ዓ.ም 1959. ዓ.ም ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ታተመ የመጽሐፉ ገጽ ብዛት 248

የመጽሐፉ ይዘት መጽሐፉ አርባ ምዕራፎች ሲኖሩት በኔ አተያይ የመጽሐፉ ይዘት በሶስት ጭብጦች ላይ ያተኩራል። ታሪክን አንደኛው በ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፊት በተለይ በ700 አመታት ውስጥ ስለነበሩት ነገሥታትና የኢትዮጵያ ኁኔታ ያትታል። ሁለተኛ የግራኝን ወረራና ሶስተኛ የኦሮሞ ነገድ አመጣጥና አሰፋፈር የያዘ ነው።

ከ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ኪነ ጥበብ የተስፋፋበት፣ አብያተ ክርስቲያናት በብዛት የታነጹበት፣ የሐረግ ስእል የተስፋፋበት ዘመን ነበር ይላል። (በዚህ አገዛዝ ወቅት አፄ ናዖድ፣ አፄ ይስሐቅ፣ አፄ ዘርአ ያእቆብ ትልቁን ቦታ ይይዛሉ። በተለይ በአፄ ናዖድ ዘመን ሕዝብ ብዙ ፍትሕ ያገኘበት ነበር። (ገጽ 6፣ 11)

በ14 እስከ 15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ አምድ ጽዮን፣ አፄ ሰይፈ አርእድ፣ አፄ ዘርአ ያእቆብ ሡልጣናዊ ግዛቶችን እየወጉ ይፋትን፣ ደዋሮን፣ አዳልን፣ ሐረርን፣ ፈጠጋርን፣ ባሌን መያዝ የቻሉበት ነበር። በወቅቱ ሸዋ የኢትዮጵያ የክርስቲያኖች ልብ ነበረች። (ገጽ 13)

በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአፄ አምደ ጽዮን ታላቅ ግዛት ነበር። በአጼ ልብነ ድንግል ወቅት የጦር አዛዥ ፋሲል ሲሆን በግራኝ ሠራዊት ከሞተ በኃላ አዛዥ ሐመልማል ይገዛው ነበር። ጅማ፣ ከፋ፣ እናሪያ፣ ጃንጀሮ (ኤሉባቦር) ወደ ንጉሡ ግዛት የመለሰው የአፄ ይስሐቅ የጦር ሰራዊት ነው። (ገጽ 14፣ 16)

ለ250 አመታት ከዛጒዌ ሥርወ መንግሥት መውደቅ በኋላ የነገሥታቱ ዋና ተግባር ከቱርክ እና ከእስልምና በወረራ የተያዙትን ግዛቶች ማስመለስ ነበር። በዚያ ጊዜ እስልምና የሚላቸው የቱርክ፣ የአረብ ሀገራት ወረራን ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ የማይረሱ ሁለት ብርቱ ሴት እቴጌዎች አሉ። እሌኒና እቴጌ ሰብለ ወንጌል ናቸው። እሌኒ በአፄ ልብነ ድንግል፣ በአፄ ናዖድ ዘመን ትልቅ የፖለቲካ ሥራን በመስራት የታወቀች ዲፕሎማት መሆኗን ታሪኳን ላነበበ ግልጽ ነው። (ገጽ 25)

እቴጌ ሰብለ ወንጌል የአፄ ልብነ ድንግል ልጅ ሚስት የገላውዴዎስ እናት ናት። እጅግ ውብና ደግ ናት “ሰብለ እንደ ወንዶች ብርታትና እንደ እናቶች ርኅራኄ አጣምራ የያዘች ሴት ነበረች” ተብሎላታል። በግራኝ ወረራ የነበራት ሚና የፖርቱጋሎችን ቁስለኞች ግንባር ድረስ ገብታ ቁስል ታስር፣ ውሃ ታጠጣ፣ ታበላ ነበር። (ገጽ 141)

ይኩኖ አምላክ የይፋት፣ የደዋሮ፣ የፈጠጋር እስላሞችን (ቱርክና፣ አረብ፣ ሱሜሌዎችን) ይዋጋ ነበር። በኋላም ልብነ ድንግል አሸንፎ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ጠቀለላቸው ። ከዚያም ብዙዎችን በጋብቻ አዛመዳቸው። በዚህም የአፄ ዘርአ ያእቆብ፣ የአፄ በእደ ማርያም ፣ አፄ ናዖድ እቴጌዎች (ሚስቶች) ሁሉ ከደዋሮ ከሐዲያ ከምስራቅ ሙስሊሞች ሱልጣኖች ቤተሰብ የተገኙ ናቸው። (ገጽ 33)

በኢትዮጵያ ታሪክ ሒደት ያልተደባለቀ ያልተዛመደ አለ ለማለት አይቻልም። አንድ ወገን ገዛን አጠቃን ማለት አያስደፍርም። ይህ ታሪክን አለማገናዘብ ነው። በዚህ ዘመን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የነበረው የማኅፉዝ ታሪክ ነው። ማኅፉዝ በአፄ ልብነ ድንግል ወቅት የዘይላ ገዥ (ባሕረ ነጋሽ) ነበር። የሱን ታሪክ የጻፈው ፖርቱጋላዊው መነኩሴ አባ ፍራንቺስኮ አልቫሬዝ ነው።

ማኅፉድ በኢትዮጵያ የጅሀድ ጦርነት እንዲቀጥል አክራሪዎችን ለማደራጀት ሰብኳል። በ1508 ዓ.ም. ወደ ደዋሮ፣ ሸዋ፣ ፈጠጋር እየገባ በውጊያ ብዙ ወርቅና እህል እየዘረፈ ወደ አረብ በመሸጥ የጦር መሳሪያ ይገዛበት ነበር። (ገጽ 40)

ማኅፉዝ በጣም አይሎ ስለነበር ወደ አዳል (በአሁኑ አፋር) ዘምቶ ጀግና ካለ ይግጠመኝ ብሎ ነበር። የአፄ ልብነ ድንግል ሠራዊት ገጠመው። ቁመተ ዘንካታው አባ ገብረ እንድርያስ ሔዶ ጦርነት ገጠመ። አባ ገብረ እንድርያስ የማኅፉድን አንገት ቆረጠው። 12 ሺህ አዳልና ሱማሌ በሐምሌ 1508 ሞቱ። ዘይላን ንጉሡ ያዙ (ገጽ 42)

የመጽሐፉ ሰፊውን ክፍል የያዘው የአሕመድ ኢብራሂም (ግራኝ አህመድ) ታሪክ ነው። ግራኝ ያገባው የማኅፉድን ልጅ ድል ወንበራን ነው። ከአባቷ የወረሰችው የክርስቲያኖችን ጥላቻ መሬት ያልነበረውን እስላም ወደ ሰሜን እየሔደ እንዲወር የምታስብ ነበር። ግራኝ ቀስ በቀስ በትንሽ ቀበሌ ተነስቶ የሐረርን አሚር ወግቶ ሐረርን ያዘ። 10 አመት ያክል ጅሀድን ሲያሴሩ ቆዩ። (ገጽ 54፣ 57)

ግራኝ ሠራዊቱን በማደራጀት ድንበር ላይ የነበሩ የክርስቲያን ወረዳዎችን ወግቶ ያዘ። ግራኝ በዋናነት የሚተማመነው በቱርክ ነፍጥ እና በአዳል፣ የሱማሌ ወታደሮች እንዲሁም ከቱርክ የተላከ መድፍ የአረብ ነፍጠኞችን ነበር። ግራኝ መድፍ ተኳሾቹ የሕንድ ወታደሮች ነበሩ። ከየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚዘርፋቸው ወርቅ ፣ ብር፣ የሐር ምንጣፍ የግራኝ የመሳሪያ የመድፍ መግዣ ይውሉ ነበር።

በተለይም የግራኝ ሠራዊት የሚዋጋው ቤተ ክርስቲያን ዘርፎ በሚገኘው ወርቅ ሚስቶቻቸው ስለሚያጌጡ ድሃ ሱሜሌዎችና ቱርኮች ወርቅ ለማግኘትና ሐብታም ለመሆን ይቀላቀሉ ነበር። የሀገሪቱ ንብረት ወርቅ ይከማች የነበረው ለቤተ ክርስቲያን በመስጠት ነበር። ወንጌሉ፣ መስቀሉ፣ ጽዋው የወርቅ ነበር። በነበረው የንግድ ትስስር ሙካሽና ሐር ምንጣፍ ከሶርያ በነጋዴዎች ይመጣ ነበር። (ገጽ 30,33

ምናልባት ዛሬ የምናየው የቤተ ክርስቲያን ምንጣፍና የክህነት አልባሳት የሶርያ ክርስቲያኖች ዲዛይን ይሆናል። የኛ የኢትዮጵያውያን አለባበስ ባሕል ነጭ ነው። ሥርዓተ ቅዳሴውም “የቅዳሴ ልብስ ነጭ ይሁን ቀለም የገባ አይሁን” ይላልና።

ግራኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የልብነ ድንግልን ሠራዊት ሽንብራ ኩሬ ላይ አሸነፈ። ከዚያ ቀን ጀምሮ የእስላም ወገን ለ10 አመት የበላይነት ይዞ ከሐረር ጀምሮ ሀገር እያቃጠለ ሀገር አጠፋ። ቀጥሎ ደዋሮን ባሌን በወረራ ዘረፈ። ሴቶችን ከልጆቻቸው ጋር እየያዘ ወደ አረብና ቱርክ ለባርነት ይሸጣል መሳሪያ መግዣ አደረጋቸው። (ገጽ 68- 71) ግራኝ በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ መዳወላቡ የደረሱትን ኦሮሞዎች ወግቶ አጠፋቸው። በወቅቱ ባሌን ይገዛ የነበረው ደግለሀን ነበር።

ቀጥሎ ወረራውን ወደ አንጾኪያ አዞረ። የምታምረውን ቤተ ክርስቲያን ዘረፈ። ኢትዮጵያ ማስለም ሕልሙ እውን እንደ ሆነ አሰበ። ቀጥታ ወደ አማራው ሀገር ተሻገረ። ዋናውን መቀመጫ ደብረ ብርሃን አድርጎ ሸዋን በሙሉ ያዘ። አብያተ ክርስቲያናት አጠፋ። አፄ ልብነ ድንግል ሰራዊቱን ይዞ ወደ ሰሜን ሸሸ። (ገጽ 72፣74፣ 86፣89)

ግራኝ ከሸዋ ወደ ጎንደር ከዚያም ትግራይን ወረረ። ቀጥሎ ወደ ወሎ ግሸን ሄደ ምንም የቀረው ሀገርና አብያተ ክርስቲያናት አቃጠለ ዘረፈ ሕዝብ ጨፈጨፈ። (ገጽ 89,92,96) ልብነ ድንግል 1532 አ.ም ሞተ። ልጁ አፄ ገላውዴዎስ ነገሠ። ተንቤን ላይ ተዋግቶ ድል ቀናው። ወደ ሸዋ ተመለሰ።

በ1531 ዓ.ም ፖርቱጋሎች የክርስቲያኑን መንግሥት ለማገዝ በሚል 530 ሰራዊት መጡ። ዋናው ጉዳይ ግን እስላሙን ግራኝ ካሸነፋ በኋላ ኢትዮጵያ ካቶሊክን እንድትቀበል ነበር። ግራኝ ከትግራይ ጀምሮ መሸነፍ ጀመረ። 14 አመት ሙሉ ያሸነፈው ግራኝ ቆሰለ። በየውጊያው ተሸናፊ ሆነ። የካቲት 28 ቀን 1535 በፖርቱጋል ወታደር ተመቶ ዘንተራ ላይ ሞተ።

የመጽሐፈ ሶስተኛ ጉዳይ ሆኖ የተገለጠው የኦሮሞን ታሪክ በአጭሩ ይተርካል። በነገራችን ላይ የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊም የወለጋ ኦሮሞ መሆናቸው ይታወቃል። የኦሮሞን ታሪክ ከጻፉ ምኁራን መካከል ልጅ ተድላ ኃይሉ፣ አለቃ አጽሜ፣ አባ ባሕርይ ተጠቃሽ ናቸው።

ኦሮሞዎች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንደ ሰፈሩ በጉልህ አይታወቅም። ከኤደን ባሕረ ሰላጤ እስከ ሶማሌ አውራጃ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እንደ ሰፈሩ ይኖሩ ነበር። (ገጽ 213) በዚህ አካባቢ በ10ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጦርነት ሲገጥማቸው ወደ ምስራቅ ደቡብ በመጓዝ በዋቤ ሸበሌና በጀባ ወንዝ ባሌ ቆላ ወንዞች መካከል ሰፈሩ። በ14 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአፄ ይስሐቅ ዘመን ከሶማሌዎች ጋር ጦርነት ስለነበር የዋቤን ወንዝ ተከትሎ ወደ ደጋው ደቡባዊ ኢትዮጵያ ተሰደዱ። (ገጽ 125)

ቀጥሎም ድርቅ ከሆነው ቦታ ወደ ማርና ወተት የምታፈስ ከተባለችው ከነአን አምሳያ አካባቢ ደረሱ ቦታውንም መዳ ወላቡ አሉት። በአካባቢው ለከብቶች ምቹ ስለሆኑ ከብቶቻቸው በዙ እነርሱም ረቡ። (ገጽ 216) ኦሮሞዎች የሚመሩበት አስተዳደር ሕግ የሚያውጀው የሉባዎች ጉባኤ ነው። ጉባኤው የሚደረገው ሾላ ዛፍ ስር ነው። ኦሮሞ አምልኮ የሁሉ ፈጣሪ የሆነ አምላክ እንዳለ ያምናሉ።

ኦሮሞ በመደ ወላቡ አካባቢ በጣም ተራብተው መሬት ጠበባቸው። በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ወይናደጋው ድረስ እየወጡ መውረር ጀመሩ። አባ ዱላ (የዘመቻ አባት) መምረጥ ጀመሩ። ተጉዘው ኦዳነቤ ገቡ። ከረዩ የተባለው ነገድ ባሌን፣ ፈጠጋርን፣ ደዋሮን ወረረ።

ቱለማ የተባለው ወደ ሰሜን ተጓዘ። ሜጫ እናርያን እንዲይዝ ወሎ ደግሞ ወደ ምስራቅ ተጉዞ ከወሎ እስከ ትግሬ እንዲይዝ ቀየሱ። በግራኝ ወረራ ወቅት ድምፅ አጥፍተው ቆይተው በ1524 ዓ.ም ከደቡባዊ መኖሪያቸው ለቀው ተንቀሳቀሱ። ዋቤን ተሻግረው ባሌ ሲገቡ ፋሲልን አሸነፉ ባሌን ያዙ። ቀጥሎ ወይብን ተሻግረው ያዙ። በ1544 ዓ.ም ፈጠጋርን፣ ደዋሮን በማጥቃት ይዙ።

በወቅቱ ገላውዴዎስ በግራኝ የተቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት ለማሰራት ጎጃም ውስጥ ነበር። (ገጽ 231)ቢዛም ዛሬ ወለጋ የተባለው ጠቅላይ ግዛት የሚገኙት ጋፋቶችና ዲና የተባሉ የእናርያ ጎሳዎች ነበር። በአፍሪካ ከተደረጉ ከመቶ አመት ባነሰ ጊዜው ውስጥ ከተከናወኑ የመሬት ይዞታ የሚያስደንቀው እንደ ኦሮሞ እንቅስቃሴ ታሪክ ነው።

ዝርዝር ታሪኩን ከመጽሐፉ እንዲያነቡ እጋብዛለሁ። የክቡር ይልማ ደሬሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ውጭ ሀገር ሔደው ተምረው ከተመለሱ ምሑራን መካከል ሲሆኑ። አባታቸው አቶ ዴሬሳ አመንቴ እናታቸው ወ/ሮ ጫልቱ ዴንታ ሲሆኑ ምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ከተማ አቅራቢያ ጩታ መንደር በ1900 ተወለዱ።

ወደ ውጭ ሀገር ሔደው እንግሊዝ ሀገር ሄደው በኢኮኖሚክስ ተምረዋል። ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ከጣልያን ወረራ በኋላ የንግድና ኢንዱስትሪ እንዲቋቋም፣ የመንግሥት ባንክ እንዲቋቃም አድርገዋል። በተጨማሪም የጥቁር አንበሳን ጦር መስርተው በአባልነት ሰርተዋል። የኢትዮጵያ የገንዘብ አስተዳደር ትልቁን ድርሻ አበርክተዋል። የጸሐፊውን ባዮግራፊ ሸገር ኤፍ ኤም ስንክሳር ፕሮግራም ሐምሌ 2008 የተሰራ ፕሮግራም ላይ ነው። መጽሐፉን ታነቡ ዘንድ እጋብዛለሁ። መ/ር ንዋይ ካሳሁን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *