የአዲስ አበባ ነዋሪው የማገገሚያ ወቅት ትውስታ

የኮሮና ቫይረስ በአገራችን ከተከሰተ 121 ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ በነዚህ ጊዜያትም ከስድስት ሺህ በላይ ዜጎች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ህይወትም አልፏል፡፡ ከ250 ሺህ በላይ ምርመራም ተከናውኗል፡፡

የምርመራ ሂደቱ አብዛኛው የሚያተኩረው ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንኪኪ ሊኖራቸው ይችላል ተብለው በሚገመቱ አካላት ላይ ሲሆን በስራቸው ምክንያት ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ የተባሉ አካላትም ምርመራ እንዲደረግላቸው ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በዚህም የተነሳ አንዳንዶቹ ምንም ምልክት ሳያሳዩ ሲመረመሩ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ከፊሎቹ ደግሞ በአስከሬን ምርመራ ወቅት ቫይረሱ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስቴር ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ነዋሪ የሆኑት አቶ ሙሉጌታ ደርሶ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የበሽታው ምልክት ባይታይባቸውም ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ ነገር ግን ከምርመራ በኋላ የቫይረሱ ተጠቂ መሆናቸው ተደውሎ ተነገራቸው፡፡ ታዲያ ያልገመቱት ነበርና የተሳሳተ ሪፖርት ነው የመሰላቸው፡፡ እውነቱ ሲረጋገጥ ግን ወደ ለይቶ ማከሚያ ማዕከል እንዲገቡ ተደረጉ፡፡

“ውጤቱ በየደረጃው ሲረጋገጥ የተሳሳተና ለማጭበርበር እንዳልሆነ ስረዳ የሆነ ስሜት ፈጥሮብኛል” የሚሉት አቶ ሙሉጌታ፤ የታመመ ሰው ትንፋሽ አጥሮት በማሽን እየተደገፈ በኦክስጂን አየር የሚወስድ ሳልና ማስነጠሱ ከፍተኛ የህመም ስሜት ይኖረዋል የሚል ግምት ስለነበራቸው ለጊዜው ድንጋጤን እንደፈጠረባቸውም ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም እርሳቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው የገቡበት ሚሊኒየም ማዕከል በርካታ ግለሰቦች ምልክቱ ስለማይታይባቸው ጠንካሮችና ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ፣ የተሰጣቸውን ምግብ በአግባቡ የሚወስዱ “ምንም አልሆንም” የሚሉ ስለነበሩ በሥነ ልቦና ረገድም መረጋጋት መቻላቸውን አውስተዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ፤ በመላምት ደረጃ ካልሆነ በወቅቱ ለቫይረሱ አጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራትን እንዳልፈጸሙ፤ እንደየሥራ ባህሪያቸው ርቀትን በመጠበቅና ጭምብል በማድረግም ጥንቃቄ ያደርጉ እንደነበር፤ በወረዳው ባለ ጉዳዮች ቢሮ ከመግባታቸው በፊት የእጅ መታጠቢያ ጭምር እንደተዘጋጀና ሁሉም ታጥቦ እንዲገባ እየተደረገ እንደሆነ፤ የወረቀት ንክኪም እንዳይኖር ጓንት በማድረግ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸው በጥንቃቄ ህብረተሰቡንም የመደገፍና የቅድመ ጥንቃቄ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱንም አመላክተዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ እንደሚሉት፤ ለቫይረሱ ተጋላጭ ከመሆናቸው በፊት የእንጦጦ መንገድ ፕሮጀክት የወሰን ማስከበር ሥራ ላይ ስለነበሩ በዚህም ወደ 80 ቤቶች ለመንገዱ የሚፈለገውን ቦታ በማስለቀቅ እዛ አካባቢ ግልጽነት ሳይኖር ሲቀር የማስረዳትና የማወያየት ሥራዎች በተናጠል ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ በመላምት ደረጃም ይህ ሥራ ለቫይረሱ ሳያጋልጣቸው እንዳልቀረ ይታመናል፡፡

ማገገሚያ ከመግባታቸው በፊትም ሆነ ከገቡ በኋላ ምልክቱ እንዳልታየባቸው የሚናገሩት አቶ ሙሉጌታ፤ በአጠቃላይ አገግመው ለመውጣት 14 ቀናትን መቆየታቸውንና ከዚያም በኋላ በተደረገ ተከታታይ ሦስት ምርመራ አብሯቸው ከገቡት ሌሎች አራት የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ነጻ ሆነው መውጣት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡ በማዕከሉ እያሉም የወረዳውን ሥራ በስልክና በቪዲዮ ኮንፈረንስ ይመሩ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

“ሚሊኒየም አዳራሽ የለይቶ ማከሚያ የነበረንን ቆይታ በተመለከት መንግስት የሚያደርገው ጥንቃቄ የተሻለና ጥሩ ነው፡፡ እንደ ቫይታሚን ሲ ያሉና የሰውነት የመከላከል አቅምን ሊያሳድጉ የሚችሉ ምግቦች ይቀርባሉ፡፡ የጤና ባለሙያዎች ድጋፍና እንክብካቤ፤ የተሻለ ነው፡፡ በቂ የሆነ አልጋ፣ ብርድ ልብስ፣ አንሶላ በየሰዓቱ ንጽህና እየተጠበቀ በኬሚካል ይጸዳል፡፡ ከምግብ በፊትና በኋላ ንጽህናን መጠበቅ የሚያስችሉ የእጅ መታጠቢያዎች በአቅራቢያው አሉ፡፡ በተለይ ከደም ግፊት ስኳርና ኤች አይቪ ኤድስ ጋር ተያይዞ ተጓዳኝ ህመም ላለባቸው ግለሰቦች ምግብ በሚመቻቸው መልኩ ይዘጋጃል፡፡ እያንዳንዱ ሰው በየሃይማኖቱ ጸሎት የሚያደርግበት ሥፍራ ስለተዘጋጀ ጸሎት እናደርጋለን” በማለት አቶ ሙሉጌታ በማዕከሉ በነበራቸው ቆይታ የተመለከቱትን በጎ ጎኖች ጠቅሰዋል፡፡ ነርሶችም ሀኪሞችም ጭምር ደስ የሚል ስሜት ፈጥረው ከተቋሙ አገግመው የሚወጡትን የሚሸኝበት ሂደትም የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ሙሉጌታ አክለውም፤ ምልክቱ የታየበትም ያልታየበትም፤ እናቶችም አባቶችም ህጻናትም የሚጠቀሙት የጋራ መጸዳጃ ቤትና የጋራ መታጠቢያ ቤት ውስጥ መሆኑን፤ አባቶች እናቶች ህጻናትን ጭምር ይዘው የሚገቡ ነፍሰ ጡሮች ለብቻቸው እንዲሆኑ አለመደረጉ፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ከፍ ባለ ቁጥርና ርቀትን ባልጠበቀ መልኩ መሆኑን በጉድለት መታዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ እድሜያቸው የገፋ፣ ስኳር፣ ግፊት፣ ኤች አይቪ ኤድስ ያለባቸው፣ ነፍሰ ጡር እናቶች ለብቻቸው እንዲያገግሙ ማድረግ በስነልቦናም ራስን ገንብቶ ከመውጣት ይልቅ የማሰብና የመጨነቅ ሁኔታ ስለሚፈጥር ትኩረት ሊሰጠው እንሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ታማሚው ከአልባሳት ጀምሮ የሚፈልጋቸውን ነገሮች ማስገባት የሚችለው በሳምንት አንድ ጊዜ ብቻ መሆኑን የታዘቡት አቶ ሙሉጌታ፤ ከንጽህናና ተያያዥ ጉዳዮች አንጻር ግን ይህ ምቹ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡ አዲስ ዘመን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *