Press "Enter" to skip to content

(title)

የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች ሁከቶች ተከስተው ነበር። በዚህም የጸጥታ ኃይሎችን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል። አሁን መጠኑ በውል ያልታወቁ ንብረትም ወድሟል።

አለመረጋጋቱ ክፉኛ ካናወጣቸው የኦሮሚያ ክልል ከተሞች መካከል ከአዲስ አበባ 165 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ የምትገኘው የባቱ (ዝዋይ) ከተማ አንዷ ናት። በዚህም በከተማዋ ታዋቂ ከሚባሉት ተቋማት መካከል የሚገኙት የአባይ ሆቴል ባለቤት አቶ ሰለሞን ማሞ እና በድርጅቴ ስም ጥሩኝ ያሉት የቫሊ ላንድ ሆቴል ባለቤት ለአስርተ ዓመታት ያፈሩት ንብረታቸው በግፍ እንደወደመባቸው ይናገራሉ።

አቶ ሰለሞን ማሞ ይባላሉ። ተወልደው ያደጉት በዝዋይ ከተማ ሲሆን ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ናቸው።  እርሳቸው እንደሚሉት እናታቸው የተወለዱትም የኖሩትም እዚያው ከተማ ውስጥ ነው። ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የቀን ሥራ ከመስራት ተነስተው በርካታ ንብረቶችን እንዳፈሩ እና 6 ሱቆች፣ ፎቶ ቤት፣ ሆቴል (አባይ ሆቴል)፣ መጋዘን፣ ባለቤታቸው የሚሰሩበት ልብስ ቤት እንደነበራቸው ይናገራሉ።

አቶ ሰለሞን እንደሚሉት የዚያን ዕለት ቀን ላይ ሥራ በዝቶባቸው ስለዋሉ ወደ ቤት የገቡት የንግድ ድርጅቶቻቸውን ሂሳብ እንኳን ሳይሰሩ ነበር። ምንም የሰሙት ነገር አልነበረም። ከዚያ ግን ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ገደማ ስልካቸው ጠራ። በዚያ ውድቅት ሌሊት ስልክ ላለማንሳት ቢወስኑም ከእንቅልፋቸው መነሳታቸው አልቀረም።

በዚህ ወቅት ጩኸት ሰሙ። ጩኸቱ ምን እንደሆነ ለማረጋገጥ በር ከፍተው ሲወጡ “ከፍተኛ የጩኸት ድምፅ ይሰማል ነበር” ይላሉ። እንዳሉን ከሆነ የሆነ አደጋ የተፈጠረ አሊያም ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ እንደተከሰተ ነበር የገመቱት። ሁኔታው ምን እንደሆነ ስላልተገለጠላቸው ተመልሰው ወደ ቤት በመግባት ወደ ተደወለላቸው ስልክ መልሰው ደወሉ።

ይህን ጊዜ ነበር የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል የሰሙት። የሰሙት መርዶ ድንጋጤና ሃዘን ቢፈጥርባቸውም፤ እየጨመረ የመጣው ጩኸትም ቀልባቸውን በተነው። “ከዚያም ከጓደኞቼ ጋር መደዋወል ጀመርን” ይላሉ።

ሆቴሎች፣ መኪናዎች እየተቃጠሉ እንደሆነ መረጃ ደረሳቸው። የስልክ መረጃ ልውውጡም ቀጠለ። ብዙም ሳይቆይ ከጎናቸው ያለ ሆቴልና የሆቴሉ ባለቤት መኖሪያ ቤት ተቃጠለ። ባለቤቶቹ እርዳታ ቢማፀኑንም፤ በወቅቱ ሊደርስላቸው የቻለ አካል እንዳልነበር አቶ ሰለሞን ይገልፃሉ።

ሁኔታው እየከፋ መጣ በየቦታው የቃጠሎ ዜና መጉረፍ ጀመረ። እርሳቸውም ሊታደጉኝ ይችላሉ ያሏቸው ሰዎች ጋር ደጋግመው ቢደውሉም፤ የሁሉም ስልክ ዝግ ነበር። በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ከማለዳው 12 ሰዓት ሆነ።

በዚህ ጊዜ እርሳቸው ሆቴል የሚያድሩ ሠራተኞች ጋር ደውለው “ውጡና እራሳችሁን አድኑ” ሲሉ መልዕክት አስተላለፉ። ትንሽ ቆይቶም በችግር ላሳደገቻቸው እናታቸው መታሰቢያነት በእናታቸው ስም ‘አባይ’ ሲሉ የሰየሙት ሆቴላቸው መቃጠል ጀመረ።

“በዚህ ጊዜ የሆቴሉ ሠራተኞችና ጎረቤቶች ጉዳቱ እንዳይከፋ ሲሊንደሮችን ለማውጣት ሲሞክሩ እነርሱም ላይ ድብደባ ደረሰባቸው” ይላሉ። ታዲያ ይህን ያዩ ጎረቤቶቻቸው ከባለቤታቸውና ከአራት ልጆቻቸው ጋር ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳስወጧቸውና ሕይወታቸውን እንደታደጉላ ቸው ይናገራሉ። መኖሪያ ቤታቸውንም እንደተሰባበረ ጠቅሰው፤ በግምት ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ንብረት እንደወደመባቸው ይገልፃሉ።

ግራጫ መስመር የንግድ ድርጅቴ ታዋቂ ስለሆነ በድርጅቴ ስም ልጠራ ያሉት ሌላኛው ተጎጂ ደግሞ የቫሊ ላንድ ሆቴል ባለቤት ናቸው። እርሳቸውም እንደ አቶ ሰለሞን ሁከቱ ሲፈጠር እርሳቸውን ጨምሮ ከ6 የቤተሰብ አባላቸው ጋር ቤት ውስጥ ነበሩ። ከሌሊት ሰባት ሰዓት ጀምሮ ከፍተኛ ድምፅ እየተሰማ ነበር ይላሉ። ሁከቱ ሲነሳ ግን የድምፃዊውን መሞት እንኳን እንዳልሰሙ ይናገራሉ።

በባቱ ከተማ ተወልደው እንዳደጉ የሚናገሩት ግለሰቡ “ከቀን ሥራ ከልዋጭ ልዋጭ ከቆራሌው ጀምሬ ነው ይህንን ከተማ ሳለማ የኖርኩት” ይላሉ – በ30 ዓመታት ጥረው ግረው ያፈሩት ንብረትም እንደወደመባቸው በምሬት ይገልጻሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ቫሊ ላንድ ሆቴሎች ተቃጥለውባቸዋል። ቁጥር አንዱ ከሁለት ዓመት በፊት የተከፈተ ሲሆን 51 የመኝታ ክፍሎች ነበሩት ቁጥር ሁለቱ ደግሞ አዲስ ሊያስመርቁ ያዘጋጁት 50 ክፍሎችን የያዘ ሆቴል ነበር።

ከዚህም ባሻገር መጋዘን ሙሉ እቃ፣ ቢራ የጫነ አይሱዙ መኪና እና መኖሪያ ቤታቸው እንደተቃጠለባቸው በመግለፅ “አንድም ንብረት የለኝም፤ ከሰው ጋር ተጠግቼ ነው ያለሁት” ሲሉ በደረሰው ጥፋት በጣም ማዘናቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ባለሃብቶቹ ከኅብረተሰቡ ጋር ጥብቅ ትስስር እንዳላቸውና ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የከፋ ችግር አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ይናገራሉ። አቶ ሰለሞን እንደሚሉት በአገሪቷ የተከሰተውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ የሆኑ ሰዎችን ለመደገፍ በተዋጣው 500 ሺህ ብር የተገዛ እህል ጭምር ነው የተቃጠለው ይላሉ።

ንብረታቸውን ሁሉ ያጡት አቶ ሰለሞን ቤተሰባቸው ከዘመድ ጋር እንደተጠጉ እንዲሁም ከእርሳቸው ጋር ይሰሩ የነበሩ 45 ሠራተኞቻቸውም መበተናቸውን አስረድተዋል። “የልማት አምባሳደር ተብዬ የተሸለምኩበት ከተማ ናት፤ ይህንን ጥቃት ምን እንዳመጣብኝ አላውቅም” የሚሉ ት የቫሊ ላንድ ሆቴል ባለቤት በበኩላቸው ከ170 በላይ ሠራተኞቻቸው እና ቤተሰቦቻቸውም እንደተበተኑ በመግለፅ “ለስንት ሰው የምተርፍ ሰው ዛሬ ራሴንም ማስጠለል አቅቶኝ ነው ያለሁት” ሲሉ በተሰበረ ስሜት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱ ሲፈፀም ተጎጂዎችን ለመታደግ ሲጥሩ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎችን መኖራቸውን የሚጠቅሱት የቫሊ ላንድ ሆቴል ባለቤት፤ “ከስንዴ ውስጥ እንክርዳድ ይኖራል” በማለት ጥቃቱን ተከትሎ ድርጊቱን የአንድ ማኅበረሰብን ድርጊት ማድረግ እንደማይገባ ይገልፃሉ።

በወቅቱ ከቤታቸው ሊወጡ የቻሉትም በአካባቢው ነዋሪዎች እርዳታ መሆኑን ይናገራሉ። አክለውም “ጥቃት አድራሾቹ የድምፃዊውን ሞት እንደ አጋጣሚ ተጠቀሙበት እንጂ ድርጊቱ ከዚህ በፊት የተጠናና የተቀነባበረ ይመስላል” ሲሉም ሁኔታውን ይገልጹታል።

“አዕምሮው የተበላሸ ትውልድ አለ” የሚሉት አቶ ሰለሞንም የተመረጡና የሚሰሩ ሰዎች ኢላማ እንደተደረጉ እንዲሁም ጥቃቱን የፈፀሙት ቡድኖች በጣም የተደራጁ እንደሚመስሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃቱን ለመከላከልና ሰዎችን ለመታደግ ሲረባረቡ የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ የሚጠቅሱት አቶ ሰለሞን ምንም እንኳን ዕድሜ ልክ ለፍተው ያፈሩት ንብረት ቢወድምባቸውም ጎረቤቶቻቸው ጥፋቱን ለማስቆም ላደረጉት ጥረት ያላቸውን አክብሮትና ምስጋና ከመግለጽ አልተቆ ጠቡም።

አቶ ሰለሞን አክለውም በዕለቱ ጥቃቱ ከጀመረበት ከሌሊቱ 7 ሰዓት አንስቶ እስከ ምሽቱ 12 ሰዓት ድረስ ያዩት የከተማው የፀጥታ አካል እንደሌለና ምሽት 12 ሰዓት ላይ መከላከያ ከገባ በኋላ በተወሰነ መልኩ ውድመቱ ጋብ ማለቱን ያስታውሳሉ። የቫሊ ላንድ ባለቤት ግን ወዳጆቻቸው የፀጥታ አካላትን ጠርተው በእነርሱ እርዳታ እርሳቸውንና ቤተሰባቸውን ከሞት እንዳተረፉላቸው ያስረዳሉ።

በከተማው ብዙ ሆቴሎችና መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን የጠቀሱት ባለሃብቱ “ከተማዋ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ናት ተመርጦ ነው ጉዳት የደረሰብኝ ለማለት እቸገራለሁ የማውቀው ንብረቴ ብቻ እንደወደመ ነው” ብለዋል።

የአሁኗ ዝዋይ ከተማ በባለሃብቶቹ ዕይታ አቶ ሰለሞን በከተማዋ ላይ በአንድ ቀን ብቻ የተፈጸመው ጥቃት ባቱን 20 እና 30 ዓመታት ወደ ኋላ መልሷታል ብለው ያምናሉ። የቫሊ ላንድ ባለቤትም ከዚህ የተለየ ሃሳብ የላቸውም። “ከተማዋ በ20 ዓመታት እንኳን የምታንሰራራ አይመስል ም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሁለቱም የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት በአካባቢው በተፈጠረው ስጋት በጥቃቱ የተጎዳውም ሆነ ያልተጎዳው ከተማዋን ጥሎ እየወጣ እንደ ሆነም ይናገራሉ። “እንዲህ ዓይነት ነገር ካለ ሰውስ እንዴት ነው ወደ ግንባታ ፊቱን የሚያዞረው? ሰው እንዴት የአገር ሃብት ያወድማል? ነፍሴን ይዤ የወጣሁ ሰው እንዴት ነው ወደ ልማት መመለስ የምችለው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ባለሃብቶቹ ይህንን ጉዳት ያደረሱት ሰዎች ለሕግ እንዲቀርቡ መንግሥትም አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጥሪ አቅርበዋል። በከተማዋ ውስጥ ሰኞ ሰኔ 22 ከሌሊቱ ጀምሮ ማክሰኞ እስከ አመሻሹ ድረስ በተፈጸመው ጥቃትና የንበረት ውድመት በባቱ ከተማ ላይ የደረሰው ውድመት ጥቂት የሚባል አይደለም።

ኃይሌ ሪዞርት፣ ቤተልሔም ሆቴል እንዲሁም ሌሎች በከተማዋ የሚገኙ በርካታ ትላልቅ ሆቴሎችና የንግድ ተቋማት መውደማቸውንም አቶ ሰለሞንና የቫሊላንድ ባለቤት ለቢቢሲ ገልጸዋል። እስካሁን የደረሰውን ውድመትና ጉዳት ለማወቅ የከተማዋ ባለስልጣናት በየቦታው እየሄዱ በመመዝገብ ላይ ሲሆኑ ቢቢሲም ስለደረሰው ውድመት ከኃላፊዎቹ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

 

 

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//soaheeme.net/4/4057774