የዓለም ጤና ድርጅት ኮሮናቫይረስ በአየር ወለድ ብናኞች ሊተላለፍ እንደሚችል ተናገረ

የዓለም ጤና ድርጅት የኮሮናቫይረስ በአየር ላይ እየተንሳፈፉ በሚቆዩ ጥቃቅን ብናኞች ሊተላለፍ ይችላል የሚለውን መረጃ እውነታነት ሊኖረው ይችላል ሲል ተቀበለ። በተለይ ይህ በአየር ላይ በሚቆዩ ጥቃቅን ብናኞች የመተላለፍ ሂደት ሰው ተጨናንቆ በሚገኝባቸው ስፍራዎች ውስጥ፣ ዝግ በሆኑና በቂ አየር በማይንቀሳቀስባቸው ቤቶች እና ቢሮዎች የመከሰት እድሉ እንዳለው ገልጿል።

ይህ ግኝት ከተረጋገጠ በቤት ውስጥ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች ላይ ለውጥ ሊደረግ ይችላል ተብሏል። ለወራት የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 መተላለፊያ መንገዶችን ሲጠቅስ ቫይረሱ የሚተላለፈው ሰዎች በሚያስሉበትና በሚያስነጥሱበት ወቅት በሚወጡ ጥቃቅን ጠብታ ፈሳሾች ነው ሲል ነበር።

እነዚህ ጠብታዎች አየር ላይ ተንሳፍፈው የሚቆዩ ሳይሆኑ ወደ ታች ወርደው በቁሶች አልያም መሬት ላይ ያርፋሉ። ለዚያም ነው እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ እንደ አንድ ቁልፍ መከላከለያ መንገድ ሲነገር የከረመው።

ነገር ግን ከ32 አገራት የተሰባሰቡ 239 ሳይንቲስቶች በዚህ ሃሳብ እንደማይስማሙ በጻፉት ግልጽ ደብዳቤ ተናግረዋል። የእነዚህ ተመራማሪዎች ሃሳብ ቫይረሱ በአየር ምክንያት ሊሰራጭም ይችላል የሚል ነው።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከሚተነፍሱት አየር የሚወጡ ጥቃቅን ብናኞች አየር ኣለይ እየተንሳፈፉ ለሰዓታት ይቆያሉ ባይ ናቸው። ” መረጃውን እንዲቀበሉ እንፈልጋለን፣” ያሉት በኮሎራዶ ዩኒቨርስቲ የኬምስትሪ ምሁር የሆኑት ጆሴ ጂሜኔዝ ናቸው።

“ይህ በዓለም ጤና ድርጅት ላይ የተሰነዘረ ጥቃት አይደለም። ሳይንሳዊ ክርክር ነው፣ ወደ ህዝቡ መውጣት የፈለግነው ከእነርሱ ጋር በርካታ ውይይት ካደረግን በኋላ መረጃዎቻችንን ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው ነው” ብለዋል ለሮይተርስ የዜና ወኪል።

የዓለም ጤና ድርጅት የእነዚህ ተመራማሪዎች ሃሳብ እውነት ሊሆን የሚችልባቸው እድሎች መኖራቸውን ተናግሯል። የጤና ድርጅቱ ይህ በተጨናነቁ ስፍራዎች ወይንም በተዘጉ ቦታዎች ሊከሰት እንደሚችል ተናግሯል።

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊዎች መረጃው የመጀመሪያ ደረጃ መሆኑንና ተጨማሪ ፍተሻ ሊካሄድበት እንደሚገባ መዘንጋት እንደሌለበት አሳስበዋል። ይህ መረጃ በሚገባ እንደሚፈተሽ የተገለፀ ሲሆን እውነታነቱ ከተረጋገጠ የኮሮናቫይረስ መከላከል መረጃዎች ላይ የተወሰነ ለውጥ መደረጉ እንዲሁም በሰፊው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ መጠቀም ሊጀመር እንደሚችል እየተገለፀ ነው። ከዚህም ባሻገር የበለጠ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በተለይ ደግሞ በመጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች እንዲሁም በህዝብ ትራንስፖርቶች ውስጥ ይህ ሊሆን ይችላል ተብሏል። ቢቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *