የፊታዉራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ አስገራሚ ፍርዶች
By: Date: June 29, 2020 Categories: ታሪክ Tags:

ሊያደርጉብህ የማትፈልገውን ነገር በሌላው ላይ አታድርግ::ሁለት ጓደኛሞች ልጆች የሾላ ፍሬ ለመሰብሰብ አስበው አንደኛው ዛፉ ላይ ወጥቶ ሲወርድ ሁለተኛው ከታች እየተቀበለ ይሰበስብ ነበር፡፡ ድንገት ከላይ ያለው ልጅ ይንሸራተትና ታች ያለው ጓደኛው ላይ ይወድቃል በዚህ ሰበብም ሾላውን ይሰበስብ የነበረው ልጅ ይሞታል፡፡

የሟች አባት ጉዳዩን ወደ ዳኞች አቅርቦ የልጄ ገዳይ በሞት ሊቀጣ ይገባዋል ብሎ አቤት አለ፡፡ የተከሳሽ ቤተሰብ ሁለቱ ልጆች ባልንጀሮች እንደነበሩና ልጃቸውም ጓደኛውን የገደለው አውቆ ሳይሆን በድንገተኛ አደጋ ስለሆነ በጉማ (የደም ካሳ) እንዲገላገሉ ጥያቄ ይቀርባል፡፡ ይሁን እንጂ የሟች አባት ይህን ሐሳብ አልቀበልም በማለቱ በነገሩ የተቸገሩት ዳኞች ጉዳዩን ወደ ፊታውራሪ ይመሩታል፡፡ ፊታውራሪም መጀመሪያ የሟች አባት የጉማውን ሐሳብ እንዲቀበል ለማግባባት ይሞክራሉ፡፡

እሱ ግን በእምቢተኝነቱ መፅናቱን ከተመለከቱ በኋላ አባት ገዳዩን ልጅ ለመግደል እንደሚችል ነገር ግን በፍትሐ ነገስት ሕግ መሠረት አገዳደሉ ተመሳሳይ መሆን ስላለበት ሾላ ዛፍ ላይ ወጥቶ ልጁ ላይ በመውደቅ እንደሚሆን ፍርድ ሰጡ፡፡ ነገሩ ያልጣመው ከሳሽም ይቅርብኝ ብሎ ለማፈግፈግ ተገደደ፡፡

ሴተኛ አዳሪም እንደሚስት:: አንድ ሰው አንዷን ሴተኛ አዳሪ ሁለት ማርትሬዛ ከፍሎ ለማደር ይስማማሉ፡፡ በዚያውም ፍቅራቸው ስለጠነከረ አብረው መኖር ይጀምራሉ፡፡ ሰውየው ሀብቱ እየጨመረ ባለፀጋ ይሆናል፡፡ እያደር ግን “እንዴት ሴተኛ አዳሪ አግብተህ ትኖራለህ” የሚለው የዘመዶቹ ውትወታ ላስቀምጥ ስላለው ሌላ ሚስት ሊያገባ ፈልጎ ከቤቴ ውጭልኝ ይላታል፡፡ እሷም ከቤትህ የምወጣ ከሆነ ካፈራነው ሀብት የድርሻዬን አካፍለኝ ትለዋለች፡፡

እሱም አንድ ቀን መጥተሽ እዚህ ቀረሽ እንጂ በሰማኒያ አላገባሁሽ የምን ሀብት ነው የማካፍልሽ ብሎ ያባርራታል፡፡ ሴትዮዋም ለፊታውራሪ ችሎት አቤቱታዋን ታሰማለች፡፡ የታደሙት አስተያየት ሰጭዎችም የሰውየውን ሐሳብ በመደገፍ “የጋብቻ ውል ሳይኖራት ሀብቱን የመካፈል መብት የላትም” ሲሉ ፈረዱ፡፡ በዚህ ጊዜ ፊታውራሪ በጉዳዩ ካሰቡበት በኋላ ሴትዮዋን ስንት ዓመት አብረው እንደኖሩ ጠየቋት፡፡ እሷም አምስት ዓመት መሆኑን ተናገረች፡፡

ይኼኔ ፊታውራሪ፣ “አዬ የሴት ነገር ይህን ያህል ዓመት እንዴት ያለ ጋብቻ ውል ተቀመጥሽ? ስለዚህ ሰውዬው በደስታ ፈነደቀ፡፡ “ይሁን እንጂ” አሉ ወደ ሰውየው ዞር ብለው “አምስት ዓመት ያሳደርካትን መጀመሪያ በተዋዋላችሁት በአንድ ምሽት ሁለት ብር ታስቦ የአምስት ዓመቱን ሂሳብ እንድትከፍላት ፈርጃለሁ” ብለው ደመደሙ፡፡ ሂሳቡ ሲሰላም ከዐቅሙ በላይ ስለሆነበት አብሮ ለመኖር ተገደደ፡፡ (ከታሪክ ድርሳናት – ዘራፍ መጽሀፍት መደብር እንዳጋራው)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *