ነጃሺ የሚባል ንጉሥም ሰውም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ የሰለመ በምድር ላይ አልነበረም። (በአባይነህ ካሴ)

ንጉሥ አርማሕ አልሰለመም እንጅ ሰልሞ ቢኾን ኖሮ ፩ ቤተ ክርስቲያን ታሪኩን በጻፈችው ነበር። የአጼ ሱስንዮስን ከተዋሕዶነት ወደ ካቶሊክነት መለወጥ ጽፋለች። የቀዳማዊ አጼ ዮሐንስን እና የአጼ ቴዎፍሎስን የአጼ ዳዊትን ቅብዓትነት ጽፋለች። አያችሁ ለመሸፋፈን ባሕርይዋ አይፈቅድላትም። ከእነርሱም ሌላ የዮዲት ጉዲትን ይሁዲነት የግራኝን ሙስሊምነት ከእነ ጥፋታቸው ስትጽፍ አልተቸገረችም። እሷ ቅሉ ታሪክ ኤዲት የሚያደርጉትን ትንቃቸዋለች።

አንደኛ ብርቱ ተቃውሞ ይገጥመው ነበረ።የአጼ ሱስንዮስን መኮትሎክ ተከትሎ ከመናንያን እስከ ሊቃውንት አልፎም እስከ ምእመናን ምድርን ያስጨነቀ ተቃውሞ ተካሒዷል። የንጉሡ የገዛ ልጃቸው የኋላው አጼ ፋሲለደስ ሳይቀር በአባቱ ማተብ መፍታት የተነሣ ብርቱ ተቃውሞ አካሒዷል። በሃይማኖት ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ ቀልድ ኖሮ አያውቁም።

በዚያን ጊዜ እንኳንስ ስሙ ያልታወቀው እስልምና ወደ ቤተ መንግሥት ሊገባ ቀርቶ ሀገሪቱ ከኬልቄዶናውያን ግፍ ሸሽተው ኢትዮጵያ የገቡት የተሠዐቱ ቅዱሳን ብርቱ ተጋድሎ እና ትኩስ ስብከት ያልበረደበት። የእነ ቅዱስ ያሬድ በቅድስና የተሞላ ተጋድሎ እንደ እሳት የተቀጣጠለበት

ሁለተኛ እጅግ በርካታ ቅዱሳን የተወለዱበት። ሥርዓተ ገዳም የተስፋፋበት። የተተኪዎቻቸውም ተጋድሎ እንደ አባቶቻቸው ሥር የሰደደበት ስለነበር ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ የመንግሥቱንም የሕዝቡንም ትኩረት በሳበ ወርቃማ ዜና ላይ ነበረች። እና በዚያ ጊዜ የሰለመ ንጉሥ ቀርቶ ተራ ዜጋም ቢኖር ኖሮ በአሉታዊም ኾነ በአዎንታዊ በለሆሳስ ሊታለፍ አይችልም።

ሶስተኛ የዘር ሐረጉ ይገለጥ ነበረ። መቼም እርሱ ብቻውን ሰልሞ አይቀር ነገር። ያውም ንጉሥ ኾኖ። ስለዚህ እገሌ ቢወልድ እገሌ የሚለው የእስልምና ዘር ሐረግ (Islamic genealogy) ቁልጭ ብሎ ይቀመጥልን ነበር። ንጉሡ ሰልሞ ልጁ ምን ኾነ? እንደዚህ ያለ የረባ ጭብጥ በሌለበት ደርሶ ሰልሞ ነበር ማለት ከጉሮሮ አይወርድም።

ቢያንስ በእነዚህ ምክንያቶች በዚያ ዘመን የሰለመ ንጉሥ ዜና ቀርቶ የአንድ ተራ ኢትዮጵያዊ መስለምም ሳይነገር የሚታለፍበት አመክንዮ አይኖርም። አዎ የቤተ ክርስቲያን ባሕርይዋ አይፈቅድላትም። ውድቀትንም ትንሣኤንም ትዘግባለች። ግን እውነት ከኾነ ብቻ።

ይህ ማለት የዛሬ ሙስሊሞችንም ኾነ የትናንቶቹን ማንነት ካለመቀበል አይቆጠርም። እስልምና በታወቀው ታሪኩ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ አይካድም። ተረት ሳይፈጠር በእውነተኛው ታሪክ ብቻ ተከባብረን እና ተፋቅረን ከመኖር የሚያግደንም የለም። ነጃሺ የሚባል ንጉሥም ሰውም በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ የሰለመ በምድር ላይ አልነበረም።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *