ህዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም፡፡ በድሉ ዋቅጅራ
By: Date: May 3, 2020 Categories: ትንታኔ Tags:

የጃዋርንና የልደቱን ውይይት አየሁት ሰማሁት፡፡ ላየው የቀሰቀሰኝ ዋና ነጥብ አንድ ላይ ያመጣቸውን ጉዳይ የማወቅ ጉጉት ነበር አገኘሁት፡፡ ያቀረቡበት መንገድ ነው ልዩነቱ የጀዋር በፖለቲከኛ ብስለትና መሰሪነት የልደቱ በወታደር ጉልበትና ማስፈራራት ከመቅረቡ በስተቀር መስከረም ሰላሳ የመንግስት ህጋዊ ተቀባይነት ስለሚያበቃ መንግስት እኛ የምንለውን የማይቀበል ከሆነ ህዝቡ ከእኛ ጋር ቆሞ መንግስት እንዲቃወም እንዲታገል ነው፡፡

በጎው ነገራቸው ደግሞ መንግስት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሁኔታው ላይ መወያየትና መስማማት አለበት የሚለው ነው፡፡ በርግጥ መንግስት ይህን ማድረግ አለበት። ይህ ሕዝብ በኮሮና ድቀቱ ላይ፣ በፖለቲካ ምክንያት የሚፈጠር ነውጥን የሚሸከም ትከሻ አይደለምየሚሰማ ጆሮ የለውም፡፡

የጃዋርና የልደቱ ትልቁ ችግር ህዝብን በኪሳቸው እንደያዙት ሳንቲም ሲፈልጉ ሊያስቀምጡት ሲፈልጉ ደግሞ አውጥተው ሊጠቀሙበት ደፍነው ለጅምላ ግዢ ዘርዝረው ለችርቻሮ ሊያውሉት የሚችሉት አድርገው መቁጠራቸው ነው፡፡ ህዝቡን እውን ቢያውቁት የትላንቱን ውይይታቸውን ይዘውለት ለመቅረብ ባልደፈሩ ነበር፡፡

በተለይ አዚህ ላይ የልደቱ ድፍረት ለከት አልነበረውም። ከመስከረም ሰላሳ በኋላ መንግስት ስብሰባ እንኳን ለመምራት መብት እንደሌለው ሲናገር ስለራሱ ሀገር የሚያወራ ፈጽሞ አይመስልም። በወረርሽኝ ምክንያት ምርጫ ስለተራዘመበት መንግስት ሳይሆን ሀገር ለቅቄ እወጣለሁ ያለበትን ቀን ስላላከበረ ቅኝ ገዢ የሚያወራ ነው የሚመስለው፡፡ የሚገርመው ከወራት በፊት ልደቱ ተቃዋሚ ፖርቲዎችን አስር ሺህ ፊርማ እንዲያሰባስቡ መጠየቅ ፓርቲዎችን ማዳከምና እንዳይመሰረቱ ማድረግ ነው። ባለበት አፉ ዛሬ መቶ ሚሊየን ህዝብ ከጎኑ እንደሆነ በሙሉ ልብ ሲናገር መስማት ጤንነቱን ያጠራጥራል። ህዝብ እኮ ስልጣን የራበው ሁሉ እየነቀለ የሚጥደው የቦና ጎመን አይደለም፡፡

ውይይታቸውን ልብ ላለ የልደቱና የጀዋር ልዩነት ምንም እንኳን ጃዋር የፓርቲያቸውን የመፍትሄ ሀሳብ ግልጽ ባያወጣውም ለችግሩ የሚያቀርቡት የመፍትሄ ሀሳብ ላይ ነው፡፡ በግሌ የጃዋር ፓርቲ የሽግግር መንግስትን እንደመፍትሄ የሚያቀርብ አይመስለኝም፡፡ ዶክተር መረራ እና ጃዋር እራሱ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎች በመሆናቸው እውቀታቸውን ተጠቅመው የተሸለ ሀሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡

የልደቱ የሽግግር መንግስት ሀሳብ ግን እንዳለው ቀድሞም በቀዳማዊ ኢህአዴግ መውደቅ ፍትጊያ ከሁለት አመት በፊት የነበረ፣ ዛሬም ከኮረና ጋር ያለ ነው፡፡ ልደቱ ከፍተኛ የስልጣን ፍላጎት ያለው ይመስለኛል። በሌላ በኩል ደግሞ የዘጠና ሰባቱ ምርጫ ህዝባዊ ህዝባዊ ቅቡልነቱን እንዳወረደውና የሚፈልገውን የስልጣን እርካብ እንደማያስረግጠው ያውቃል፡፡ በመሆኑም ፓርቲዎች በመዋጮ የሚያቋቁሙት የሽግግር መንግስት ነው ብቸኛ የማርያም መንገዱ፡፡ የኸው ነው፡፡

በርካታ ሀገሮች በኮሮና የተነሳ ምርጫ አራዝመዋል፤ የትኛው ሀገር ነው የሽግግር መንግስት የመሰረተው? የሽግግር መንግስት የተወሰነ ጊዜ ተሰፍሮለት የሚመሰረት ነው፡፡ አሁን ያጋጠመው ችግር ወረርሽኝ ነው ስድስት ወር ወይም አመት ሊወስድ ይችላል፤ አናውቅም፡፡
.
ለሁለቱም ፖለቲከኛ መሆን ካሻችሁ ህዝቡን እወቁት። አክብሩት፡፡ አክብሮታችሁ ቀርባችሁ ከማወቃችሁ ይሁን፡፡ ህዝብን የማያከብር ፖለቲከኛ ህዝብን ሊመራ አይችልም፡፡ ህዝብን አክብሩ፡፡ ህዝብ ጉልበት ስትፈልጉ የምትገዙበት የሚስጢር ኪሳችሁ ሳንቲም። ስልጣን ሲርባችሁ እየነቀላችሁ የምትጥዱት የጓሮአችሁ ጎመን አድርጋችሁ አትኩጠሩት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *