በአሜሪካ ከነዳጁ ይልቅ የበርሜሉ ዋጋ በልጧል የተባለበት ምክኒያቱ ምንድነው? (ትንታኔ)
By: Date: April 21, 2020 Categories: ትንታኔ

በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ከዜሮ በታች ሆነ። ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ቀንሷል። ማጠራቀሚያ ቦታዎችም ተጣበዋል። የአሜሪካ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ደግሞ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከዜሮ በታች ሆኗል። ይህ ማለት የነዳጅ ዘይት አምራቾችን፤ የምርት ማከማቻ ስፍራ በመጣበቡ ገዢዎቻቸው ምርቶች እንዲያነሱላቸው እየከፈሏቸው ነው ማለት ነው።

ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? በዛሬው እለት በመላው አለም መነጋገሪያ ሆኖ የዋለው የነዳጅ ዋጋ ከዜሮ በታች መሆኑ ነው። አንዳንዶች በነዳጅ ማደያ የሚሸጥበት ዋጋ መስሏቸውም እድሉን ለመጠቀም ከቤት የወጡ ሳይኖሩ አይቀሩም። እንዴት ሊሆን ቻለ የሚለውን ከማየታችን በፊት የትኛው የነዳጅ ዋጋ ነው ከዜሮ በታች የሆነው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።

ዛሬ ከዜሮ በታች የሆነው የMay 2020 የወደፊት ዋጋ (futures price) እንጂ ዛሬ ላይ ገዝቶ ዛሬውኑ ለመቀበል የሚያስችለው ዋጋ (spot price) አይደለም። futures price የሚያመለክተው ወደፊት ሻጭ እና ገዥ በተስማሙበት የወደፊት ቀን ለመግዛት ዛሬ ላይ ውል (contract) የሚገባበት ዋጋ ነው። ይህ ደግሞ ለአየር ባየር ነጋዴዎች እድል ይፈጥራል።

የወደፊት ዋጋ እንዴት ከዜሮ በታች ሆነ? ይህን በምሳሌ ብናየው የተሻለ ነው። ለምሳሌ አበበ የሚባል ሰው የነዳጅ ገበያ ላይ የወደፊት ዋጋን መውጣትና መውረድ እየተነበየ አየር ባየር የሚነግድ ሰው ነው እንበል። አበበ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ቦታ የለውም። ከሁለት ወር በፊት May 2020 ላይ ለሚረከብ ነዳጅ በጊዜው የነበረው ዋጋው $20 ነው እንበል። አበበ በገዛበት ጊዜ እና ሜይ መካከል የነዳጅ ዋጋ ይጨምራል ብሎ ስላሰበ በ20 ዶላር ቢገዛ አፈረድበትም።ለምሳሌ በዛሬ ገበያ May ላይ ለሚረከብ ነዳጅ የዉል ዋጋ 30 ዶላር ቢገባ የገዛውን ውል መልሶ በመሸጥ $10 ያተርፋል አየር ባየር።

ነገር ግን በኮሮና ቫይረስ በተከሰተው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ አበበ እንደጠበቀው ዋጋው ጨምሮ አየር ባየር ማትረፍ አልቻለም። ቃል የገባውን ነዳጅ ጊዜውን ጠብቆ እንዳይረከብ ደግሞ ማስቀመጫ ቦታ የለውም። ስለዚህ በአነስተኛ ዋጋ ሊገዛ የሚችል ማስቀመጫ ያለው ነጋዴ መፈለግ ይኖርበታል። ማስቀመጫ ያላቸውም ነጋዴዎች ተመሳሳይ ችግር ውስጥ ነው ያሉት። በአንስተኛ ዋጋ ገዝተው ገዝተው ሲያከማቹ ስለነበር ብዙ ቦታ የላቸውም። ስለዚህ አበበ በ20 የገዛው ነዳጅ በ15 ልሽጥ ቢል ወሳጅ አያገኝም። በ10 እንዲሁም በ5 ልሽጥ ቢል ወሳጅ ላያገኝ ይችላል። ነገ ደግሞ የMay 2020 የወደፊት ገበያ ውል ማስተላለፊያ የሚጠናቀቅበት ነው።

ስለዚህ ማከማቻ ሳይኖረው ቃል የገባውን ነዳጅ ከመረከብ ውል ማስተላለፊያ ጊዜው ሳያልፍበት ተጨማሪ ከኪሱ ከፍሎ የሚረከብለት ማከማቻ ያለው ነጋዴ ይፈልጋል። እድል ይቀናዉና በ20 ዶላር የገዛውን 10 ዶላር ብር ከኪሱ ከፍሎ ማከማቻ ላለው ነጋዴ ውል ያስተላልፋል። የምናውቀው ሻጭ ሲከፈለው ነው እንጅ ከፍሎ ውሰዱልኝ ሲል አይደለም። ይህን ጊዜ ነው የነዳጅ ዋጋ ከዜሮ በታች ገባ የሚባለው። ሻጭ ሊከፈለው ሲገባ ከፍሎ ሲሽጥ ማለት ነው። ይህን ካላረገ ያለው አማራጭ ነዳጁን በገባው ውል መሰረት መረከብ ነው። እሱ ደሞ አይታሰብም አየር ባየር ለሚነግድና ማከማቻ ለሌለው ሰው። በሽመልስ መኮንን

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *