ባህላዊ ሕክምና፣ ኮሮና ቫይረስ እና የእጸዋት መድኃኒት ዶ/ር መስፍን ታደሰ (የእጸዋት ተመራማሪ)

ሚያዝያ ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም (April 11, 2020) አንድ ኢትዮጵያዊ ጓደኛዬ ስልክ ደወለልኝና ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ቆይ እስቲ ሌሎች ሰዎችም አሉ አለኝና ስልኩን ክፍት ተወው። ወዲያው ሰላምታ ተለዋወጥን። ስልኩ ውስጥ ሌሎች አምስት ጓደኞች መኖራቸውን አወቅሁ።

ለካስ ያገናኘን በያለንበት ሆነን ስለሚወራው የኮሮና ቫይረስ ዜና ብዙ ጥያቄዎች ስላሉ፣ ውይይት እንድናደርግ ነበር። ቴሌ ኮንፈረስ (tele conference) መሆኑ ነበር። ሁሉም ስለኮሮና በቂ ግንዛቤ ነበራቸውና (ሐኪም፣ ኢንጂነር፣ ጋዜጠኛ፣ ወዘተ ናቸው) መሠረታዊ የሆኑትን በመተው አሳሳቢ ስለሆነባቸው ብቻ ውይይት ጀመርን።

፩ኛ ኮሮና ዓየር ውስጥ ተንሳፎ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል?

፪ኛ መሬት ከተበተነ በኋላ ወይም ዕቃ ላይ ለስንት ጊዜ ይቆያል?

፫ኛ ክትባቱ እስከሚገኝ ጊዜ ድረስ ከታወቁት ጥንቃቄዎች ውጭ ማድረግ ያለብን ሌሎች ጥንቃቄዎች ምንድ ናቸው? ወዘተ የሚሉነበሩ።

በእነዚህ ላይ ከተወያየን በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረጉ እና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣቸው ልዩ ልዩ የጥንቃቄ ምክሮች መንገዶች ሃሳቦች ወዘተ ስንወያይ በሌሎች በበለጸጉ አገሮች የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ሀገራችን ውስጥ እንዴት ሊተገበሩ ይችላሉ? የባለሙያ እና የዜና አውታሮች ሚናዎችስ እስከ ምን ድረስ ይሄዳሉ? የሚሉትን ጥያቄዎችን እያነሱ ስንወያይ

አንደኛው ጓደኛችን የባህላዊው የህክምና ሙያን አስተዋጽዖንም አነሳ። ኢትዮጵያ መድሃኒቱን ወደ ማግኘት ደረጃ ደርሳለች የሚባለው ምን ያህል ሥራ ተሰርቶ ነው? የባህል ሃኪሟ እኔ ያለኝን ዕውቀት ሰጥቻለሁ ብለዋልና የትኛው ዕጽ ነው ለዚህ በሽታ መድሃኒት የሆነው? የቻይና የባህል ሕክምና እርዳታ ምንድነው? ምን ያህል ይሄዳል? የወባ ኪኒን ለዚህ በሽታ በመከላከያነት በእርግጥ ያገለግላል ወይ?

አሪቲ ለወባ መድሃኒትነት ይውላል የሚባለው ምን ያህል እውነት አለው? ለኮሮና ሕክምና ሊውል ይችላል? ለመሆኑ ቫይረስ ዕጸዋትን ያጠቃል ወይ? ቫይረሱን ለመከላከያ ሊውሉ ይችላሉ የሚባሉት እንደ እነ ፌጦ፣ ዝንጅብል፣ ኮረሪማ፣ ሬት ወይም ዕሬት፣ ጤና አዳም፣ ወዘተ በሳይንሱ የተደገፉ ናቸው ወይ? የሚሉ እና በሌሎችም ጥያቄዎችና ስጋቶች (ኮሮና ቫይረስ ሰው ሰራሽ ነው? ዕውን ከእንስሳ የተላለፈ ነው? በሚሉ ሃሳቦች ላይ ተወያየን።

የእኔን አስተያየቶችን እና የእነርሱን አንዳንድ መልሶችን ለአንባቢያን ግንዛቤ እንዲረዳ እንደሚከተለው አቀርቤዋለሁ። በተመሳሳይ ሙያ መስኮች ያሉም የበኩላቸውን እንዲያክሉበት ወይም አስተያየቶቻቸውን እንዲሰጡ እጠይቃሁ።

፩ኛ፣ ኮሮና ዓየር ውስጥ ተንሳፎ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? – አዲስ ቫይረስ ስለሆነ እስከ አሁን አይታወቅም፣ በአንድ መርከብ ላይ ከ፲፯ (17) ቀን በኋላ መገኘቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ይሞታል” ከሚለው ሃሳብ ጋር እንደሚጋጭ አሳስቧል። “ቫይረስ ሞተ” ማለት በውስጡ የያዘው ዘረ-መል (DNA, RNA) እና በእነዚህ ውስጥ ያሉ ወይንም እነርሱን የፈጠሩት በራሂዎች (Genes) መባዛታቸውን አቆሙ ማለት ነው። ይህም የሚረጋገጠው በላቦራተሪ ጥናት ነው።

፪ኛ፣ መሬት ከተበተነ በኋላ ወይም ዕቃ ላይ ለስንት ጊዜ ይቆያል? – እስከ አሁን አይታወቅም አዲስ ቫይረስ ስለሆነ።

፫ኛ፣ ክትባቱ እስከሚገኝ ጊዜ ድረስ፣ ከታወቁት ጥንቃቄዎች ውጭ፣ ማድረግ ያለብን ሌሎች ጥንቃቄዎች ምንድ ናቸው? – እንደ የህክምና ባለሙያዎች አገላለጽ አንድ ሰው አፉን እና አፍንጫውን በመሃረብ፣ ወይም ድንገት የመጣ ማስነጠስ ከሆነ፣ የግራ እጁን ወደ አፍ እና አፍንጫው አጥፎ በማስጠጋት እዚያ ላይ ማነጠስ አለበት።

አፍ እና አፍንጫን በንጹህ መሃረብ፣ ስካርቭ፣ ጨርቅ ሁል ጊዜ መሸፈን፣ ምንም እንኳን ጽዱ ባይመስልም፣ ለራስ ጥንቃቄ የሚገባ ነው። ከዛሬ ወዲያ ይህ እየተለመደ መሄድ ይኖርበታል፣ ቢያንስ ክትባቱ እስከሚገኝ።

፬ኛ፣ ኢትዮጵያ መድሃኒቱን ወደ ማግኘት ደረጃ ደርሳለች የሚባለው ምን ያህል ሥራ ተሰርቶ ነው? – አልታወቀም፣ መልስ እንጠብቃለን።

፭ኛ፣ የባህል ሃኪሟ እኔ ያለኝን ዕውቀት ሰጭቻሁ ብለዋልና የትኛው ዕጽ ነው ለዚህ በሽታ መድሃኒት የሆነው? – አልተገለጸም፤ ምናልባት የምርምሩ እና የምርት ሂደቱ የመጨረሻው ደረጃ እስከሚደርስ ድረስ ስለሚጠበቅ ይሆናል። ይህም የተለመደ አሰራር ነው። የምርቱ እና የመድሃኒቱ የባለቤትነት ጉዳይ መጠናቀቅ ስላለበት ነው።

፮ኛ፣ የቻይና የባህል ሕክምና እርዳታ ምንድ ነው? ምን ያህል ይሄዳል? – ለዚህ መልሱ ምናልባት በሂደት ይገለጽ ይሆናል። ለጋዜጠኞች እና ለዜና አውታሮች በየጊዜው እና እንደ ሂደቱ መጠን መግለጫዎችን ይሰጣሉ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ጋዜጠኞች በትጋት እንዲከታተሉና ለሕዝብ እንዲያሳውቁ አደራ ሰጥተናል።

፯ኛ፣ የወባ ኪኒን ለዚህ በሽታ በመከላከያነት በእርግጥ ያገለግላል ወይ? – በአኃዝ ላይ የተመሰረተ በቂ ጥናት የለም። በሞት አፋፍ ላይ ላሉ እና ለነበሩ ተሰጥቶ እንደነበረ የተገለጸ ወይም ታትሞ የወጣ ሳይንሳዊ ጽሑፍ አላየንም። ልብ በሉ እዚህ ላይ፣ የኮሮና ታማሚዎች ይውሰዱት እያለ የአሜሪካው መሪ ብቻውን የሚወተውተው፣ የተለያየ ወባ መድሃኒት ነው። በመጀመሪያ የተገኘው ሲንኮና (የሳይንስ ስሙ Cinchona officinalis) ከሚባል ፔሩ አገር ከሚገኝ ዛፍ ነው። የፔሩ ገበሬዎች ነበሩ ለአውሮፖውያን ጥቅሙን የነገሩ።

፰ኛ፣ አሪቲ ለወባ መድሃኒትነት ይውላል የሚባለው ምን ያህል እውነት አለው? ለኮሮና ሕክምና ሊውል ይችላል? – ቻይናዎች እነርሱ አገር ከሚገኝ የአሪቲ ዘመድ ከሆነ ዕጽ (የሳይንስ ስሙ Artemisia annua ከሆነ) የወባ መድሃኒት ሰርተዋል፤ ስሙም አርተሚ ሲኒን (Artemisinin) ይባላል። አሪቲ (የሳይንስ ስሙ Artemisia abyssinica) በሃገራችን ከሽቶነት ሌላ በባህላዊ መንገድ ለብዙ ግልጋሎቶች ውሏል፣ ለምሳሌ የወር አበባ ለማስተካከል፣ በመውለድ ጊዜ የሚደርስን የደም ብዛት ለማስተካከል፣ እና ለሆድ ህመም ማስታገሻ፣ ጥቂቶቹ ናቸው። ስለ ኮሮና መድሃኒትነቱ የሚታወቅ ነገር የለም።

፱ኛ፣ ለመሆኑ ቫይረስ ዕጸዋትን ያጠቃል ወይ? -አዎን፤ የመጀመሪያው ቫይረስ የተገኘው ከዕጽ ነው፣ ከትምባሆ፣ የሳይንስ ስሙ ኒኮቲያና (Nicotiana tabaccum) የሆነ።

፲ኛ፣ ቫይረሱን ለመከላከያ ሊውሉ ይችላሉ የሚባሉት እንደ ፌጦ፣ ዝንጅብል፣ ኮረሪማ፣ ሬት ወምዕሬት፣ ጤና አዳም፣ ወዘተ በሳይንሱ የተደገፉ ናቸው ወይ?–

በመጀመሪያ ልብ በሉ፣ እንዲህ ዓይነቱ እውቀት ያለው በታዳጊ አገሮች ውስጥ ነው፤ ታዳጊ አገሮች ደግሞ በምርምር የገፉ አይደሉም። በተጠቀሱት አንዳንዶቹ ዕጸዋት ውስጥ ያሉትን ጥሬ ነገሮች የደም ነጭ ሕዋሳትን በሽታ የመከላከል አቅምን እንደሚያዳብሩ በጥናት ይታወቃል (immune system boosters; antioxidants ናቸው)፣ሆኖም በቀጥታ በቫይረሱ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት አይታወቅም።

፲፩ኛ፣ ኮሮና ቫይረስ ሰው ሰራሽ ነው? ዕውን ከእንስሳ የተላለፈ ነው? – መልስ የለንም፣ እንጠብቃለን። ከእንስሳት ወደ ሰው የሚተላለፉ ብዙ በሽታዎች አሉ፣ ይታወቃሉ።

ይህ የእንስሳት ሃኪሞች ሙያ ነው። እነርሱ (zoonotic diseases) ይሏቸዋል፣ ይህ ከቫይረስ፣ ባክቴርያ፣ እስከ ጥቃቅን ጥገኛ ህዋሳትን (protozoa and fungi) ያጠቃልላል።

እስከ አሁን ስለ ኮሮና መነሻ የሚጻፈው፣ የሚነገረው ሁሉ በሳይንስ ጥናት እስካልተደገፈ መላ ምት ነው የሚሆነው። ከምንጩ ያሉ ሳይንቲስቶች፣ ቻይናም ሆነ አሜሪካ፣ ወደ ፊት የሚጽፉትን እንጠብቅ። ምንጭ፡ ኢትዮ ኦንላይን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *