“ግዛዋ ካለ ከደጅሽ …”
By: Date: April 8, 2020 Categories: የጤና መረጃ,ጤና

መነሻ

ግዛዋ (ጊዜዋ) በኢትዮጵያ የባህል ህክምና ውስጥ “ሁለገብ” ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ሁለገብ ማለት ለሁሉ ሰው፣ ለሁሉ በሽታ አገልግሎት ይሰጣል እንደ ማለት ነው፡፡ እንዲሁም መላ የተክሉ ክፍል ሥሩ፣ ቅጠሉ ወዘተ ለመድኃኒት ይውላሉ፡፡ ለዚህ ነው  “ ጊዜዋ ካለ ከደጅሽ፣ ለምን ታመመ ልጅሽ?” የሚባለው ተረት የሚነገረው፡፡ ይህ ማለት ግዛዋ በደጃፍሽ እያለ ከቅጠሉ ወይ ከሥሩ፣ ማጠጣት  ስትችይ ምን ነክቶሽ ነው ልጅሽ እንዲህ የሚታመምብሽ? ብሎ እናትየዋን እንደመውቀስ፣ ስንፍና ይዟት እንደሆን ለማጎበዝ ይመስላል፡፡ ይህን የጥንት ተረት ወደ ዛሬ ኢትዮጵያ አምጥተን እንዲህ እንላለን፤ “ግዛዋ ሞልቶ በዱርሽ፣ ምነው ሰብሳቢ ሰው አጣሽ?!” ሌላው ቀርቶ የህንድ ጊንሰንግ (Indian ginseng.) ተብሎም ይጠራል፡፡ “የኢትዮጵያ ጊዜዋ” እንዳይባል ወይ ተረስቷል ወይ ተዘሏል፡፡ አልያም ህንዶች በአግባብ ስለተጠቀሙ በስማቸው ተጠርቶ ይሆናል፡፡

ግዛዋ በሳይንሳዊ መጠሪያው ዊታኒያ ሶምኒፌራ (Withania somnifera) በእንግሊዘኛ አሽዋጋንዳ (Ashwagandha  Withania,  Indian ginseng.) ይባላል፡፡ በግዕዝ፣ ዕፀ ግዕዝ፤ በኦሮሚፋ ግዛዋ ወይም ዋሃሌ (Gizawwa, Wahalle)  ይባላል፡፡

በብዙ የጭሳጭስ ነጋዴዎች ዘንድ በጣም ይታወቃል፡፡ ሥሩ ተቆራርጦ፣ ደርቆ ከነ ቀበርቾ  እና ሌሎች የጭሳጭስ ሥራሥሮች ወዘተ ጋር አብሮ ለገበያ ይቀርባል፡፡ በተለምዶ ጭሱ ተውሳክ ያስወግዳል ይባላል፡፡

በባሕል ሐኪሞች ዘንድ ብቻውን ወይም ከሌሎች ዕፀ መድኃኒት ተክሎች ጋር ተቀምሞ ሥሩ እና ቅጠሉ ለብዙ ሕመም መድኃኒትነት ይሰጣል፡፡

ይህም ሆኖ ጊዜዋ የሚፈለገውን ያህል በአገራችን ለልማት አልዋለም፤ ለጠቀሜታም አልዋለም፣ ተሻሽሎ አልቀረበም፤ ከቶውንም ሥሩ እየተነቀለ ማንም ባልገመተው መንገድ ወደ ውጭ እየተሸጠ ነው፡፡ ምናልባትም በጥሬ ዕቃ ደረጃ ሲሸጥ በጭራሮ ዋጋ ይሸጥ ይሆናል፡፡ የገዙት ብዙ ሙያ ይሰሩበታል፡፡ በፋብሪካ ከተቀናበረ በኋላ በውድ ዋጋ ለዓለም ገበያ ያቀርቡታል፡፡

ሀ/ ጊዜዋ በሌሎች አገራት

ጊዜዋ በሌሎች አገራት ምን ይቀጠሙበታል?

በዚህ https://www.healthline.com/nutrition/12-proven-ashwagandha-benefits#1 መረጃ መረብ ላይ እንዲህ ይነበባል፡፡ ከጊዜዋ የሚዘጋጅ ንጥረ መድኃኒት 12 ያህል የጤና ጠቀሜታዎች አሉት፡፡

 1. በህንድ ከ ሶስት ሺ አመታት በላይ ጠቀሜታ ላይ ውሏል፡፡ ጭንቀት ለማስወገድ፣ ኃይል ለመስጠት እና የሰው ትኩረት ለማሻሻል የታወቀ ነው፤
 2. ለዓይነት 2 የስኳር ታማሚዎች የደም ስኳር መጠንን ለመቀነስ ይረዳል፤
 3. የዕጢ ዕብጠት ሴሎችን (tumor cells) ለመግደል እና ብዙ የነቀርሳ ዓይነትን (several types of cancer) ለማስወገድ ይረዳል፤
 4. በከፍተኛ ጭንቀት ወይም ውጥረት ውስጥ ያሉ ታማሚዎችን የኮርቲሶል መጠን በመቀነስ (lower cortisol levels ) ይረዳል፤
 5. በእንስሳትም ሆነ በሰው ላይ የተደረጉ ብዙ ጥናቶች ጊዜዋ ጭንቀትን እንደሚቀንስ ታውቋል፤
 6. ድብርትን ይቀንሳል፤
 7. የወንድን ቴስቶስትሮን በመጨመር ( increase testosterone) የዘር ፍሬን ያሻሽላል፤
 8. የጡንቻን ይዘት በማጎልበት፣ የሰውነትን ስብ በመቀነስ፣ የወንዶችን ጥንካሬ ይጨምራል፤
 9. የበሽታ ገዳይ ሴሎችን ሥራ በማጎልበት፣ የሰውነት ብግነትን ወይም መቆጣት ይቀንሳል፤
 10. ከፀረ ብግነት ብቃቱ በተጨማሪ የልብን ጤና ያሻሽላል፣ ይህም ኮልስትሮል እና ትራይግላይስራይድ (reducing cholesterol and triglyceride levels) መጠንን በመቀነስ ነው፤
 11. የአዕምሮን ተግባር፣ አስተውሎትን፣ ምላሽ ቶሎ መስጠት እና ሥራን የማቀላጠፍ ብቃት ያሻሽላል፣
 12. ብዙ ሰዎች ሊወስዱት ይችላሉ፡፡ ለብዙዎች ተስማሚ ነው፡፡ ከሥሩ ተጣርቶ የተዘጋጀውን ከ45ዐ እስከ 5ዐዐ ሚሊግራም ካፕሱል በቀን አንዴ ወይም ሁለቴ መውሰድ ይቻላሉ፡፡ ቢሆንም መውሰድ የማይገባቸው ሰዎች አሉ፡፡ እርጉዝ እና የሚያጠቡ እናቶች፤ የሪህ ብግነት ያለባቸው፤ ዓይነት አንድ የስኳር ታማሚ፣ የታይሮይድ መድሐኒት ሕክምና በመውሰድ ላይ ያሉ እና ሌሎችም ጥንቃቄ የሚሻቸው ሰዎች፡፡

ለ/ ጊዜዋ ልማቱ ይቅደም፤

ለማልማት ዘሩን መጠቀም ነው፡፡ ባፈራበት ወራት ፍሬው ይቀላል፡፡ ይህን ቀይ ፍሬ ለቅሞ አፍርጦ በጥላ ቦታ ማድረቅ ነው፡፡ ዝናብ በጀመረበት ወራት በማሳ ዳርቻ፣ በጓሮ ወይም በሰፊው ማልማት በተፈለገበት ስፍራ መዝራት ነው፡፡ ሥሩ እስከ ሁለት አመት ውስጥ ለጠቀሜታ ይደርሳል፡፡

የግዛዋ ፍሬ ምስል

ሐ/ ጊዜዋ እጥርብ ቅጠል

የጊዜዋ እርጥብ ቅጠል ምስል 

እርጥብ ቅጠሉን በቀላሉ በቤት ውስጥ ቀጥሎ ባለው መጠቀም

በብርድ ቁስለት፣ በነርቭ ሕመም ወይም በሌላ አፉ ወደ አንድ ወገን ጠሞ፣ ዓይን ፍጥጥ ብሎ የሚታመሙ በቅጠሉ እንዲህ አድርገው እራሳቸውን ያክሙበት፡፡

 • ጤናማ ሰፊ ቅጠሎችን መቀንጠስ፣
 • ማታ ፊትን በአብሽ ሊጥ እያሹ መታጠብ፣
 • ሊተኙ ሲሉ ቅጠሉን ሞቅ እያደረጉ ፊት ላይ በሙሉ ደህና አድርጎ ማልበስ፣
 • ከላይ ፊትን ሸፍኖ መተኛት፣
 • ማለዳ ፊትን በሞቀ ውሃ እና በሳሙና መታጠብ፣
 • ውጤቱን እያዩ ለተወሰኑ ቀናት ወይም ለሳምንት እንደዚህ መታከም፡፡

መ/ ጤናማ ቅጠሎችን መልቀም እና ማድረቅ

የግዛዋ ቅጠል በብዙ ተባይ ይበላል፡፡ ለመድኃኒት እርጥብ ቅጠሉ ሲለቀም በምንም ተባይ ያልተበሉ እና ሰፋ ሰፋ ያሉ መሆን አለባቸው፡፡ ብትን አድርጎ በጥላ ቦታ ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡ ከዚያም ደረቁን አሽጎ መስቀመጥ ወይም አድቅቆ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡

ደረቅ ቅጠሉ ለመድኃኒታማ ሻይ እንዴት እንደሚውል በዚህ

https://lavalheureuse.com/boutique-web/en/ashwagandha-leaves-herbal-tea-p152/

መረጃ መረብ እንዲህ ቀርቧል፡፡

የጊዜዋ ደረቅ ቅጠል ለዕፀዋት ሻይ ይሆናል፡፡  በብረት ማዕድን ይዘቱ ከፍተኛ ስለሆነ ለደም ማነስ እጅግ ይረዳል፡፡ አረጋጊም ነው፣ አነቃቂም ነው፡፡

 • ነርቭን ያነቃቃል፣ Nerve Tonic
 • አበረታች ቶኒክ፣ Regenerative tonic
 • አስተውሎትን ያግዛል፣ Promotes memory
 • ለጥሩ እንቅልፍ ይረዳል፣ Promotes a restful sleep

ደረቅ ቅጠሉን ሻይ ለማዘጋጀት

አንድ ሾርባ ማንኪያ ደረቅ የግዛዋ ቅጠል፣ በአንድ ኩባያ የፈላ ውሃ ውስጥ ለ 5 ደቂቃ መዘፍዘፍ፤ በቀን ከ 1 እስከ 3 ኩባያ መጠጣት፡፡

ሠ/ ሥሩን መሰብሰብ

ሥሩን በጥንቃቄ መንቀል እና መሰብሰብ ለሌላ ጊዜ ጠቀሜታ ላይ ለማዋል ይረዳል፡፡ ምንም እንኳ አሁን የትም የሚገኝ ዕፀዋት ቢመስለንም፤ ግዛዋ በአሁኑ አያያዝ ሊጠፋ ወይም ሊመናመን ይችላል፡፡ ዋጋውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ ነው፡፡ ተክሉን ሥሩን ለመድኃኒት ለመንቀል ስትፈልጉ ሙሉ በሙሉ አለመንቀል ነው፡፡ በአንድ በኩል መቆፈር እና ጠንከር ያሉ ሥሮችን መቁረጥ ነው፡፡ ቀጥሎም አፈሩን መሸፈን እና ለሌላ ጊዜ እንዲያድግ መተው ነው፡፡

የተሰበሰበውን ሥር በተቆፈረበት ዕለት ወድያው ማጠብ፣ ከነልጣጩ እያለ በመጠን እንደ ጌሾ መቁረጥ እና በጥላ እና ነፋሻ ቦታ ማድረቅ ያስፈልጋል፡፡ በሌላም በኩል ለዚሁ ሲባል የተዘጋጀ መሣሪያ ያለው ሰው በእርጥብነቱ ማድቀቅ፣ በአግባቡ ማድረቅ ከዚያም ወደ ዱቄት ዓይነት መቀየር እና ማዘጋጀት ይችላል፡፡

ረ/ ከሥሩም የጤና ሻይ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡

ከላይ በተነገረው ጥንቃቄ ዓይነት የተዘጋጀውን የግዛዋ ሥር የደረቀውን፣ አንድ የቡና ስኒ ያህል ሰፍሮ በአንድ ሊትር ውሃ ለ15 ደቂቃ ያህል ማፍላት፡፡ እስከ 6 የሻይ ብርጭቆ ይገኝበታል፡፡ ቀላ ያለ ከታች በምስሉ ላይ ያለውን መልክ ይሰጣል፡፡  እንደ አስፈላጊነቱ በቀን እስከ ሁለት ሻይ ብርጭቆ ወይም ማታ መጠጣት ይቻላል፡፡ ያለ ስኳር፣ በትንሽ ስኳር ወይም በማር ማጣጣም ይቻላል፡፡

የጊዜዋ ሥር ሻይ

ማጠቃለያ፣ 

በአገር ደረጃ ስለ ጊዜዋ ብዙ ነገር ማድረግ ይመከራል፡፡ በሰፊው ማልማት፣ ብዙ ምርምር ማድረግ፣ ግዛዋ ባለበት ጥሩ አያያዝ እንዲደረግለት ማድረግ፣ ከጓሮም ሆነ ከዱር የአሰባሰብ እና የአያያዝ መመሪያ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ግዛዋ በተለይም ለነርቭ ህመም እና ለነቀርሳ ከፍተኛ ተስፋ የሚጣልበት የመድኃኒት ተክል ነው፡፡

ይህ ጽሁፍ መጀመርያ የወጣው ኢትዮ ላይን ድረገጽ ላይ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *