ሲንጋፖር ከ20ሺህ በላይ የውጪ አገር ዜጎችን በለይቶ ማቆያ ውስጥ አስቀመጠች

ሲንጋፖር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋ በመምጣቱ 20 ሺህ የውጭ አገር ሠራተኞች በማደሪያ ክፍላቸው ውስጥ ለ14 ቀናት እንዲቆዩ አዘዘች። እነዚህ ሠራተኞች የህንድ የታይላንድ የስሪላንካና የባንግላዲሽ ዜግነት ያላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

ሠራተኞቹ በሁለት የተለያዩ ህንፃዎች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን 13 ሺህ ሠራተኞች ያሉበት አንዱ ማደሪያ ውስጥ ብቻ 63 በቫይረሱ መያዛቸው የተረጋገጠ ሲሆን 6800 ሠራተኞች ባሉበት የማደሪያ ሕንፃ ደግሞ 28 ታማሚዎች ተገኝተዋል።

የሲንጋፖር መንግሥት ወደ እነዚህ ሁለት የመኖሪያ ህንፃዎች ማንም እንዳይገባና እንዳይወጣ ሲል የእንቅስቃሴ ገደብ አስቀምጧል። እነዚህ ህንጻዎች ከደቡብ እስያ ለሚመጡ የግንባታ ሠራተኞች ማደሪያ በመሆን የሚያገለግሉ ናቸው ተብሏል።

ሠራተኞቹ በክፍላቸው ለአስራ አራት ቀን ሲቆዩ ክፍያቸው የማይቋረጥ ሲሆን በቀን ሦስቴ እንዲመገቡ ይደረጋል ተብሏል። የሠራተኞቹን ደሞዝ አሰሪያዎቻቸው የሚሸፍኑ ሲሆን የምግባቸውንም ወጪ እንዲችሉ ተደርጓል ተብሏል።

ነገር ግን ክፍሎቹ በሰው ብዛት መጨናነቃቸውና ንጽህናቸው አለመጠበቁን አንስተው የሚተቹ አልጠፉም።

ነዋሪዎቹም ቢሆኑ እነዚህ ማደሪያዎች የንጽህና ክፍላቸው የሚያፈስ ምግብ ለማግኘት ረዣዥም ሰልፍ የሚደረግባቸውና በበረሮ የተሞሉ መሆኑን ይናገራሉ።

በሲንጋፖር ፑንጎልና ዌስቲት የሚገኙት እነዚህ ማደሪያዎች ሙሉ በሙሉ መውጣትና መግባት ተከልክሎባቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *