የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በወንበር ልክ ብቻ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ከዛሬ ጀምሮ ተሳፋሪዎችን በወንበር ልክ ብቻ በመጫን አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ገልጿል። የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ባቡሩ በቀን በአማካይ 110 ሺህ ሰዎችን ያስተናግድ ነበር።

የኮሮናቫይረስ በኢትዮጵያ ከተከሰተ በኋላ ደግሞ እለታዊ የማስተናገድ አቅሙን ወደ 45 ሺህ ሰዎች ዝቅ አድርጎ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ሰርቷል። ሆኖም የቫይረሱ ስርጭት እንዳይኖርና በተገቢው ርቀት ለማስተናገድ ሲባል የትራንስፖርት አገልግሎቱን ከዛሬ ጀምሮ በወንበር ልክ ብቻ አድርጓል።

ከባቡሩ ጎን ለጎን 10 የጎልደን ባስ ትራንስፖርት አውቶቡሶች ከአያት እስከ ጦር ሃይሎች እንዲሁም ከጊዮርጊስ እስከ ቃሊቲ የባቡር መስመሩን ተከትለው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉን ዶክተር ስንታየሁ ገልጸዋል። አውቶቡሶቹ ይህንን አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ ያደረጉት በላይነህ ክንዴ የተባሉት ባለሃብት መሆናቸውም ታውቋል። በቀጣይ የተሳፋሪዎች ቁጥር እየታየ የባሶቹ ቁጥር ከፍ እንዲል የሚደረግ መሆኑም ተገልጿል። ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *