ኢዜማ የቀጣዩ አገር አቀፍ ምርጫ ቀንን መወሰንም ማራዘምም የሚችለው ፓርላማው ነው ሲል ኦነግ ፓርላማው መወሰንም ማራዘምም አይችልም ብሏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የምርጫ ሰሌዳውን እንደሰረዘ መግለፁ ይታወሳል፡፡ አሁን ያለንበት የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫ እንድናደርግ ስለማይፈቅድ ይራዘም ከሚሉት ፓርቲዎች መካከል የነበረው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ኢዜማ

ምርጫ ቦርድ ራሱ አውጦት የነበረውን የጊዜ ሰሌዳ ነው መሰረዙን የገለፀው እንጂ ምርጫው መተላለፉንና መቼ እንደሚደረግ የመወሰን ስልጣን ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ብሏል፡፡ ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ነው መካሄድ ያለበት ከሚሉት ፓርቲዎች መካከል የነበረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በበኩሉ የተወካዮች ምክር ቤት ብቻውን የምርጫ ቀን ማራዘምም መወሰንም አይችልም ብሏል፡፡

የኢዜማ ህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ቦርዱ ምርጫ የማራዘምም የምርጫ ቀን የመወሰንም ስልጣን የለውም፤የምርጫ ቦርድም ይሄን እንዲወስንበት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው የላከው ብለዋል፡፡

አቶ ናትናኤል ምርጫው አይደረግም ወይም ምርጫው በዚህ ጊዜ ነው የሚደረገው የሚለውን የምንሰማው ገና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ብለዋል፡፡ ምርጫውን የተመለከተ ማንኛውም ውሳኔ ግን መወሰን ያለበት የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የባለድርሻ አካላትን አመለካከት ከግምት ባስገባ መልኩ መሆን ነው ያለበት ሲሉ አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

የኦነግ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኦቦ ቀጀላ መርዳሳ ለጣቢያችን እንዳሉት ደግሞ ምርጫ ቦርድ ብቻውን የምርጫ ጊዜ ማራዘም አይችልም የተወካዮች ምክር ቤትም ብቻውን የምርጫ ቀን ማራዘምም መወሰንም አይችልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኦቦ ቀጀላ የተወካዮች ምክር ቤት የስልጣን ዘመን ማለቂያ ላይ እንዲህ ያለ ነገር ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት ህገ መንግስቱ ላይም የተቀመጠ ነገር ስለሌለ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ሁሉ ሊወያዩበትና ሊመክሩበት ይገባል ብለዋል፡፡

ከእጩዎችና ከመራጮች ምዝገባ አንስቶ አጠቃላይ ቅድመ ምርጫ ዝግጅቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ካልተከናወነ ደግሞ የምርጫውን ቀን መግፋታቸው አይቀርም በሚል ጉዳዩን እንዲያዩት ለተወካዮች ምክር ቤት ላኩት እንጂ ምክር ቤቱ የስልጣን ዘመኑ ባለቀበት ሁኔታ የምርጫ ቀን መወሰን አይችልም ብለዋል ኦቦ ቀጀላ፡፡

ወረርሽኙ የአለምን ስራ እንደማቆሙ እኛም በቤታችን ሆነን ነው እየሰራን ያለነው ያሉት ፓርቲዎቹ ወረርሽኙ በአለምና በሀገር የመጣ እንደመሆኑ ከመንግስት ጋር በመሆን እሱን ተረባርበን መግታት አለብን ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *