ኢሳት ውስጥ በነበርኩባቸው ጊዜያት የደበኳችሁ ነገር ቢኖር ቢሮ ስገባ ብቻዬን ተንበርክኬ ለኢሳት ስኬት ጸሎት ማድረጌን ነው -ጋዜጠኛ ደረጀ ሃ/ወልድ ከኢሳት ስለመልቀቁ
By: Date: April 3, 2020 Categories: ሁነቶች

ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተ ወልድ ለዘጠኝ አመታት ካገለገለበት ኢሳት የቴሌቭዥን ጣቢያ መልቀቁን አስመልክቶ ለአክባሪዎቹና ለወዳጆቹ የሚከተለውን መልዕክት አስተላልፏል።

በዘሀበሻ ደረጀ ከኢሳት ለቀቀ የሚለው ዜና ከተሰማ በኋላ በርካታ ወዳጆቼ እውነት ነው ወይ? የሚል ጥያቄ እያቀረባችሁልኝ ነው።
በአጭሩ አዎ እውነት ነው።

ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በሠራተኝነት ሳይሆን በትግል መንፈስ ካገለገልኩበት ከኢሳት ከለቀቅኩ አንድ ወር ሆኖኛል። ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት የኤዲቶሪያል ፖሊሲውን ጠብቄና አክብሬ በቻልኩት አቅም የተሰጠኝን የሥራ ድርሻ ሳላጓድል ከማንም አንሳለሁ ብዬ ሳልሸማቀቅ ከማንም እበልጣለሁ ብዬ ሳልኩራራ ኢሳትን ልክ እንደ ቤቴ ባልደረቦቼንም ልክ እንደ ወንድሞቼና እህቶቼ በመቁጠር፤ በፍጹም ታማኝነት አገልግያለሁ።

ኢሳት ሲነሳ አንግቦ የያዘውን ዋነኛ ተልዕኮ ሲያሳካም አብሬ በመኖሬ ኩራት ይሰማኛል። ከሁሉም በላይ በኢሳት በቆየሁባቸው ዘጠኝ ዓመታት ሙያዬን በመተገንም ሆነ ኢሳትን ሽፋን በማድረግ የፈጸምኩት ህሊናን የሚጎረብጥ አንዳችም ነገር ባለመኖሩ ደስ ይለኛል።

ምናልባት ኢሳትን አስመልክቶ በተደጋጋሚ በድብቅ የፈጸምኩት ነገር ቢኖር ምሽት ላይ በሰላም ያዋልከኝ አምላክ በሰላም አሳድረኝ ስል አለያም አንዳንዴ ቀደም ብዬ ብቻዬን ቢሮ ስገባ- እዚያው ቢሮ ውስጥ ተንበርክኬ ስለ ኢሳት ስኬት ጸሎት ማድረጌ ነው።

በቆይታዬ አብራችሁን ለነበራችሁ የኢሳት ወዳጆች ብቻ ሳይሆን በፈጸምናቸው ስህተቶች ሳቢያ ስትነቅፉን ለነበራችሁት እንዲሁም የጥንካሬያችን ምክንያት ለነበራችሁት ለምትጠሉን ሁሉ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ። ሁላችሁንም እወዳችኋለሁ።

አሁን ለቀሩት ባልደረቦቼም መጪው ጊዜ የስኬት እንዲሆንላችሁ ምኞቴ ነው። ከእንግዲህ ግን ከኢሳት ጋር ፋይሌን ዘግቻለሁ። ዝርዝሩ ስለማይጠቅም ለጊዜው ይቆዬን። ለኢሳት ተከታታዮቼ ከእንግዲህ ከእኔ ጋር የምንገናኘው ላሳድጋትና ላሻሽላት እያሰብኩት ባለችው የዩቲዩብ ቻነሌ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *