ጃዋር መሀመድ ሀገራዊ ጥሪ አስተላለፈ
By: Date: March 23, 2020 Categories: የጤና መረጃ Tags:

በዚህ ወቅት የኮሮና ቫይረስ ሀገራችን መግባት ብቻ ሳይኾን፣ መስፋፍቱንም ማመን ይገባናል። እንደ ሀገር ባሳየነው ያልተገባ ቸልተኝነት ምክንያት በአሁኑ ወቅት ቫይረሱ ቢያንስ እስከ ዞን ከተሞች እንደደረሰ ይገመታል። በሚቀጥለው ወር ሚያዚያ (April) አጋማሽ ላይ ቁጥሩ ከፍተኛ ደረጃ ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ይኼን ኹኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ከእንግዲህ ትኩረታችን ምን መኾን አለበት የሚለውን በተመለከተ የተወሰኑ ነጥበችን ማስቀመጥ እፈልጋለሁ፡፡

1) ቫይረሱ በደረሰባቸው ከተሞች ውስጥ የበለጠ እንዳይስፋፋ መረባረብ። ይህን ለማድረግ ሳይውል ሳያድር በከተሞች፣ ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች መካከል የሚደረግ ጉዞ ላይ እቀባ ሊደረግ ይገባል፣

2) ያልደረሰባቸው ከተሞች እና የገጠር መንደሮች እንዳይገባ መሞከር። ለዚህ ደግሞ በከተሞች እና ገጠር መንደሮች መካከል የሚደረግን ጉዞ ማስቆም፤ በተለይ ደግሞ ገጠር እና ከተሞች የሚገናኙባቸውን ገበያዎች ለጊዜው ማስቀረት፣

3) በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ውስጥ የህመም ምልክት የሚያሳዩት ወደ ህክምና ማዕከላት በማድረስ ነፍስ ለማዳን የሚያስችል ፈጣን የሎጂስቲክ ዝግጅት ማድረግ፣

4) የህክምና ተቋማት እና ባለሞያዎች ኮሮናን ለመቋቋም ሲጠመዱ፣ የሌላ የውስጥ ደዌ በሽታ ህመምተኞች በትኩረት አናሳነት እንዳይጎዱ ከአሁኑ ቀድሞ መዘጋጀት፣

5) ወረርሽኙ የሚያስከትለውን ማኅበራዊ ቀውስ (ለምሳሌ ከቀብር ጋር የተያያዘ) ለመግታት መላ ማበጀት፣ 5) ወረርሽኙ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ቀውስ (በተለይ የምግብ እጥረት) ለመቋቋም ከአሁኑ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ፣

6) ወረረሽኙ የሚፈጥረውን መደናገጥ እና መተርማምስ ሊያስከትለው የሚችለውን የጸጥታ መናጋት ለመግታት ፈጣን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ፡፡ እነዚህን ሥራዎች በተሳካ ኹኔታ ለመከወን ከፍተኛ ርብርብ እና ቅንጅት ይጠይቃል። ኾኖም ዋናው ኋላፊነት በጤና ባለሞያዎች እና በጸጥታ ኋይሉ (መከላከያ እና ፖሊስ) ላይ ይወድቃል።

ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ (አምላክ አይበለውና) አብዛኛው የሲቪል አመራር የቤት ቁራኛ ስለሚኾን እምብዛም ሚና አይኖረውም። ስለዚህ የጤና ባለሞያዎች እና ወታደሩን ካሁኑ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ይህ ማለት በዋነኝነት ሥነ-ልቦናዊ ዝግጅት ነው፡፡ የችግሩን ግዝፈት እና የሚወድቅባቸውን ኋላፊነት አውቀው አእምሯቸውን እንዲያዘጋጁ ያግዛል፡፡ በተለይ የጸጥታ ኋይሉ መንግሥት ዜጎች ላይ ሊያስተላልፍ የሚችላቸውን ገደቦች ከማስፈጸም በተጨማሪ አስፈላጊውን ግብዓት ማጓጓዝ እና ማከፋፈልም ስለሚኖርበት ይህንን ግዳጅ ከሕዝቡ ሳይጋጭ ሊከውን የሚችልበትን ዝርዝር እቅድ ማውጣት ይኖርበታል። የጤና ባለሞያዎችም ኾኑ ወታደሩ ይህንን ኋላፊነት ለመወጣት እራሳቸውን ከቫይረሱ መከላከል አለባቸው። ለዚህም ከበሽታው የመከላከያ ቁሳቁሶች ከማንኛውም ማኅበረሰብ አስቀድሞ ለእነሱ በበቂ ኹኔታ መድረስ እና መከፋፈል አለበት።

ህዝባችን ፈታኝ ጊዜ ስለሚጠብቀው በቀረችን ጊዜ በፍጥነት እና በትብብር በመዘጋጀት እና በመተግበር የከፋ አደጋ እንዳይደርስ ሁላችንም የበኩልችንን ሀለፊነት እንወጣ!

(ጃዋር መሀመድ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *