የአድዋ ድል መዘዝና ዓባይ
By: Date: February 29, 2020 Categories: ታሪክ Tags:

አድዋ የኢትዮጵያን ነፃነት ያስከበረ ክዋኔ ብቻ ሳይሆን፣ የጥቁር ሕዝብ በዘረኞችና በቅኝ ገዢዎች ላይ ኃይለኛ በትር ያሳረፈ ሂደት ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዕድልም ከሌሎች የአፍሪቃ አገሮች ሊለይ እንደቻለ እውን ነው፡፡ ኢትዮጵያን ቅኝ ከማድረጉ ውጥን በስተጀርባ ጣሊያን ብቻ አልነበረችም፣ እንግሊዝም ዋነኛዋ አካል በመሆኗ፣ አድዋ የእሷም ሽንፈት ጭምር ነበር፡፡ እንግሊዝ ዓባይን ለመቆጣጠር የነበራትን ህልም አድዋ አጨለመው፡፡

የዓባይ ተፋሰስን ለመቆጣጠር በእንግሊዝና በፈረንሳይ መሀል ሽኩቻ ይካሄድ የነበረ ሲሆን፣ የአድዋ ድል በተጠናቀቀ ማግስት ፈረንሳይ አፍሪቃን ለመቆጣጠር የነደፈችውን ውጥን በስራ ለመተርጎም ጥረት ጀመረች፡፡ ከዚህ የፈረንሳይ እቅድ ጋር በተያያዘ፣ ፋሾዳ በሚባል የሱዳን ከባቢ ከእንግሊዝ ጋር ተፋጠጡ፡፡

ዓባይ ንብረቷ እንደሆነ እንግሊዝ ታስብ የነበረ ሲሆን፣ በአንድ ወቅት የእንግሊዝ ከፍተኛ ባለሥልጣን እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል፤

“መጋቢት 28 ቀን እአአ 1895 ዓም፣ ሰር ኤድዋርድ ግሬይ፣ በእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስቴር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (የእንግሊዝ ፓርላማ) ንግግር ባደረገ ጊዜ፣ የዓባይ ተፋሰስ ከላይ እስከታች በግብጽና በእንግሊዝ ሥልጣን ክልል ውስጥ ስለሆነ፣ ማናቸውም ሌላ መንግስት ጣልቃ ለመግባት የሚያደርገውን ሙከራ የእንግሊዝ መንግስት ወዳጅነት የተሳነው አቋም አድርጎ እንደሚመለከት ገልጾ(ጸ)…፡፡ ሰለዚህ….የዓባይ ተፋሰስ በእኛ ስር ስለመሆኑ ክርክር ውስጥ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ ዓባይ እንደቤታችን ነው” አሉ፡፡

ከአድዋ ድል ቀደም ሲል፣ ማለትም እ.ኤ.አ መጋቢት 24 እና ሚያዚያ 15 1891 ዓም፣ ዓባይን በተመለከተ ጣሊያን እጇን እንዳታስገባ በኢጣልያንና በእንግሊዝ የተፈረመው ፕሮቶኮል ደንግጓል፡፡

ውጥኗ ሁሉ የተመሰቃቀለባትና ዐባይን ለመቆጣጠር ባሰበችውና በፈለገችው አቅጣጫ መጓዝ ያልቻለችው እንግሊዝ ሌላ ፖሊሲ ነደፈች፡፡ ሶስቱ የቅኝ ገዥዎች፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኢጣልያን እአአ ታህሳስ 13 ቀን 1906 ዓም ለንደን ላይ ተገናኝተው ኢትዮጵያን በተመለከተ መራኮት እንዳይኖር ስምምነት አደረጉ፡፡

በዚሁ ስምምነት መሰረት፣ ወደሽ ነው ገጣቢት እንዲሉ፣ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነት ሊጠበቅ እንደሚገባ ሁሉም ተስማሙ፡፡ በስምምነቱ አንቀጽ 4 ላይ፣ ዓባይን በተመለከተ፣ “የእንግሊዝና የግብጽ ጥቅም እንዳይነካ ሦስቱ መንግስታት” ተመካክረው እንደሚሰሩ ሰፈረ፡፡

ስለስምምነቱ መረጃው የደረሳቸው አፄ ምንሊክ፣ “….እንደሚታወቀው ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሉዐላዊ መብት ነው ብለን በምንገምተው ማናቸውም ጉዳይ ላይ በምንም ዓይነት የተባለው ውል ገደብ ሊሆን አለመቻሉን በዚሁ አጋጣሚ እናሳስባለን” አሉ፡፡

ከዓባይ ጉዳይ በተጨማሪ፣ በአድዋ ድል ማግስት ቀደም ሲል ግብጽን ድል ያደረገው ሱዳን ላይ እንግሊዝ ዘመተ፡፡ ከሁለት አመት ዘመቻ በኋላም ሱዳን በእንግሊዝ ቅኝ ግዛትነት ስር ወድቆ፣ ነጭ ዓባይ በእንግሊዝ ቁጥጥር ስር ዋለ፡፡

እንዲያ በመሆኑም፣ አድዋ ለኢትዮጵያ ነፃነት፣ ለሱዳን ባርነትን አስከተለ፡፡ የአድዋን ድል ተገን በማድረግ፣ መጀመሪያ በግብጽ ኋላ ላይ ደግሞ በሱዳን ስር ውሎ የነበሩትን እነ አሶሳን፣ ኮማሻንና ቤኒ ሻንጉልን የሚያጠቃልለውን ምዕራባዊ ክፍል አፄ ምንሊክ በቁጥጥራቸው ስር ማድረጋቸው ሱዳን ላይ ተጨማሪ ጉዳት ደረሰ፡፡

የቅኝ ገዢዎቹ ዓባይን በተመለከተ የነበራቸው ፍላጎት ላይ የዐድዋ ድል ቀዝቃዛ ውሃ በመቸለሱ፣ በጉልበት ለመተግበር አስበው የነበረውን ውጥናቸውን በሌላ መንገድ ለማስፈጸም ተገደዱ፡፡ እአአ በ1929 ዓም እና በ1959፣ በእንግሊዝ መሪነት ዓባይን በተመለከት ኢትዮጵያን ያላካተቱ ሁለት ስምምነቶች ተደረጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *