‹‹የመጤ›› እና ‹‹የተወላጅ›› ትርክት የት ያደርሳል?!

ካስመዲ የተባለ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም The Populist Zeitgeist በሚል ርዕስ አንድ ጽሑፍ አቅርቦ ነበር፡፡ ይህ ጽሑፉ የሕዝብን ስሜት በመኮርኮር ዘላቂ ያልሆነ አቋራጭ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለመፈለግ አዝማሚያ (ፖፑሊዝም) አዲስና ያልተንዛዛ ፍች የሚሰጥ ሆኗል፡፡ ምሁሩ፣ በተለይም በሁለት ዕሣቤዎች ላይ ነበር ያተኮረው፡-
ይህ ዓይነቱ ፖለቲካዊ አዝማሚያ በከፍተኛ ደረጃ በስሜት በተቃኘ ዲስኩር የሚገለጽ መሆኑና በዋናነት የመራጮችን ድምፅ ለማግኘት ታሳቢ ተደርገው የሚቀረፁ ‹‹የጥቅመኛ ፖሊሲዎች››ን የሚይዝ በመሆኑ ላይ፣ ለግል ፖለቲካዊ ጥቅም ሲባል የሕዝብን ስሜት መኮርኮር ከዲስኩርና ከጥቅም አነፍናፊነትም በላይ መሆኑን የሚያስረዳው ጽሑፉ፣ አዝማሚያው በደንብ በተብራራ መልኩ የቀረበ ፖለቲካዊ ርእዮተ ዓለም ባይሆንም፣ በጥቂት መሠረታዊ ዕምነቶች ላይ የተመሠረተ ‹‹እርዮተ-ዓለም›› መሆኑን ይገልጻል፡፡

የሕዝብን ስሜት በመኮርኮር ዘለቄታዊነት በሌላቸው ወቅታዊ ትኩሳቶች ላይ የሚያተኩሩ ፖለቲከኞች፣ ማኅበረሰቡን ‹‹ብዙኃኑ ሕዝብ›› እና ‹‹ልሒቃን›› በተባሉ ሁለት ተቃራኒ ምድቦች ከፍለው ነው የሚመለከቱት፡፡ ለተከታዮቻቸውም የሚሰብኩት ‹‹ብዙኃኑ ሕዝብ›› በመሠረቱ መልካም፣ ‹‹ልሒቃን›› ደግሞ በመሠረቱ የነቀዙና ከሕዝቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት የራቁ መሆናቸውን ነው፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ለማስረፅ የሚሞክሩት ሌላኛው ዕሣቤ ደግሞ ፖለቲካ ‹‹የብዙኃኑ ፈቃድ›› ነጸብራቅ መሆን እንዳለበት ነው፡፡
ይህን አዝማሚያ አደገኛ የሚያደርገው ማኅበረሰባዊ ክፍፍሉ የሚመሠረተው በማንነት እንዲሁም በ‹‹ወገን›› እና በ‹‹ጠላት›› መካከል ‹‹አለ›› ተብሎ ከሚታሰበው ግልጽ ልዩነት በሚመነጭ ስሜት ላይ መሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ባለው ፖለቲካዊ አዝማሚያ የውይይት መድረኮች ሁሉ በልሒቃን ቁጥጥር ሥር መሆናቸው ስለሚታመን ድርጊቶች የሚገለጹት በትንኮሳና በዐመፅ ነው፡፡
ለመሆኑ የሕዝብን ስሜት በመኮርኮር ዘለቄታዊነት በሌላቸው ወቅታዊ ትኩሳቶች ላይ የማተኮር ፖለቲካዊ አዝማሚያ መንሥዔዎች ምንድር ናቸው?
• የወጣቶች ሥራ አጥነት የሚፈጥረው ቀቢፀ ተስፋ፣
• በኅብረተሰቡ ውስጥ እየጎላ የሚመጣ የገቢ ልዩነት፣
• መንግሥታዊው ሥርዓት የራሱን አጀንዳና ፍላጎቶች እውን ለማድረግ ከመጣር በቀር የዜጎችን ድምፅ እንደማይሰማ መደምደም፣
• በነባር የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ዕምነት ማጣት፣
• የብዙኃኑን ቀልብ መግዛት የሚችሉ፣ በጣም በቀላሉ የሚሳኩ የሚመስሉ የአቋራጭ መፍትሔዎችን የሚያቀርቡና የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን የሚያራክሱ ወትዋቾች መከሰት ናቸው፡፡

የሕዝብን ስሜት በመኮርኮር ወቅታዊ ትኩሳት የመፍጠር ፖለቲካዊ አዝማሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መንሥዔ ሲሆን በተደጋጋሚ ታዝበናል፡፡ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ዕሣቤዎች በዳበሩባቸው ምዕራብ አውሮፓና ሰሜን አሜሪካ እንኳ ሳይቀር ለናዚ/ ፋሺዝም አስተሳሰብ የቀረበ አደገኛ ዐቋም የሚያንጸባርቁ ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ አሸንፈው ወደ ሥልጣን እየመጡ ናቸው፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች የብዙኃኑን ድጋፍ ለማሰባሰብ የቻሉበት የጸረ ስደተኞች ዐቋም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የሰብዓዊ መብቶችን በማስከበር ረገድ የተመዘገቡ ስኬቶችን እንዳይቀለብስ አሥጊ ሆኗል፡፡

በእኛም ሀገር የበቀሉ አክራሪ ብሔር ተኮር ፖለቲከኞች የሕዝብ ድጋፍ ለማሰባሰብ ከሚጠቀሙባቸው መቀስቀሻዎች አንዱ ‹‹የመጤ›› እና ‹‹የተወላጅ›› ትርክት ነው፡፡
በፖለቲካ ዕውቀታቸው ያልበሰሉ ወጣቶችን በየብሔራቸው በማደራጀት ‹‹ጠላት›› ተደርገው በተሣሉ ወገኖች ላይ ጥቃት እንዲያደርሱ በመቀስቀስ በተለያዩ አካባቢዎች ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ተፈጽመዋል፡፡

መሬት ዋነኛ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ቁጥጥር መሣሪያ በሆነባት፣ ከአጠቃላይ ሕዝቧ ሰማንያ በመቶ ያህሉ የገጠር ነዋሪ በሆነባት እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች ‹‹ከአገር/መሬት ባለቤትነት›› ተለይተው በማይታዩባት ኢትዮጵያ ‹‹የመጤ›› እና ‹‹የተወላጅ›› ትርክት ብሔር ተኮር ገጽታ ተላብሶ ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት፣ ለሚሊዮኖች መፈናቀልና ለንብረት ውድመት ምክንያት ሆኗል፡፡

‹‹ሂውማን ራይትስ ዎች›› እ.ኤ.አ በ2017 ዓ.ም በዓለም ሀገራት ያለውን የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ይፋ ባደረገበት መግለጫ ላይ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ኬኔትሮዝ The Dangerous Rise of Populism በሚል ርዕስ ባቀረበው ጽሑፍ የቀኝ ዘመም ፖለቲካን አደገኛነት ተንትኗል፡፡

የሕዝብን ስሜት በመቀስቀስ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት የሚፈጥሩ ፖሊቲከኞች ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱት እነርሱ ለሚያቀነቅኑት ‹‹የብዙኃን ፈቃድ›› እንቅፋት አድርገው መሆኑን የሚገልጸው ኬኔትሮዝ፣ ሰብዓዊ መብቶች ሰዎች ሁሉ የሚጎናጸፏቸው የመሆናቸውን እውነታ እንደማይቀበሉም ያስረዳል፡፡

‹‹ሰዎች፤ መብቶችን በተመረጠ ሁኔታ ማስከበር ይቻላል በሚል አደገኛ ግምት- ማለትም፣ የራሳቸው መብት እስካልተነካ ድረስ የሌሎች መብት ሊጣስ እንደሚችል በማሰብ ይጽናናሉ፡፡›› የሚለው የሰብዓዊ መብቶች ተከላካዩ፣ ሰብዓዊ መብቶች ግን በባሕርያቸው ሳይነጣጠሉ አንድ ላይ የሚወሰዱ እንጂ እንደ ሆቴል ምግብ ከገበታ ዝርዝር ላይ የሚመረጡ አለመሆናቸውን ያስታውሳል፡፡
ኬኔትሮዝ ትንታኔውን በመቀጠል ‹‹ጎረቤቶችህን አትወድዳቸው ይሆናል፤ ነገር ግን፣ ዛሬ የእነርሱን መብት መሥዋዕት ካደረግህ፤ ነገ አንተም ተመሳሳይ ዕጣ ይደርስብሃል፤ ምክንያቱም፣ መብቶች የተመሠረቱት አንተ እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ለሌሎች ማድረግ እንዳለብህ በሚያሳስብ ብድር የመመለስ ዕሣቤ ላይ ነውና፡፡ የተወሰኑ ወገኖችን መብቶች መጣስ በአሁኑ ሰዓት በስማቸው የመብት ጥሰት እንዲፈጸም ምክንያት ለሆኑ ‹ብዙኃን› የኋላ ኋላ አስፈላጊ የሆኑ መሠረቶችን መናድ ነው፡፡›› ሲል ያስጠነቅቃል፡፡

በደቡብ ምሥራቅ እስያ ጥናት ላይ የተሠማራው ቦንጁዌጎ የፊሊፒንሱ ፕሬዚደንት ዱቴርቴ ‹‹የብዙኃኑን ፈቃድ›› በመፈጸም ሰበብ የሚያደርሷቸውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በተነተነበት ጽሑፍ እንደገለጸው፣ ብዙዎቹ ፖሊቲከኞች ቢያንስ ለይስሙላም ቢሆን በሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ተገዥ መሆናቸውን ይናገራሉ፤ እንደ ዱቴርቴ ዓይነቶቹ ዓምባገነኖች ግን ዋነኛ ባሕርይአዊ መገለጫ በሰብዓዊ መብቶች ተቋማትና ዕሣቤዎች ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ናቸው፡፡

መደምደሚያ
ብዝኃነትን በራሱ ለዓላማቸው መሳካት እንቅፋት አድርገው የሚወስዱት ለጊዜአዊ ጥቅም ሲሉ የሕዝብን ስሜት የሚኮረኩሩ ፖሊቲከኞች ‹‹እንወክለዋለን›› የሚሉትን ወገን ጥቅም በማስከበር ሽፋን ማንኛውንም ዓይነት የዘር አድልዎ ለማስወገድ የተደረገውን ዓለም አቀፍ ስምምነት ከመጣስ ወደ ኋላ አይመለሱም፡፡

የእንዲህ ዓይነቶቹ ፖሊቲከኞች ዲስኩርና ተግባርዋና ማጠንጠኛ የሰብዓዊ መብቶች ዕሤቶች መሠረቶች የሆኑትን ሁሉን አቀፍነት፣ የማይነጣጠሉና የማይገሠሡ የመሆናቸውን እውነታ የሚጻረር ነው፡፡

ሰሞኑን እንዳስተዋልነው፣ ተጨባጭ የፖሊሲ አማራጭ ከማቅረብ ይልቅ ለጊዜአዊ ጥቅም ሲሉ የሕዝብን ስሜት የሚኮረኩሩ ፖሊቲከኞች በሕዝብ መካከል ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች በመቀስቀስ ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ ዐቅም አላቸው፡፡

በአውሮፓና በአሜሪካ ሲሆን እንዳየነው የሕዝብን ስሜት በመቀስቀስ ወቅታዊ ትኩሳት የሚፈጥሩ ፖሊቲከኞች ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ግድ እንደማይሰጣቸው በይፋ እየተናገሩ እንኳ በሰፊ ልዩነት በምርጫ አሸናፊ ሆነው ሥልጣን ይዘዋል፡፡ ይህም የሚያሳየው በዚህ ዘመን ያለው የዴሞክራሲ መንፈስ ከሰብዓዊ መብቶች መርሖዎች እየተነጠለ የመጣ መሆኑን ነው፡፡

በኢትዮጵያም ቢሆን የሕዝብን ስሜት በመኮርኮር ፖለቲካዊ ግባቸውን ለማሳካት የሚሹ ወትዋቾች ‹‹የእኛ አይደለም›› ብለው የሚያስቡትን ወገን ሰብዓዊ መብቶች በመጨፍለቅ ሊያደርሱ የሚችሉትን ጉዳት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየታዘብን ነው፡፡ 2012 ዓ.ም የምርጫ ዘመን እንደ መሆኑ እንዲህ ዓይነቶቹ የፖለቲካ አትራፊዎች በብሔርና ሃይማኖት ተኮር ቅስቀሳቸው አማካይነት አብላጫ ድምፅ አግኝተው ሥልጣን ለመጨበጥ ተዘጋጅተዋል፡፡

ስለሆነም፣ የሰብዓዊ መብቶች ተከላካዮችና ፖለቲከኞች ወደ ችግሩ ሊመሩ የሚችሉ ሥነልቡናዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁናቴዎችን በማጥናት መፍትሔ የሚያመጡ ሥልቶችን በመቀየስ እንዲሁም ሕዝቡን በማንቃት ሊመጣ ያለውን አሰቃቂ አደጋ ማስቀረት ይገባቸዋል፡፡

(ይህ ጽሑፍ ቀደም ሲል በመልዕክተ ኢሰመጉ ላይ የታተመ ነው)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *