SHARE

በበአላት መዳረሻ ወቅት የሚፈፀሙ ወንጀሎችንና ህገ – ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ባከናወነው ኦፕሬሽን ህገ- ወጥ የጦር መሣሪያዎችን እና ሀሰተኛ የብር ኖቶችን ጨምሮ በርካታ የወንጀል ፍሬዎችን በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ፖሊስ ኮሚሽኑ ከሌሎች የፀጥታ አካላት፣ ከክ/ከተማ አስተዳደርና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባከናወነው ኦፕሬሽን የወንጀል ፍሬዎችን ከነተጠርጣዎቹ በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ ይገኛል፡፡

የወንጀልና ትራፊክ አደጋ ምርመራ ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ሐሰን ነጋሽ እንዳስታወቁት ከህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ 11 ሽጉጦች ከ1600 በላይ መሰል የሽጉጥ ጥይቶች እንዲሁም ሀሰተኛ የብር ኖቶች ከማተሚያ ማሽን ጋር በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡

ቅዳሜ ታህሣስ 25/2012 ዓ.ም ከጧቱ 2፡30 አካባቢ በቦሌ ክ/ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ኒያላ ሞተርስ ጀርባ ወንጀል የፈፀሙ 6 አባላት ያሉት አንድ የዘረፋ ቡድን በህብረተሰቡ ትብብር በሰዓታት ልዩነት ተጠርጣሪዎቹን ፖሊስ በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ መርካቶ ሸክላ ተራ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ከበርበሬ ጋር ባዕድ ነገር ቀላቅለው ለመሸጥ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 6 ተጠርጣሪዎች ከነ-ኤግዚቢቱ ሊያዙ መቻላቸውን ም/ኮሚሽነር ሐሰን ነጋሽ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ከተለያዩ ተሽከርካሪዎች ላይ 8 ተጠርጣሪዎች ከሰረቁት 331 ስፖኪዮ፤ የዝናብ መጥረጊያ እና ሌሎች የተሽከርካሪ አካላት፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮች ፣ላፕቶፕ ኮምፒውተር ፣ ቴሌቪዥን ፣ የቤት እና የግንባታ ዕቃዎች እንዲሁም ግራሙ ያልታወቀ አደዛዠ እፅ በተደረገው ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር ከዋሉ የወንጀል ፍሬዎች መካከል ይገኙበታል ብለዋል ም/ኮሚሽነር ሐሰን ነጋሽ ፡፡

በአጠቃላይ ሰሞኑን በተደረገው ኦፕሬሽን 276 ተጠርጣሪዎች በጥናት ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሲሆን ተከሳሾችን በተመለከተ ምርመራው መቀጠሉን ም/ኮሚሽነር ሐሰን ነጋሽ ተናግረው የ2012 ዓመተ ምህረት የገና በአል በሠላም እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበው ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች መልካም በዓል እንዲሆንላቸው በኮሚሽኑ ስም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here