የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመገናኛ ብዙሃን በአግባቡ ሽፋን እየሰጡን አይደለም አለ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትልልቅ ስራዎችን ቢሰራም መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ሽፋን እየሰጣቸው አለመሆኑን የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ ተናገሩ፡፡ አፈ ጉባኤዋ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብረሂም እንደተናገሩት

በአዋሳኝ ቦታ ላይ ያሉ የወረዳዎችና የዞን አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎችን እንዲሁም ወጣቶችን የሚያካትቱ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡ ነገር ግን ለሰፊው ህዝብ እንዲደርስ ሁለት ጊዜ ለመገናኛ ብዙሃን ጥሪ ቢያቀርቡም መረጃውን ለህዝብ ለማድረስ ፈቃደኛ ሆኖ የተገኘ መገናኛ ብዙሃን አልተገኘም፡፡

‹‹ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስራዎችን እንዳትዘግቡ የተባለ ይመስል መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን ሽፋን እየሰጡን አይደለም፡፡ ቀድሞ መግለጫ ቢሰጥም እየተስተናገደ አይደለም፡፡›› ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፤ መገናኛ ብዙሃን የሸሹበት ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነላቸው ጠቁመዋል፡፡

ፌዴሬሽኑ ከሌላ ጊዜው በተሻለ መልኩ ህዝብ ለህዝብ ለማቀራረብ ውይይት ላይ ትኩረቱ አድርጎ እየሰራ መሆኑን አመልክተው፤ በየክልሉ በመሄድ አማራ ክልል ከትግራይና ከአፋር ክልል ጋር ባይወያይም ሌሎች ሁሉንም ክልሎች በማገናኘት የማወያየት ሥራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ የአማራ ክልል ሰዎችም ሲመቻቸው ውይይቱ የሚካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ክልሎች ደግሞ የየራሳቸውን ዞኖችና ወረዳዎች እያገናኙ እያወያዩ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን የመሳሰሉ ሰፋፊ ሥራዎች ቢሰሩም ለሰፊው ህዝብ በማዳረስ በኩል መገናኛ ብዙሃን ሃላፊነታቸውን እየተወጡ አለመሆናቸውንም ነው ያመለከቱት፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *