በየመንገዱ የስልክ ስክሪን ማጠንከሪያ ተብሎ አገልግሎት ላይ እየዋለ ስላለው ፈሳሽ የሚያውቀው ነገር አለመኖሩን የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
By: Date: December 10, 2019 Categories: ኢኮኖሚ Tags:

ናኖ ቴክኖሎጂ ማለት ዘረፈ ብዙ ቴክኖሎጂዎችን በውስጡ የሚይዝ መሆኑን ተገልጿል፡፡ የሞባይል ስልክ ስክሪን ማጠንከሪያ ተብሎ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ፈሳሽ መፈተሽ እንዳለበት የባለስልጣኑ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አወቀ ሺፈራው በተለይ ለኢቲቪ ተናግረዋል።

በፍተሻውም ወቅት በስልክ ገጽ ላይ የሚቀባው ፈሳሽ ጨረራ አለው ወይስ የለውም፤ የጨረራ ይዘቱ ምን ያህል ነው የሚለው ፍተሻ እንደሚደረግበት ገልጸዋል። በፍተሻው ውጤት መሠረት ጨረራ አመንጪ ከሆነ ደግሞ መጠኑ ከዚህ በላይ ከሆነ ጉዳት አለው፣ ከዚህ በታች ከሆነ ደግሞ ጉዳት የለውም የሚለውን በሳይንሳዊ ትንታኔ መሠረት መናገር ይቻላል፤ ይህ ባልታወቀበት ሁኔታ ግን ይህ ነው ብለን መናገር አንችልም በማለት አብራርተዋል።

አያይዘውም፣ በተቋማችን አሠራር አንድ ጨረር አመንጪ ቁስ አካል ወደ አገር ውስጥ ሲገባ አስመጨዎቹ ያመጡትን ነገር ወደ ተቋማችን አምጥተው የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባቸው ሕጉ ያስገድዳል።

በዚህ መሠረት አስመጪዎች ያስገቡትን ምርት ወደ እኛ ሲያመጡ የገባው ቁስ አካል ወይም መሣሪያ ምን ያህል ጨረር እንደሚያመነጭ፣ በምን ዓይነት መንገድ ጥቅም ላይ እንደሚውል፣ ጥቅም ላይ ሲውል መወሰድ ስላለባቸው ጥንቃቄዎች እና አስገዳጅ የቁጥጥር መስፈርቶች መሟላታቸውን አረጋግጠን እንመልሳለን ብለዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ናኖ ቴክኖሎጂ የተባለ ቁስ እንዴት እንደገባ ማን እንዳስገባው ተቋማችን የሚያውቀው ነገር የለም ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ይህ የናኖ ቴክኖሎጂ ተብሎ በየመንገዱ ለስልክ ማጠንከሪያ ተብሎ እየተሸጠ ያለው ፈሳሽ በተቋማችን የቁጥጥር ሥርዓት ውስጥ አላለፈም ሲሉ ተናግረዋል።

ሆኖም ግን የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከያ ባለሥልጣን ከዚህ ጋር ተያይዞ ስለሚከሰት ጉዳት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል በማለት አቶ አወቀ አመልክተዋል።

ከዚህ ባለፈ ግን የጉምሩክ መሥሪያ ቤት ይህ የገባው ቁስ አካል ለምን ዓላማ እንደሚገባ፣ ጉዳት የሚያስከትል ነው አይደለም የሚለውን ጨምሮ የት እና በእነማን መግባት አለበት የሚለውን የሚወስን ተቋም መሆኑ ጠቅሰዋል። በመጨረሻም ጉዳዩን አስመልክቶ ከፖሊስ አካል ወይም ከሸማቾች ጥበቃ የይጣራልን ጥያቄ ከመጣ ለመተባበር ዝግጁ ነን ሲሉ ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *