Press "Enter" to skip to content

በኢትዮጵያስ ደጎልን መሆን የሚጠይቅበት ጊዜ እየመጣ ይሆን? ጋዜጠኛ ፋሲል የኔያለም

ጠ/ሚ አብይ አህመድ በብሄረሰቦች በአል ላይ ተገኝተው ፦ “የኢትዮጵያን ብልጽግናና መጻዒ እጣ ፋንታዋን ለመወሰን ለሚደረግ ማንኛውም መስዋዕትነት ራሳችሁን እንድታዘጋጁ ጥሪ አቀርባለሁ።” ብለዋል።

ለጊዜው የይሆናል ትንተና ውስጥ ሳልገባ፣ የዶ/ር አብይ ጥሪ የመከላከያ ሰራዊቱን ጽናትና ገለልተኝነት የሚፈትን ከፍ ያለ ነገር ከፊታችን እየመጣ መሆኑን የሚጠቁም ይመስለኛል የምትለዋን ብቻ በመናገር ወደ አንድ ጀግና ሰው ታሪክ ላምራ።

ቻርለስ ደጎል። ደጎል ከጎልማሳነቱ ጀምሮ አገሩን ፈረንሳይን ታላቅ የማድረግ ህልም ነበረው። ቻርለስ አገሩ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት በጀርመኖች ብትሸነፈም የአርበኝነት ተጋድሎውን አጠናክሮ በመቀጠሉና ለድል በመብቃቱ፣ ይመኘው የነበረውን ስልጣን በአጋጣሚ ለመጨበጥ ቻለ። ደጎል ፈረንሳይን ታላቅ የማደረግ ህልሙ በቀላሉ እንደማይሳካ መረዳት የቻለው ስልጣን በያዘ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ነው ። አመት ሳይቆይ በፖለቲከኞች የተራራቀ የሃሳብ ልዩነት የተነሳ በፓርላማ ውስጥ በሚፈጠር ሽኩቻ አገሩን መምራት እንዳቃተው ሲረዳ፣ ተጨማሪ ስልጣን እንዲሰጠው ፓርላማውን ጠየቀ። የሚሰማው ሰው ግን አላገኘም። እንዲያውም አምባገነን ለመሆን ይፈልጋል በሚል ዘመቻ ተከፈተበት ። ብዙም ሳይቆይ ተሰፋ ቆርጦ ስልጣኑን በማስረከብ የጡረታ ህይወቱን መምራት ጀመረ። ስልጣን በለቀቀ በ6 አመታት ውስጥ የፈረንሳይ ፖለቲካ እየተበላሸ በመሄዱ ከ 18 ያላነሱ መሪዎች ሲቀያየሩ ተመለከተ፤ አገሩ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመግባትም ጫፍ ላይ መደረሷን ሲመለከትም “አገሬን ማዳን አለብኝ”የሚል የውስጥ ለውስጥ ቅሰቅሳ ጀመረ ።

በእኤአ 1958 አልጀሪያ ውስጥ የነበሩ የፈረንሳይ የጦር መኮንኖች መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ወደ ፓሪስ መግባት ጀመሩ። ፓሪስ ውስጥ በስውር የተደራጁትም ሃይሎች ዝግጅታቸውን ጨርሰው ወደ ቤተመንግስቱ ለማምራት ጥሪ በመጠባበቅ ላይ ናቸው። የወቅቱ ጠ/ሚኒስትር ሌላ ደም መፋሰስ ሊከሰት ይችላል ብለው ስጋት ስለገባቸው ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ወሰኑ ። ደጎልም ተጠራና “የምትፈልገውን ስልጣን ውሰድና አገራችንን ከእልቂት ታደጋት” ተባለ። በእስተርጅና ወደ ስልጣን የመጣው ቻርለስ ወዲያውኑ ፓርላማው እረፍት እንዲወጣ አደረገ። መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ያሰቡትን ወታደሮችንም አስጠነቀቀ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የፖለቲካ ስርዓቱ ከፓርላሜንታዊ ወደ ፕሬዚዳንታዊ ስርዓት እንዲለወጥ የሚያደረግ ህገመንግስት እንዲረቀቀ አስደረገና ህዝበ ውሳኔ ተሰጠበት። እጅግ አብዛኛው ህዝብ አዲሱን ህገ መንግስት ደግፎ ድምጽ ሰጠ። ዛሬም ድረስ ጸንቶ የቆየው 5ኛው ሪፑብሊክም በፈረንሳይ ተመሰረተ። ፈረንሳይ ከድህነትና ከእርስ በርስ ጦርነት ወጥታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከሃያላን አገራት ተርታ ተመደበች። (የቻርለስ የአስተዳደር ዘይቤ ዛሬ ደጎሊዝም በሚል ንድፈ ሃሳብ ይታወቃል። )

ደጎል ጂን ሞኔ (ት) የሚባል በጣም ጎበዝ የሆነ የኢኮኖሚ አማካሪ ነበረው። አንድ ቀን ሞኔት ደጎልን፣ “ስማ ወዳጄ! ፈረንሳይን ታላቅ እናደርጋታለን እያልክ የምትፍኮረው ይህን የደከመ ኢኮኖሚ ይዘህ ነው? በዚህ ድህነት አይደለም ታላቅ አገር ልትመሰርት፣ የአገሪቱን ህልውናዋም ጠብቀህ ማቆየት አትችልም” ብሎ በግልጽ ነገረው። ደጎልም ሞኔትን “ልክ ነህ፣ በል ከአሁን በሁዋላ ኢኮኖሚውን አንተ ምራው፣ እኔ ጣልቃ አልገባህም ” ብሎ ሾመው ። ሞኔት አገሩን ብቻ ሳይሆን መላ አውሮፓን በኢኮኖሚ ያስተሳሰረውን ንደፈ ሃሳብ ይዞ ብቅ አለ። ሞኔት የአውሮፓ ህበረት መስራች አባት የሚባለውም ለዚህ ነው።

ደጎል ለሁሉም ነገር መሰረቱ ስርዓት ( order) ነው ብሎ የሚያምን፤ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን ህይወቱም እንዲሁ በስርዓት የተሞላ፣ ቅንጦትና በገንዘብ የሚገኙ ደስታዎች የማያማልሉት ቆፍጣና ወታደርና ፖለቲከኛ ነበር።

በኢትዮጵያስ ደጎልን መሆን የሚጠይቅበት ጊዜ እየመጣ ይሆን?

ልብ ያለው ልብ ይበል!

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

//glugreez.com/4/4057774