Press "Enter" to skip to content

የጌዲዮ ዞን ፌደራል መንግስት በክልልነት እንዲያዋቅረው ጠየቀ።

የጌድዮ ዞን አዋሳኝ የሆነው የሲዳማ ዞን በህዝበ ውሳኔ ወደ ከልልነት ማደጉን ተከትሎ ከደቡብ ክልል ጋር ያለው የየብስ ግንኙነት ይቋረጣል። በጌዲዮ ዞን ምክር ቤት የህግ ፍትህ እና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ

ሰብሳቢ አቶ ሽፈራው ቦጋለ ለኢትዮ ኤፍ ኤም እንዳሉት ሲዳማ ዞን ከደቡብ ክልል እራሱን ችሎ በክልልነት ደረጃ ሲወጣ የጌዲዮ ዞን ከየትናውም የደቡብ ክልል ዞኖች ጋር በጂኦግራፊ አቀማመጥ የማይገናኝ መሆኑን ተከትሎ የአስተዳደር ሁኔታው አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል ብለዋል፡፡

በ56 ብሔር ብሔረሰቦች የተዋቀረው የደቡብ ክልል ባሳለፍነው ሳምንት የሲዳማ ዞን በህዝበ ውሳኔ ወደ ክልልነት ማደግ የሚያስችል ውሳኔ ተላልፏል። በመሆኑም ቀሪዎቹ 55 ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ የአስተዳደር መዋቅር ይቀጥላሉ የሚል ጭምጭምታ መሰማቱን ተከትሎ የጌድዮ ዞን ከተቀረው የደቡብ ክልል ዞኖች ጋር ስለማይዋሰን በክልልነት እንዲዋቀር ተጠይቋል።

እንደ አቶ ሽፈራው ገለጻ የህዝቡ የክልልነት ጥያቄ የመነጨው ሲዳማ በክልልነት መውጣቱን ተከትሎ ዞኑ ከደቡብ ክልል ጋር በመልክዓ ምድር በቀጥታ ስለማይገናኝ ብቻም ሳይሆን አስቀድሞ ሲደርስበት የነበረው ኢ-ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል እና የመልካም አስተዳደር እጦት ተጋላጭ እሆናለሁ የሚል ስጋት ስላለበት ነው፡፡

በመሆኑም የዞኑ ምክር ቤቱ ባለፈው ስብሰባው ጉዳዩን በተመለከተ መክሮበት እንደነበር አቶ ሽፈራው አስታውሰዋል፡፡ እንደ ጌዲዮ ዞን በሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኘው የይርጋ ጨፌ ቡና መገኛ እንደመሆኑ ለአመታት ከዚህ ሀብት ተጠቃሚ ሳይሆን ቀርቷልም ብለዋል።

ከደቡብ ክልል ጋር በመነጋገር ጌድዮ ዞን ከ55ቱ አንድ ሆኖ ወይም ለብቻው እንደ ክልል ይዋቀራል በሚለው ጉዳይ ላይ ህዝቡን በማወያየት ከሁለቱ በአንዱ ላይ እንዲስማማ እንደሚደረግም አቶ ሽፈራው ገልጸዋል።

ይህም ሲሆን የዞኑን ህዝብ ፍላጎት በመጨፍለቅ ሳይሆን ዘመኑ በሚፈቅደው ዲሞክራሲያዊ መንገድ ጥያቄው እንዲመለስ ይደረጋል ብለዋል አቶ ሽፈራው፡፡ ጉዳዩ የፖለቲካ በመሆኑ የዞኑ አመራር ከህዝቡ እና ከክልሉ ጋር እየተወያዩ መሆኑን የገለጹት አቶ ሽፈራው ውይይቱ ግን በበቂ ሁኔታ እየተካሄደ አይደለም ብለዋል።

የቀድሞ የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ደምሴ በበኩላቸው የጌዲዮ ዞን ከሲዳማ ክልልነት ምላሽ በኋላ የዞኑ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ከሌሎቹ የክልሉ ዞኖች ጋር በጋራ ለመቀጠል ያስቸግረዋል ብለዋል፡፡

የዞኑ ተፈጥሯዊ አቀማመጥ በራሱ ለክልል እንሁን ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ በመሆኑ ከደቡብ ክልል ተለይተን በቀጥታ ተጠሪነቱ ለፌደራሉ መንግስት እንዲሆን እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ የደቡብ ክልል መንግስት አስተያየትን ለማካተት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *