ከተሞቹ ስምምነታቸውን በአዲስ መልክ ለማደስ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባና ዋሽንግተን ዲሲ የእትማማች ከተማነት ስምምነታቸውን በአዲስ መልክ ለማደስ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ፡፡ ስምምነቱን ኢ/ር ታከለ ኡማና የዋሽንግተን ዲሲ ከንቲባ ሙሪየል ቦውሰር የተፈራረሙት ሲሆን ሁለቱ ከተሞች በኢኮኖሚ፣ ጤና፣ የባህል ልውውጥና አረንጓዴ ልማት ላይ በጋራ ለመስራት ተሰማምተዋል፡፡

በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ መረጃ ለመለዋወጥና በጋራ የሚሰሩ የልማት ስራዎች ላይ ለመሳተፍ ተስማምተዋል፡፡ ሀገራዊ የቢዝነስ ሀሳቦች ማደግ በሚችሉበት ዙሪያ በከተማ አስተዳደርና በንግድ ዘርፍ ማህበራት ደረጃ በጋራ መስራትም በስምምነቱ ውስጥ ተካቷል፡፡

በተለያዩ የፈጠራ ሀሳቦችና የቴክኖሎጂ እድገቶች ላይ በጋራ መስራት፤ የፈጠራ ሀሳቦች እንዲተገበሩ ልምድን መለዋወጥም የእህትማማች ከተማነት ስምምነት ውስጥ ተጠቅሷል፡፡

በጤና ዘርፍ ደግሞ ለዘርፉ ማደግ አስተዋጽኦ ካላቸው የጤና ፖሊሲዎች ጀምሮ በሽታን መከላከል ላይ በሚስሩ ስራዎች ዙሪያ በጋራ ለመስራት ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የሁለቱ ከተማ ነዋሪዎች ያሏቸው ባህላዊ እሴቶችን መለዋወጥና እንዲያድጉ መደጋገፍም በስምምነቱ የተካተተ ነው፡፡

በሁለቱ ከተማዎች ላይ የሚሰሩ የአረንጓዴ ፕሮጀክቶች ላይ ልምድ መለዋወጥ፣ በትራንፖርቴሽንና በኮንሽትራክሽን ዘርፉ ላይ የመፍትሄ ሀሳቦችን መለዋወጥና ድጋፍ ማድረግ በአዲስ አበባና በዋሽንግተን ዲሲ መካከል የእህትማማች ከተማነት ስምምነቱን እንደ አዲስ ለማደስ በተፈረመው ስምምነት ላይ የተካተተ ነው፡፡

በቀጣይም ከተለያዩ መንግስታዊ ተቋማትና ነዋሪዎች የተካተቱበት የስምምነቱን አፈጻጸም የሚከታተል ኮሚቴ በሁለቱም በኩል እንደሚቋቋም ከከንቲባ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *