“በሱሉልታ ፖሊስ መፅሐፎቼ ታግተውብኛል” የ27 ዓመት መፅሐፍ ደራሲ ሰብስቤ ሃሰን

የ27 ዓመት የግጥም መድበል ደራሲ ሰብስቤ ሃሰን መፅሐፍቱን ለሥርጭት በሚያጓጉዝበት ጊዜ በሱሉልታ ከተማ ፖሊስ እንደታገቱበት ለቢቢሲ ገለፀ። እርሱ እንደሚለው መጽሐፉ ከታገተ 1 ወር ከ10 ቀን አካባቢ ይሆነዋል።

“መጽሃፉ የመጀመሪያዬ ስለነበር በአካባቢው የሚያውቁኝ ሰዎች ይገዙኛል ብዬ አስጭኜ እየወሰድኩ ነበር” የሚለው ደራሲው፤ ከታተመበት አዲስ አበባ ወደ ሌላ ስፍራ በመጓጓዝ ላይ ሳለ ሱሉልታ ላይ እንደታገተ ይናገራል።

መፅሐፎቹ ብቻ ሳይሆን የጫኑት ሹፌርና ረዳቱ በፖሊስ መታሰራቸውንና መጽሃፉም መታገቱን ከ8 ቀናት በኋላ መስማቱን ያስረዳል፤ በወቅቱ መጽሐፉን ሌላ ዕቃ ከጫነ መኪና ጋር ልኮ እርሱ በሌላ መኪና ለመድረስ ተሳፍሮ እንደነበር በማስታወስ።

በአዲስ አበባ ማንኩሳ ማተሚያ ቤት የታተመው ይሄው ’27 ዓመት’ የሚል ርዕስ ያለው መፅሐፍ የታገተው በዋናነት የፖለቲካ ይዘት ሊኖረው ስለሚችል ይገምገም በማለት እንደሆነ ይናገራል።

እንደ ሰብስቤ ከሆነ በአጠቃላይ 2 ሺህ ቅጂ መጽሐፍትን ያሳተመ ሲሆን ወደ አካባቢው ለማጓጓዝ ጭኖት የነበረው በቁጥር 800 ኮፒ ነው። “መጽሐፌ መታገቱን እንደሰማሁ የአዕምሮ ንብረት ባለቤትነት ማስረጃ ይዤ ሄጄ ባሳያቸውም፤ አንተን አንፈልግህም ስንፈልግህ ትመጣለህ በማለትና መጽሐፉ ግምገማ ላይ መሆኑን ገልጸው አሰናበቱኝ” ይላል።
መጽሐፉ ከመታተሙ በፊት በደቡብ ወሎ ባህልና ቱሪዝም አስገምግሜና ‘ይታተምለት’ የሚል የትብብር ደብዳቤም አስጽፌ ነው ያሳተምኩት የሚለው ደራሲው፤ መጽሐፉ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያጠነጥን ለቢቢሲ ገልጿል።

ይሄው ’27 ዓመት’ የተሰኘው መፅሐፍ 152 ገጽ ሲኖረው ከ93 በላይ ግጥሞችን ያካተተ ነው። ዳራሲው የሱሉልታ ፖሊስ የሰጠውን ምላሽ ይዞ የአዲስ አበባ አዴፓ ቢሮ በመሄድ ማመልከቱን፤ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም አቤት ማለቱንና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወደ ኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ እንደላከው አመልክቷል።

ሰብስቤ ሃሰን አክሎም “የኦሮሚያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በአግባቡ አስተናግዶ ጉዳዩን ለያዘችው ፖሊስ ደውሎ መጽሐፉ እንዲሰጠኝ ቢያዛትም የተለያየ ምክንያት እየደረደረችና መጽሐፉ ተገምግሞ አላለቀም በማለት ሳትፈቅድ ቀረች” ይላል።

ጉዳዩን ለያዘችው ፖሊስም መጽሐፍቱ የእሱ መሆናቸውን ባሳየበት ወቅትም “መረጃው እንደምትጽፍ እንጂ መጽሐፉ የአንተ መሆኑን አይገልጽም” የሚል ምላሽ እንደሰጠችው በመግለፅ መፍትሔ ሊያገኝ እንዳልቻለ ቅሬታውን ያሰማል።

እንደ ሰብስቤ ከሆነ የመኪናው አሽከርካሪና ረዳቱም ሌላ ምርመራ ስላለባቸው በሚል እስካሁን እንደታሰሩ ናቸው። ፍርድ ቤት ሲሄዱም የሚሰጣቸው ምክንያት መጽሐፉ ተገምግሞ አላለቀም የሚል ነው ሲል ያክላል።

ከጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ጋር በነበረው ንግግር መጽሐፉን እንደሚያስለቅቁለት ቃል ቢገቡለትም፤ ይሄው ሳይለቀቅ ከ15 ቀናት በላይ መሆኑን ይናገራል። እስካሁን የሚሰጠው መልስ “ምርመራው አላለቀም” የሚል እንደሆነ የሚናገረው ሰብስቤ “ይሁን ከተባለስ ፖሊስ መጽሐፍ ይገመግማል ወይ?” ሲልም ይጠይቃል።

መፅሐፉን ለማሳተም እና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ100 ሺህ ብር በላይ አውጥቶበታል። ስለ ጉዳዩ ለማጣራት የደወልንላቸው የሱሉልታ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ፅ/ቤት የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ኩምሳ ደገፉ እረፍት ላይ መቆየታቸው ገልፀው ስለጉዳዩ ማጣራት እንዳለባቸው ገልፀውልናል።

ወደ ሱሉልታ ከተማ አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊም ወይንሸት ግርማም እንዲሁ ሞክረን ነበር፤ እርሳቸውም ከኢትዮጵያ ውጪ ለሥልጠና ሄደው ከተመለሱ ገና ሦስት ቀናት መሆናቸውን ጠቅሰው ሌላ ቀን እንድንደውልላቸው ነግረውናል። ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንም መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም። ቢቢሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *