የአንበጣ መንጋ በምስራቅ ሀረርጌ ዞን 14ሺህ ሔክታር መሬት ላይ ጉዳት አድርሷል ተባለ
By: Date: November 7, 2019 Categories: ዜና Tags:

በምስራቅ ሀረርጌ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ 14 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚገኝ እጽዋት ላይ ጉዳት ማድረሱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር 26ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎች ፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የመከላከል ስራ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የሰብልና አዝዕርት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ዘለቀ አብዲሳ እንደተናገሩት የአንበጣው መንጋ በዞኑ በ7 ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 57 ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ተከስቷል።

“በዞኑ ኮምቦልቻ፣ጃርሶ፣ቀርሳ፣ሜታ፣ጎሮጉቱ፣ጭናክሰንና ደደር ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ 14ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የሚገኙ ሰብል፣ግጦሽ፣ደን፣ሳርና ሌሎች እጽዋቶች ላይ ጉዳት አስከትሏል”ብለዋል።

ችግሩን ለመቆጣጠርም 26ሺህ የሚጠጉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከተሳተፉበት ባህላዊ የመከላከል ስራ በተጨማሪ ስርጭቱ ከፍተኛ በሆነበት 398 ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ ኢሲ 97 ፐርሰንት 97%/ የተባለውን 365 ሊትር ኬሚካል በአውሮፕላንና በተሽከርካሪ የመርጨት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅትም የአንበጣው መንጋ ከተከሰተባቸው ሰባት ወረዳዎች መካከል ኮምቦልቻ፣ጃርሶና ጭናክሰን ወረዳዎችን ነጻ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፈው የመኽር ወቅት ከፍተኛ የሆነ ዝናብ በመጣሉ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ተገምቶ እንደነበረ የገለጹት በቢሮው የአዝዕርት ልማት ጥበቃ የድህረ ምርት አያያዝ ባለሞያ አቶ አሸብር ሞላ አንበጣው ሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል።

ችግሩን በመረዳት ህብረተሰቡንና ተማሪዎችን በማደራጀት የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብና አርሶ አደሩን በማደራጀት በባህላዊ መንገድ የመከላከሉ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ገልጸው ይህ ተግባር ቀጣይነት እንደሚኖረው ተናግረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *