Press "Enter" to skip to content

የግብፅ ከበባ እና ኢትዮጵያ

ከ80 በመቶ በላይ ለዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ናይል ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ ወንዟን በሚገባ እንዳትጠቀም ግብጽ ከመቶ ዓመታት በፊት አንስቶ የተለያዩ የማዳከሚያ ስልቶችን ስትጠቀም ቆይታለች።

የማዳከሚያ ስልቶቹ በቀጥታ ጦር አዝምቶ ለመደብደብ ከመሞከር አንስቶ አስከ ረቂቅና ውስብስብ ሴራዎችን እስከመፈጸም ይደርሳል። ኢትዮጵያ ከስምንት ዓመት በፊት የህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመሯን ተከትሎ ግብጽ በስውርና በግልጽ የተለያዩ ጫናዎችን በማሳረፍ ላይ ትግኛለች።

ለአብነት ያህልም ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጋር የተለየ ግንኙነት በመመስረት በዲፕሎማሲ ስም የጦር ቀጠና ለመገንባት ጥረቶችን በማድረግ ላይ ትገኛለች። ከሁለት ዓመት በፊት በቀይ ባህር ወደቦች ላይ በተለይም በአሰብና በጅቡቲ ወደቦች ላይ ወታደራዊ ማዕከሎችን ለመገንባት ከአገራቱ ጋር ስምምነት ፈጽማለች።

ኢትዮጵያ ለገቢ ወጪ ንግዷ ማሳለጫ ከኬንያ፣ሱዳን፣ኤርትራ ሶማሊያና ሌሎች አገራት ጋር ስምምነት መፈጸሟ ይታወቃል። ስምምነቱን ተከትሎ ከዚህ በፊት በብቸኝነት የወደብ አገልግሎት ስትሰጥ የቆየችው ጅቡቲ ኩርፊያ ላይ ትገኛለች።

የኩርፊያውን አጋጣሚ ለመጠቀም ጊዜ ያልፈጀባት ግብጽ በጅቡቲ የሎጅስቲክስ ማዕከል ለመገንባት ከጅቡቲ መንግስት ጋር ተስማምታለች። በኢትዮጵያ የውሰጥ ፖለቲካና ቅሬኔዎችን ማስፋት የሚያስችሉ የተለያዩ የፖለቲካ ሴራዎች ማካሄድ እንዳለ ሆኖ ከደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ ጋር አዲስ የማዳከሚያ ስልቶች መንደፏን የተለያዩ ዘገባዎች በመውጣት ላይ ናቸው።

የግብጽ ለኢትዮጵያ ሁነኛ አጋር የሚባሉት ሱዳን፣ደቡብ ሱዳን፣ሶማሊያና ዩጋንዳን ወደራሷ ለመጠቅለል ከባድ ፍልሚያ ላይ ትገኛለች። ኢትዮጵያ በደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ላይ ባላት ተጽዕኖ ምክንያት ደስተኛ ያልሆነችው ዩጋንዳ ከግብጽ ጋር የመስራት ፍላጎት እንዳላት ፕሬዘዳንት ዮሪ ሙሴቪኒ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል።

ዩጋንዳ ከ10 ዓመት በፊት ግብጽና ሱዳን ረግጠው የወጡበትን የናይል ተፋሰስ አገራት ማዕቀፍን በማዘጋጀት እና የተፋሰሱ አባል አገራት ወደ ስምምነት እንዲመጡ ያስቻለውን የኢንቴቤ ስምምነት እንዳይተገበር ከግብጽ ጋር የማበር አዝማሚያዎች በመታየት ላይ ናው።

ለደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደራዊ ድጋፍ አደርጋለሁ በሚል ሰበብም ግብጽ ወደ ጁባ አይኗን ከጣለች ሰነባብታለች። ሰሞንኛው የደቡብ ሱዳን፣ የግብፅና የኡጋንዳ መሪዎች ኢትዮጵያ የታላቁን የህዳሴ ግድብ ሰርታ እንዳታጠናቅቅ ሴራዎችን እየጎነጎኑ መሆኑ የብዙ ኢትዮጵያዊያንን ትኩረት ስቧል።

ጄምስ ሞይስስ የሚል የሽፋን ስም የሚጠቀም የቀድሞ የኡጋንዳ ሰላይ ለሪፖርተሬ ከሰጠው ሰነድ አገኘሁ ብሎ የደቡብ ሱዳኑ የዜና ወኪል ዘግቧል፡፡ 3 ገፅ በሚሆነው ሰነድ ይሄ የኡጋንዳ የውጪ ጸጥታ ድርጅት (ESO) ይሰራ የነበረ ሰላይ ግብፅ፣ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ሰፊ የተባለ ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ ዘመቻ አሲረውባታል ብሏል፡፡

ከዶክመንቱ የተገኘው መረጃ ሶስቱ ሃገራት በምስራቅ አፍሪካ ላይ ያላቸውን ማንኛውንም ፍላጎት ለማሳካት በቅንጅትና በትብብር እየሰሩ እንደሆነም ያሳያል፡፡ የቀድሞው የኡጋንዳ ሰላይ እንዲህ ይላል፡- “በቀጠናው ሀገሬ ኡጋንዳ ቁጥር አንድ የግብፅ ወዳጅ የሆነችበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ አንዲት ሉአላዊ ሀገርን ወዳጅ ማድረግ ምንም ችግር የለውም፤ ግን ሌሎች ሀገራት ላይ ጉዳት ለማድረስ ወዳጅ መሆን በደንብ ችግር አለው” ብሏል፡፡

ሰላዩ ጄምስ “ለዚህ ነው ይሄንን መረጃ በሰው በኩል ካምፓላ ላይ አግኝቼ ለደቡብ ሱዳን የዜና ወኪል ጋዜጠኛ ልሰጥ የቻልኩት” ሲል ተናግሯል፡፡ የግብፁ ፕሬዝዳነት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ፣ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እና የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ወደፊት እንዳይራመድ ኢትዮጵያ ላይ እያሴሩ ነው የሚለው የቀድሞ የኡጋንዳ ሰላይ “እኔ ለብዙ አመታት ለኡጋንዳ ሰላይ ሆኜ አገልግያለሁ

አብዛኛዎቹ ተልዕኮዎቼ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ ላይ ነበሩ፤ ስለ ጉዳዩ ብዙ አውቃለሁ እንዲህ አይነት ነገር ከምስራቅ አፍሪካ ተልእኮዎቼ በፊት ገጥሞኝ አያውቅም” ሲል ዘርዝሯል በሰነዱ ላይ፡፡

ይህ የቀድሞ ሰላይ በራስ ወዳድነት የተነዱ፣ ከራሳቸው ጥቅም ሌላ የሌላው ሃገር ጉዳት በፍፁም የማያስጨንቃቸው ሲል ይከሳቸዋል ሶስቱን ሀገራት፡፡ “ሶስቱም ሀገራት የራሳቸው ፍላጎት አላቸው የሚለው ይህ ሰላይ አልሲሲ ሀገራቸው ናይልን እንደተቆጣጠረች እንድትቆይ ይፈልጋሉ፣ኡጋንዳ ደግሞ በግብፅ ርዳታ ሳልቫ ኪርን በስልጣን ማቆየት ትፈልጋለች፣ ሳልቫ ኪር ደግሞ የወደፊት ዕጣ ፈንታቸው በኡጋንዳው መሪ ሙሴቬኒ ላይ የተመሰረተ ነው” ሲል ሰላዩ ጄምስ ተናግሯል፡፡

በዶክመንቱ ላይ የቀድሞው ሰላይ ጄምስ ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትጨርስ የሚያስችሉ በሶስቱ ሀገራት የተቀረፁ ዘዴዎችን አጋልጧል፡፡ ከነዚህ የሃገራቱ ሴራዎች መካከል ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት የምትገባ ከሆነ ደቡብ ሱዳንና ኡጋንዳ ግብፅን ሊያግዟት አቅደዋል፡፡

ግብፅንም ድብቅ መስመሮችን በመጠቀም ለደቡብ ሱዳን ጦር መሳርያዎችን ትልካለች ሲል ይከሳል፡፡ አል ሲሲ ሁሌም ለሳልቫኪር በ2 አይነት መንገድ ጦር መሳርያ ያደርሳሉ፤ አንደኛው በግብርና ውጤቶችና በመድሃኒቶች አስመስሎ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ኡጋንዳን እንደ አቀባይ በማድረግ ነው ተብሏል፡፡

ጄምስ ሞይስ ከዚህ ቀደምም እንደ አውሮፓውያኑ በሐምሌ 2013 በኡጋንዳና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን ሚስጥር በማጋለጥ በዚያው አመት በ ታህሳስ 2013 የርስ በርስ ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡

ኢትይጵይ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የዲፕሎማሲያዊ የበላይነት እንዳይወሰድባት የራሷን ስራ በመስራት ላይ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነቢያት ጌታቸው ለኢትዮ ኤፍ ኤም መናገራቸው ይታወሳል።

ግብጽም በጅቡቲ ወደብ ላይ ልትገነባ ስላሰበችው የሎጅስቲክስ ማዕከል ጉዳይ በቀርበት እየተከታተሉት እንደሆነም መናገራቸው አይዘነጋም። ግብጽ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ጫና ወስት በመክተት ወደራሷ ፍላጎት ለመጠምዘዝ እጅግ ውስብስብ ስልቶችን በመከተል ላይ ትገኛለች።

ኢትዮጵያ፣ግብጽና ሱዳን በህዳሴው ግድብ ዙሪያ በአሜሪካ አደራዳሪነት በዋሸንግተን የሚያደርጉት የሶሰትዮሽ ውይይት ዛሬ እንደሚጀመር የሚጠበቅ ሲሆን የሶስቱ አገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ሰፍራው አቀንተዋል።

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *