በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የሰደድ እሳት አደጋ ተከሰተ፤

በትናንትናው እለት ማምሻ ገደማ በቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ የጀመረው የሰደድ እሳት አደጋ ዛሬም ድረስ ቀጥሎ በግምት ወደ 1500 ሄክታር ገደማ ጥፋት ማድረሱን የፓርኩ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በትግራይ ክልል በሁመራ ከተማ አቅራቢያ ከኤርትራው ብሔራዊ የዝሆኖች ጥበቃ ስፍራ የሚዋሰነው የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ በህገ-ወጦች ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በተገመተ የእሳት አደጋ ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰበት መሆኑን የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዘነበ ገልጠዋል።

የእሳት አደጋው በፓርኩ በወራውራ፣ ጠበቆ፣ ኮርቸሊት እና ሰሊንጎቦ ቀጠናዎች መከሰቱን ሰምተናል። ዛሬ ቀኑን ሙሉ እሳቱ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቀነስ በጥበቃ ሰራተኞች ለመቆጣጠር መሞከሩን የገለጡት ኃላፊው መቆጣጠር አለመቻሉን ጠቁመው ነገ የአካባቢውን ነዋሪዎች በማሳተፍ እሳቱን ለመቆጣጠር መታቀዱን ነግረውናል።

ኃላፊውም ጉዳዮን አስመልክቶ የሚመለከታቸው አካላት በፓርኩ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ መረባረብ እንደሚኖርባቸው ጠቁመው ነገ ለሚደረገው እሳት የማጥፋት ርብርብም በስፍራው ያሉ አካላት ሁሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። የቃፍታ ሽራሮ ብሔራዊ ፓርክ በኢትዮጵያ ከሚገኙ ዘጠኝ የዝሆን መዳረሻዎች ውስጥ አንዱ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *