በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት የተገነባው ትምህርት ቤት ለአገልግሎት በቃ


በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በጎንደር ከተማ በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የሎዛ ብርሃን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከነገ በስቲያ እንደሚመረቅ የከተማ አስተዳደሩ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ አማረ መስፍን ለኢዜአ እንደተናገሩት በትምህርት ቤቱ ምረቃ ላይ ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸውን ጨምሮ የፌዴራልና የክልል የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም የከተማው ነዋሪዎችና አመራሮች ተሳታፊ ይሆናሉ።

ለትምህርት ቤቱ በመጀመሪያው ምእራፍ ተገንብተው የተጠናቀቁ 14 የመማሪያ ክፍሎች ከ300 በላይ የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን በዘንድሮ ትምህርት ዘመን ተቀብለው ማስተማር ጀምረዋል።

ትምህርት ቤቱ ቤተ-መጻህፍትና ቤተ-ሙከራ እንዲሁም የአስተዳዳር ህንጻዎች የተሟሉለት ሲሆን ርዕሰ-መምህርና መምህራን ተመድበውለት የማስተማር ስራውን እንዲጀምር መደረጉንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የትምህርት ግብአቶችን የማሟላት ስራ የተከናወነ ሲሆን በአካባቢው ከሚገኙ አምስት የገጠር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወደ 9ኛ ክፍል ያለፉ ተማሪዎችንም ትምህርት ቤቱ ተቀብሎ ማስተናገዱን ተናግረዋል።

“በሁለተኛው ምእራፍ የተጀመሩ 14 የመማሪያ ክፍሎችም በመጠናቀቅ ላይ ናቸው” ያሉት ሃላፊው “በቀጣዩ አመት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር ይጀምራል” ብለዋል።

“ትምህርት ቤቱን በሂደት እስከ 12ኛ ክፍል ለማሳደግ ታቅዷል” ያሉት ሃላፊው ለውስጥ ድርጅት ማሟያ የሚስፈልገውን 20 ሚሊዮን ብር በከተማ አስተዳዳሩና በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማሟላት መታሰቡንም አስረድተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለትምህር ቤቱ ግንባታ የዋለውን ከስድስት ሄክታር በላይ ቦታ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ለተነሺዎች የካሳ ክፍያ መፈጸሙንም ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ዓመት ግንባታው ተጀምሮ ባጠረ ጊዜ የተጠናቀቀው ይህ ትምህርት ቤት የከተማውን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት ከፍ እንደሚያደርገው ይጠበቃል።


yeahun

0 Comments

Your email address will not be published. Required fields are marked *

0Shares