Press "Enter" to skip to content

የአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት የመጀመሪያዎቹ አዳሪ ተማሪዎች የወለጋ ልጆች የነበሩ ስለመሆኑ ያውቃሉን?

እኔ አማኑኤል አብርሐም መጋቢት 8 ቀን 1905 ዓ.ም በወለጋ ክሐገር በግምቢ አውራጃ በቦጂ ወረዳ፣ በባቦ ቀበሌ በንቲ አደሬ በተባለ ስፍራ በአያቴ ማልሞ ቤት ተወለድኩ፡፡ አባቴ አብርሃም ታቶ ጉርሙ ሲሆኑ እናቴ ደግሞ ቀናቱ ማልሞ ገመ ይባላሉ፡፡

12 አመት ከመንፈቅ ሲሆነኝ ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ የወለጋው ገዢ ደጃዝማች ገብረ ማርያም (ኩማሳ ሞረዳ) በ1915 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ሲያርፉ ልጃቸው ደጃዝማች ሀብተ ማርያም ተኳቸው፡፡ ደጃ ገብረ ማርያም ከመሞታቸው በፊት በጊቢያቸው አካባቢ አንድ ትቤት ከፍተው በአማርኛና በፈረንሳይኛ ትት ይሰጥበት ነበር፡፡

በዚህ ትቤት 6 ወር ያህል እንግሊዝኛ ፊደል ከቆጠርኩ በኋላ በ1918 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትቤት የመሄድ መልካም እድል አጋጠመኝ፡፡ ልዑል ራስ ተፈሪ መኮንን አዲስ አበባ ላይ ተፈሪ መኮንን የተሰኘ ዘመናዊ ትቤት አሰርተው ሚያዝያ 17 ቀን 1917 ዓ.ም ተመረቀ፡፡

አላማቸው ከመላ ኢትዮጵያ ወጣቶችን በማሰባሰብ በዘመናዊ ትት እንዲሳተፉ ማድረግ ስለነበር ደጃ ሀብተ ማርያምም የወለጋን ልጆች ወደ አዲስ አበባ ለትት እንዲልኩ ታዘዙ፡፡

እሳቸውም የመኳንንቶቻቸውን የቅርብ ዘመዶቻቸውንና የአሽከሮቻቸውን 23 ልጆች መርጠው ወደ አዲስ አበባ እንዲላኩ ወሰኑ፡፡ የተመረጡት ልጆች በ1918 ዓ.ም ከመስቀል በኋላ በፊታውራሪ ቀነአ ወንድም በፊታውራሪ አባ ጉርሙ ኃላፊነት በከብትና በእግር ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ጀመሩ፡፡ በጥቅምት ወር 1918 ዓም አዲስ አበባ ደርሰን ጉለሌ ደጃሀብተ ማርያም ጊቢ ሰፈርን፡፡

በአአ የደጃሀብተ ማርያም ወኪል የነበሩት ፊታ ኪዳነ ማርያም ወደ አልጋ ወራሽ ጊቢ ሄደው የወለጋ ልጆችን መምጣት በመናገራቸው ጥቅምት 9 ቀን 1918 ዓ.ም ከሰአት በኋላ አልጋ ወራሽ ጊቢ ሄድን፡፡ በላይኛው ጊቢ ፊት በር ተሰልፈን ፈረንሳይኛ ለጀመሩ አረንጓዴ እንግሊዝኛ ለጀመሩ ቢጫ አማርኛ ለጀመሩ ቀይ ሪቫን ተሰጥቶን በ3 ተከፍለን አልጋ ወራሽን ስንጠብቅ በአጀብ መጡ፡፡

አልጋ ወራሽም ከአገራችን ወጣን፣ ከቤተሰብ ተለየን በማለት ሀሳብ አይግባችሁ፡፡ በሚቻለን ሁሉ እናት አባት ሆነን እንጠብቃችኋለን የሚል አበረታች ንግግር አደረጉልን፡፡ በማግስቱ ወደ ተፈሪ መኮንን ትቤት ሄደን፣ አስተዳዳሪው ሐኪም ወርቅነህ በአዳሪ ተማሪነት ተቀበሉን፡፡ የወለጋ ልጆች የመጀመሪያዎች አዳሪ ተማሪዎች የመሆን እድል አገኘን፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የአአ እና የዳር አገር ሌሎች ተማሪዎች ተቀላቀሉን፡፡

በመጀመሪያ ጊዜ ምግቡ በሙሉ በአልጋ ወራሽ ጊቢ እየተሰናዳ ይላክልን ነበር፡፡ ስኳር ብለን የሰየምነው ከረሜላና ጣፋጭ ምግብ ለወለጋ ልጆች እየተባለ በልዑል ራስ ተፈሪ ትዕዛዝ በየጊዜው ይመጣልን ነበር፡፡ የአዳሪ ተማሪዎች ቁጥር እየበዛ ሲመጣ ማዕድ ቤቶች ተሰርተውና አስተዳዳሪዎች ተቀጥረው ምግባችን በትቤቱ ምድር ቤት መዘጋጀት ጀመረ፡፡

በየሳምንቱ ሐሙስ የአልጋ ወራሽ ሚስት እሜቴ ወሮ መነን እንጀራ ወጥና የማር ብርዝ ይዘው እየመጡ ባንዱ ገበታ ተቀምጠው ግብር ያበሉን ነበር፡፡ ልዑል አልጋ ወራሽ ገበታ ላይ እንዳለን እየመጡ በመካከላችን በመዘዋወር፣ አንዳንድ ልጆችን በማነጋገር ያበረታቱን ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ሁለቱም ልዑላን እንደ አባትና እንደ እናት እየተንከባከቡን፣ በአለምና በደስታ እንማር ጀመር፡፡

አማኑኤል አብርሃም የሕይወቴ ትዝታ አአዩ ፕሬስ 1992 ዓ.ም ገጽ 1 10

የፎቶ መግለጫ፣ በምስሉ ላይ የሚታዩት በ1915 ዓ.ም የሞቱት አባታቸውን ደጃኩምሳ ሞረዳን በመተካት የወለጋ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች ሀብተ ማርያም ሲሆኑ ምስሉ የተገኘውም ከመጽሀፉ ነው፡፡

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *