Press "Enter" to skip to content

የጎጃም አዲስ አበባ መንገድ ዛሬም አልተከፈተም፤ መንገድ ላይ ያደሩ ተጓዦች እንደተቸገሩ ናቸው፡፡

ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ከትናንት ረፋድ ጀምሮ ኦሮሚያ ክልል ጎሃ ጽዮን አካባቢ በመዘጋቱ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ማለፍ አልቻሉም፡፡

ከጎንደርና ጎጃም ሁሉም አካባቢዎች በመነሳት ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ላይ የነበሩ ሁሉም የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ በመከልከላቸው ተጓዦቹ ለከፋ እንግልት ተዳርገዋል፡፡ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች፣ ለሕክምና ክትትል የሚሄዱ ታካሚዎች፣ በሃይማኖታዊ ጉዞ የነበሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎችና ቤተሰብ ለመጠየቅ የሚጓዙ ሁሉ ናቸው ለእንግልት የተዳረጉት፡፡

የደጀን ወረዳ አስተዳደርና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ካሳ አስፋው ‹‹መንገዱ ትናንት 10፡00 አካባቢ ተከፈተ ተብሎ ነበር፤ ተሽከርካሪዎችም እውነት መስሏቸው ሄዱ፤ ግን ማታ ተመልሰው ነው የመጡት፡፡ መንደኞች የሚያናግራቸውም የመንግሥት አካል እንኳ የለም፡፡ ወጣቶችና ሲቪል ታጣቂዎች መንገዱን ዘግተው እያስፈራሩ ይመልሷቸዋል፡፡ ፖሊሶች ደግሞ ቆመው ያያሉ›› ብለዋል፡፡

ለኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የፀጥታ ኃላፊዎች ስልክ ደውለው ሲጠይቁ ‹‹ወደ አዲስ አበባ ሰልፍ የሚሄዱ ካሉ እየፈተሽን ነው፤ ተፈትሸው ለሰልፉ የማይሄዱትን እያሳለፍን ነው›› እንዳሏቸውና የሚያልፍ ተሽከርካሪ ግን እንዳልነበረ አቶ ካሳ ተናግረዋል፡፡ አብመድ መንገደኞቹን ለሰልፍ ይሂዱ ለሌላ ጉዳይ በፍተሻ እንዴት ማረጋገጥ እንደሚቻል አያውቅም፡፡

አቶ ካሳ እንደተናሩት ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ በርካታ ተሽከርካሪዎች ደጀን ከተማ እንደቆሙ አድረገዋል፤ ተማሪዎችም የምዝገባ ጊዜ እያለፈባቸው ነው፡፡ ‹‹ከባሕር ዳር መግቢያ እስከ ዓባይ አፋፍ ድረስ ደጀን ከተማ ላይ በሁለቱም አቅጣጫ መኪና ቆሟል፤ የዓባይ ባስ ክሲዮን ማኅበር ከ25 በላይ አውቶቡሶች ግን ተሳፋሪዎችን ይዘው ወደመጡበት ትናንት ተመልሰዋል›› ብለዋል ኃላፊው፡፡

መንገደኞቹን ሕዝቡ በየሆቴሉ ድንኳን እየተጣለ ለመንከባከብ እየሞከረ መሆኑን የገለጹጽት አቶ ካሳ ተማሪዎቹ በፍጥነት መንገድ እንዲከፈት እና በመጉላላታቸው ለሚያልፈው የምዝገባ ጊዜ ኃላፊነት የሚወስድ አካል እንዲኖር እየጠየቁ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ተወካይ ኃላፊ ኮማንደር ግርማ ጫኔ ከኦሮሚያ ክልል መሪዎች ጋር በጉዳዩ ዙሪያ እየተነጋሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹መንገዱን የዘጋው በየቦታው ያለ ወጣት ነው፤ ለወጣቶቹም ተልዕኮ የሰጠ የመንግሥት አካል የለም›› መባላቸውን የገለጹት ኮማንደር ግርማ እንዲሁ በወጣቶች ከተዘጋ ወዲያውኑ ፖሊስ ሊያስከፍተው ይገባ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም አቅጣጫ ያለምንም ችግር ተሽከርካሪዎች እያለፉ መሆኑንና አልፎ አልፎ ብዙ ተሽከርካሪዎች በየመንዱ መቆማቸው ለመጭዎቹም እንቅፋት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እኛም እንደ ዞን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንም ከኦሮሚያ ጋር እየተነጋገርን ችግሩ እንዲፈታ እየጣርን ነው ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እየተጉላሉ መሆኑንና ወደ ሀገሪቱ መዲና መግባትን መከልከል ተገቢ አለመሆኑንም ለኦሮሚያ ፖሊስ ጭምር ማሳወቃቸውን ነው ኮማደር ግርማ ለአብመድ የገለጹት፡፡

የመንገደኞች መጉላላት ተገቢ አለመሆኑን በማመልከት በአስቸኳይ እንዲከፈት መንግሥት መሥራት እንዳበለትም አስገንዝበዋል፡፡
ከኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጉዳዩ እንደሚመለከታቸው ተገልጾ የእጅ ስልካቸው የተሰጠን ኮማንደር ለማ ሆርዶፋ የተወሰነ ደቂቃ ጠብቁኝና ደውሉ ካሉ በኋላ ስልክ አያነሱም፡፡

 

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *