Press "Enter" to skip to content

‹‹ኬኔቶ›› እና የጤና መዘዙ

በበዓላት ከሚዘጋጁ ልዩ ልዩ ባህላዊ መጠጦች አንዱ ነው፡፡ እንደ ጠላና አረቄ ዝግጅቱ አድካሚ አይደለም፡፡ የሚደርስበት ጊዜ አጭር ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዶች የ24 ሰዓት ጠላ ይሉታል፡፡ ከገብስ አሻሮ የሚዘጋጀው ኬኔቶ ወይም ቃሪቦ ጣፋጭና የማያሰክር ባህላዊ መጠጥ ነው፡፡

ኬኔቶን ለማዘጋጀት ከተገኘ ጥቁር ገብስ ከጠፋም ነጩን መጠቀም ይቻላል፡፡ ገብሱ አሻሮ እስኪሆን የሚቆላው በትልቅ ብረት ምጣድ ነው፡፡ ከተቆላ በኋላ በትልቅ ብረት ድስት ውኃ ይጣዳል፡፡ ውኃው መፍላት እንደጀመረም ተቆልቶ የተዘጋጀው የገብስ አሻሮ ይጨመርበታል፡፡

በደንብ ተንተክትኮ ድስቱ አፋፍ ላይ የሚንሳፈፈው አረፋ እንደ ሻይ ሲቀላ ገብሱ ከውኃው እየተጣራ በደምበጃን ወይም ባልዲ እንዲጠራቀም ይደረጋል፡፡ በረድ ሲል መጠነኛ እርሾ (የፈረንጅ እርሾ) እንዲሁም ስኳር ይጨመርበታል፡፡ አንዳንዶች ልዩ ልዩ ጣዕም እንዲሰጠው ሎሚ፣ ብርትኳን፣ ማርና የመሳሰሉትን ይጨምሩበታል፡፡

የተጨመረው እርሾና ስኳር ከልኩ ካላነሰ ልክ በ24ተኛ ሰዓቱ ይፈላል ወይም ለመጠጣት ዝግጁ ይሆናል ይባላል፡፡ የ24 ሰዓት ጠላ የሚሉትም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ አያሰክርም ተብሎ ስለሚታሰብ አልኮል የማይጠጡ ሰዎች ኬኔቶን ይመርጣሉ ሕፃናት ሳይቀሩ ኬኔቶ በብርጭቆ እየተሞላ እየተሰጣቸው ይጨልጣሉ፡፡ ኬኔቶ በየዝግጅቱ አማራጭ መጠጥ ሆኖ ይቀርባል፡፡

ከገብስ አሻሮ የሚዘጋጅ በመሆኑ ቀለሙ እንደ ጠላ ቡናማ ሳይሆን ጥቁር ነው፡፡ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ለዘመናት ሲጠጣ የኖረው ኬኔቶ ከመጣፈጡ ባለፈ የጎንዮሽ ጤና ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል አይጠረጠርም፡፡ ነገር ግን ኬኔቶ የሚያደርሰው የጤና ችግር እንዳለው የተረጋገጠው በአገር ውስጥ ተመራማሪዎች እ.ኤ.አ. በ2017፣ በውጭ አገር ተመራማሪዎች ደግሞ ከሰሞኑ ነው፡፡

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ምግብ ረዳት ፕሮፌሰር ኩመላ ዲባባና በሌሎች ሦስት ባለሙያዎች በኬኔቶ ላይ የተሠራው ጥናት ‹‹ኬኔቶ በገጠርና በከተማ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ባህላዊ መጠጥ ሲጠጡት የኖሩ ቢሆንም በጤና ላይ ስለሚኖረው የጎንዮሽ ጉዳት ግን ምንም ዓይነት ጥናት አልተደረገም፤›› የሚል መግቢያ አለው፡፡

የሚዘጋጀው በየዕለቱ ለምግብነት ከሚውሉ ግብዓቶች ሆኖ ሳለ ምን ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት ሊኖረው ይችላል የሚል ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፡፡ ኬኔቶ የጎንዮሽ ጉዳት እንዲኖረው ያደረገው ግን የሚዘጋጅበት መንገድ ነው ይላል ጥናቱ፡፡ በዚህ ባህላዊ መጠጥ ውስጥ “ካንሰር አማጭ” እንደሆነ የሚነገርለት፣ በሴል ላይ ከባድ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል በምርምር የተረጋገጠበት፣ በነርቭ ላይ ዕክል የመፍጠር አቅም እንዳለው የሚነገርለት፣ በተዋልዶ ጤና ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያደርስ የተወራለት ‹‹አክላማይድ›› የተባለ ኬሚካል ይገኝበታል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንደሚገልጹት፣ አክላማይድ የተባለው ኬሚካል በምግብ ውስጥ እንደሚገኝ የተረጋገጠው እ.ኤ.አ. በ2002 ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ኬሚካሉ የሚታወቀው ለኢንዱስትሪ ግብዓት በመሆን ነው፡፡ አክላማይድ በገብስ በስንዴና በተለያዩ በስታርች የበለፀጉ የሰብል እህሎች እንዲሁም በድንችና በመሳሰሉት ምርቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ አስትሮጂን የተባለ የአሚኖ አሲድ ዓይነት ፕሮቲን ባላቸው ምግቦችም አክላማይድ ይገኛል፡፡

እነዚህ በስታርች የበለፀጉ ምርቶች ከፍተኛ የአክላማይድ ኬሚካል ያሉት የሚኖራቸው ከ120 ሴንቲ ግሬድ በላይ በሆነ ሙቀት ሲበስሉ፣ ሲቆሉ ወይም ሲጠበሱ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ፡፡

ገብስ ደግሞ ከፍተኛ የስታርች ይዘት ያለው፣ አስትሮጂን የተባለው አሚኖ አሲድ የሚገኝበት የሰብል ምርት ነው፡፡ ኬኔቶ ለማዘጋጀት ከ120 ሴንቲግሬድ በላይ በሆነ ሙቀት ገብስ ተቆልቶ አሻሮ ሲሆን፣ በውስጡ የሚኖረው የኬሚካሉ ክምችት በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፡፡ ‹‹ገብሱን እንደ ከሰል አድርገው ነው የሚቆሉት፡፡ ቀለሙ ብቻ የሚፈለግ በሚመስል መልኩ አሻሮ ተደርጎ ይዘጋጃል፤›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ኩመላ፣ በአንድ ኪሎ ግራም ውስጥ የሚኖረው የኬሚካሉ መጠን ወደ 3,440 ማይክሮ ግራም እንደሚያድግ ገልጸዋል፡፡

አክላማይድ በቡና፣ በአረንጓዴ ሻይና በተለያዩ ምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ይገኛል፡፡ ክምችቱ የሚጨምረውም በከፍተኛ ሙቀት ምግብ ሲጠበስ፣ ሲቀቀል እንዲሁም ሲቆላ ነው፡፡ የሚያደርሰው ጉዳት እንደሚወሰደው መጠን የተለያየ ይሆናል፡፡

በኬኔቶ ላይ የኬሚካሉን ክምችት እንዳይፈጥር ለማድረግ ገብስን ለቆሎነት በሚውል መጠን መቁላት ግድ እንደሆነ ረዳት ፕሮፌሰር ኩመላ ገልጸዋል፡፡

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *