የቀደሙት ያቆዩትን የመረዳዳት ባህል ትውልዱ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ ብጹ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አሳሰቡ
By: Date: September 22, 2019 Categories: ሁነቶች,ዜና

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብጹ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ አባቶችና እናቶች ያቆዩትን የመረዳዳት ባህል ትውልዱ ሊያስቀጥለው እንደሚገባ አሳሰቡ።

ብጹ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ይህንን ያሉት በችግር ላይ የሚገኙ ህጻናትን ለመደገፍ ያለመ የአንድነት ማህበር ምስረታ ላይ በመገኘት ባደረጉት ንግግር ነው። የቀደሙ አባቶችና እናቶች በችግር ውስጥ ያሉ ህጻናትን በመርዳትና በመደገፍ ለወግ ለማዕረግ ማብቃታቸውን በማስታወስ የአሁኑ ትውልድም ለሌሎች መኖርን ተግባራዊ ማድረግ አለበት ብለዋል።

በተለይ እንደ አገር በአንድ ወቅት የገጠመን የረሃብ ችግር ለመፍታት በወቅቱ የነበሩ የቤተክርስቲያኗ አባቶች የህጻናትና የቤተሰብ ጉዳይ ድርጅትን አቋቁመዋል። ከተቋቋመ 45 ዓመታትን ያስቆጠረው ይህ ድርጅት ከ42 ሺህ በላይ ህጻናትን አሳድጎ ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል።

ይህ በጎ ተግባር ትውልዱ እንዲያስቀጥለውና የቀደሙትን ፈለግ ተከትሎ የመረዳዳት ባህል እንዲያጎለብት ጥሪያቸውን አቅርበዋል። የድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ቀሲስ ሳምሶን በቀለ በበኩላቸው ድርጅቱ በተለያዩ ምክንያቶች ሳቢያ የቀድሞ አባቶችና እናቶች ያቆዩትን ያህል ህጻናትን የመርዳት ስራ እየሰራ አይደለም ነው ያሉት።

ድርጅቱ ለችግር የተጋለጡ ሃይማኖትና ብሔርን ሳይለይ ኤርትራን ጨምር በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በ36 ቅርንጫፎች አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ተቋማት 18 ብቻ ሲሆኑ ችግረኛ ህፃናትን የመቀበል አቅማቸውም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለድርጅቱ ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርጉ የቆዩት ግሪክና መሰል አገራት የኦኮኖሚ ቀውስ ውስጥ መግባትና ሌሎችም አገሮች ከኢትዮጵያ በላይ ችግር ላለባቸው አገራት  ድጋፉን በማዛወራቸው መሆኑን ጠቁመዋል።

ይህንን በጎ ተግባር ለማስቀጠል የቀድሞ አባላቶች በጋራ ይህንን ድርጅት ለመደገፍ የሚያስችል ማህበር በዛሬው ዕለት አቋቁመዋል። ብፁ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ለዚህ በጎ ተግባር መጠናከር ቤተክርስቲያኗ የበኩሏን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል። የአሁኑ ትውልድም ይህንን በጎ ተግባር ለማስቀጠል አሻራውን እንዲያሳርፍ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ምንጭ ኢዜአ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *