ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በወልዲያው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ያስተላለፉት ተጠየቃዊ መልእክት (በታደሰ ወርቁ)

ዛሬ መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለውን መንግሥታዊ በደል እና ፖለቲካዊ ጥቃት የሚያወግዙ ሰላማዊ ሰልፎችበአንጎለላ ጠራ ላልይበላ ወልደያ ደብር ብርሃን ባሕርዳር ሞጣ ቡሬ እንፍራንዝ ደብረ ማርቆስ በፍኖተ ሰላም ቆቦ መንዝ መሐል ሜዳ በምንጃ ዳንግላ መርዓዊ መቅደላ ዋድላ ኮን ዳባት ውጫሌ ዳላንታ ደባርቅ ቢቸና ጫጫ ግሽ ዓባይ በአንዳቤት በጃራ ገዶ ማጀቴና በሌሎችም ከተሞች በሰላም ተካሔደው በሰላም ተጠናቀዋል፡፡

በሰሜን ወሎ በወልደያ ከተማ በተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ እርጅናንና የጤናቸውን እክል ምክንያት ሳያደርጉ የተለመደውን አባታዊ ጥብዓት ተለብሰው የሀገረስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ቡነ ቄርሎስ ሲገኙ በባሕርዳር ከተማ በተካሔደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ደግሞ ልማት ከቆራጥነት ጋር የተሰማማላቸው የባሕርዳርና አከባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ተገኘተው መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በወልዲያ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተገኙት አረጋዊውና ሊቁ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ አጤ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ እና ለማዘመን ደፋ ቀና ሲሉና በየስፍራ ሲንከራተቱ መባጃታቸውን አዘክረውና÷መቅደላ አፋፍ ላይ ሲደርሱ÷የውጭና የውስጥ ጠላት ወረራቸው ከውጭ ጠላት የግቢ ጠላት ይከፋል ምስጢሩን ያውቃል መውጫና መግቢያ ቀዳዳውን ያውቃል እናም ሁሉም ወዳጅ መስለው ጠላት እንደሆኑባቸው የተመለከቱትና ሁሉ ነገር ከአቅማቸው በላይ ሲሆንባቸው

አጤ ቴዎድሮስ ሀገር ኢትዮጵያ ሰው ይፍጠርልሽ በማለት እጃቸውን ለባዕድ ከመስጠት ራሳቸውን ማጥፋታቸው ለሰልፈኛው ተርከው በዘመኑ አይዞህ ባይ አግኘተው ቢሆን ኖሮ ሕልማቸውም ተሳክቶ ይህ ሁሉ አደጋ በኢትዮጵያ አይርስብም ነበር ሲሉ ገልጠዋል፡፡

ወቅታዊውን ሀገራዊ መከፋፈል ከአጤ ቴዎድሮስ የአንድነት ሕልም ጋር አሰናስነው ለሰልፈኛው ያመሳጠሩት ሊቁ ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ‹ ከ1966 ዓ.ም ጀምሮ በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ሲዘራ የነበረው የዘር አሜኬላ ይሔው ፍሬ አፍርቶ ኢትዮጵያን የደምና የውድመት ሀገር አድረጓታል፡፡

ጎሳ ከጎሳ ደም ማፋሰሱ ወንድም ወንድም ማጋደሉ በጎሳ ልዮነት ንብረት ማውደሙ ይኼው አርባ ስድሰተኛ ዓመቱን ይዟል ብለው ከገለጡ በኋላ እነዚሁ ጎሰኞች አሁን ደግሞ ወደ አንጋፋዋ ቤተ ክርስቲያን ፊታቸውን አዞረዋል፡፡ይኼ ደግሞ ለጤናቸው አይደለም፤ ሲያዝባቸው ነው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ ሰላም ማውረዳቸውን በፖለቲካ እምነታቸው የተነሣ የታሰሩት መፍታታቸውን ሁለቱን ሲኖዶሶች አንድ በማድረጋቸውና የተቀማባትን የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ እንዲመለስ ማድረጋቸው

በመልካምነት የዘረዘሩት ብፁዕነታቸውአሁን ሀገሪቷ ላይ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ካለው ጥፋት ጋር አነጻጽረው የወልደያ ከተማ ሰልፈኞችን አግኘቶ ከማጣት ይሰወራቸው በማለት የዶክተር ዓብይን የመጀመሪያ ወራት መልካም ተግባራት አግኘቶ እንደማጣት ቆጥረውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይን እኚህ ወንድማችን የመጀመሪያ አመጣጣቸው መልካም ነበር መፈክራቸውም መልካም ነበር በእሾህ መካከል እንደሚገኙም ይረዳኛል የሚሉት ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ በዮዲትም በግራኝም በጣሊያን ወረራ ጊዜም በአንድ ቀን ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት ተቃጥለው አይታወቅም፡፡ይህ በታሪካችን ዐይተነውን የማናውቀው ውድመት የታየው በእርሳቸው ዘመን ነው፡፡

እናም ከዛሬ ጀምሮ ሃይማኖትንና ጎሳ መሠረት ያደረገ የዘር ማጥፋት የንብረት ማውደምና ክርስቲያኖችን የልጅ ልጅ ካዮበት ማፍለስ ይቁም ሲሉ መንግሥትን አሳስበዋል፡፡

ሕዝብን ከሕዝብ ጋር ለማናከስና ለማባላት ቤተ ክርስቲያንን ለማስጠላት አንድን ታሪክ ከአንድ ታሪክ ጋር እያጣመሙ መጓዝን የዕለት ሥራቸው ያደረጉ መስክ ወለድ ፖለቲከኞች መኖራቸውን ያስታወሱት በፁዕነታቸው የሃይማኖት ሰው መስለውና ፖለቲካቸውን በጀርባቸው አዝለው የኦሮሚያ ቤተ ክህነት

ይቋቋም የሚሉት ወገኖች ዓላማ የኦሮሞ ሕዝብ በቋንቋን እንዲሰበክለትና እንዲቀደስለት አስበውለት ሳይሆን የኦሮሞን ሕዝብ ከሰሜኑና ከሌላውም ወገኑ ለመለየት የዘየዱት ስልት መሆኑን ልታውቁት ይገባል ሲሉሴራውን ገልጠዋል፡፡

የዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ መብት መከበር ለመጠየቅ የተካሔደ ሰልፍ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው ምድር ለሰው ልጆች ሁሉ በእኩልነትና በነጻነት የተሰጠች እንጂ የተወሰኑ ቡድኖች ብቻ መጠቀሚያ ሰላልሆነች በሕገ መንግሥቱ የተሰጠን የመኖርና የማምለክ ነጻነት መንግሥት እንዲያስጠብቅልን ተግቶ ሊሠራ ይገባል ብለዋል፡፡

ይህን ዘገባ ያጠናቀርኩት የተላከልኝን የድምፅ ሪከርድ በመጠቀም ነው። ምንም እንኳን ብፁዕ አቡነ አብርሃም በባሕርዳር ያስተላለፉት መልእክት አንዳንድ ወንድሞቻችን ቢያስነብቡንም የተቀዳውን ሙሉ ድምፅ ከአገኘው እንዲሁ አጠናቅሬ የማቀርብላችሁ መሆኔን ከወዲሁ አሳውቃለሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *