Press "Enter" to skip to content

ግብፅ በግድቡ ላይ ያቀረበችው ሀሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚዳፈር ነው ተባለ።

በህዳሴው ግድብ ላይ ግብጽ ያቀረበችውን አዲስ ሀሳብ ኢትዮጵያ ውድቅ አድርጋለች፡፡ የሦስቱ ሀገራት የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሮች ከሰሞኑ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ ዙሪያ መምከራቸው ይታወሳል፡፡

በዚህም ግብፅ በህዳሴው ግድብ ላይ ከበፊቱ የሦስትዮሽ ስምምነት ያፈነገጠ ሀሳብ አቅርባለች፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በቅርቡ በግብጽ የቀረበው ምክረ-ሀሳብም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ገልፀዋል።

ምክረ ሀሳቡ የግብፅን ጥቅም ብቻ ያማከለ እና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ ከግድቡ የአሞላል ሂደት እና በግድቡ አሰራር ላይም የግብፅ ባለሞያዎች እንዲሳተፉ የሚሉ እና ሌሎችም ምክረ ሀሳቦችን ነው ያቀረበችው፡፡

ግብፅ ያቀረበችው ምክረ ሀሳብ ኢትዮጵያ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ኪዩቢክ ውሀ እንድትለቅ እና በግብፅ የሚገኘውን አስዋን ግድብ ከ165 ሜትር ዝቅ የሚል ከሆነ ተጨማሪ ውሀ ኢትዮጵያ እንድትለቅ የሚጠይቅ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሀሳቡ ሉዓላዊነቷን የሚዳፈር በመሆኑ ውድቅ አድርጋለች፡፡ በግድቡ ላይ የኢትዮጵያ ጥቅምና የመወሰን መብቷ በግብፅ ይሁኝታ እንዲመሠረት መታሰቡም መቼም ቢሆን ውድቅ የሚደረግ ሀሳብ ነው ብለዋል ሚኒስትሩ።

በመሆኑም ሌላ ድርድር ይካሄዳል፡፡ ሦስቱ ሀገሮች (ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ) ከመስከረም 19 እስከ 22/2012 በጉዳዩ ላይ እንደሚመክሩ የኢፌዴሪ የውሀ፣ መስኖና ኢነርጅ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ጉዳዩንም ከሦስቱ ሀገሮች የተወጣጣ ገለልተኛ የሳይንስና ምርምር ብሔራዊ ኮሚቴ ያጠናዋል ተብሏል፡፡

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *