Press "Enter" to skip to content

በግድቡ ዙሪያ የግብጽ ጉዞዎች ንቃትና ትጋት ይሻሉ

“የውጭ ጫና ለመቋቋም የሚቻለው የቤት ውስጥ ፖለቲካን ማስተካከል ሲቻል ነው። በውስጥ ያልተስተካከለ ነገር ካለ የውጭ ጉልበተኛን መቋቋም ያስቸግራል። በቤት ውስጥ ብዙ ቀዳዳዎች አሉ፡፡ እነዚህን መዝጋት ወሳኝና የመጀመሪያው ነው።” – ፕሮፌሰር መረራ
—-
ግብጽ የህዳሴ ግድቡን የውሃ መሙያ ጊዜ ለማራዘም የምታደርጋቸውን ጥረቶች ለማምከን የኢትዮጵያ መንግሥት የነቃ ዲፕሎማሲና ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ ማድረግ እንዳለበት ምሁራን ያሳስባሉ።

የግብጽ ባለስልጣናት ሰሞኑን በግድቡ አሞላልና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የተለያየ ሀሳብ እየሰነዘሩ ናቸው። የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜህ ሽኩሪ፣ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታንና የውሃ አሞላል ሂደት በተመለከተ በሱዳን፣ በኢትዮጵያና በግብጽ ለአራት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ውይይት ምንም ውጤት እንዳላስገኘ ተናግረዋል።

የግብጽ መስኖ ሚኒስቴር በታላቁ የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና ሥራ አጀማመር ላይ ኢትዮጵያ የግብጽና የሱዳንን እቅድ ውድቅ ማድረጓንም ከሶስቱ አገራት ድርድር በኋላ ለግብጽ መገናኛ ብዙኃን ይፋ አድርጓል።

የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በስምንተኛው የግብጽ ወጣቶች ብሄራዊ ጉባዔ ላይ ‹‹የአረብ አብዮት ባይካሄድ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን አትገነባም ሲሉ ቁጭታቸውን ገልጸዋል።

ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በግብጽ አገር የሰሩቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ ዓባይ ለግብጾች ህይወታቸው፣ ምግባቸው፣ መጠጣቸው፣ ውቃቢያቸው ጭምር በመሆኑ ቤት እንኳ ሲያከራዩ የበሩ ፊት ወደ አባይ የዞረው ዋጋው በእጥፍ እንደሚጨምርና ግብጾችን በዓባይ ላይ በመደበኛ ስነልቦና ተደራድሮ በምክንያታዊነት ማሳመን እንደማይቻል፤ ኢትዮጵያም ይህን ተገንዝባ በጥንቃቄ መንቀሳቀስ እንዳለባት ያስጠነቅቃሉ።

እንደ ፕሮፌሰር መረራ ገለፃ፤ የውጭ ጫና ለመቋቋም የሚቻለው የቤት ውስጥ ፖለቲካን ማስተካከል ሲቻል ነው። በውስጥ ያልተስተካከለ ነገር ካለ የውጭ ጉልበተኛን መቋቋም ያስቸግራል። በቤት ውስጥ ብዙ ቀዳዳዎች አሉ፡፡ እነዚህን መዝጋት ወሳኝና የመጀመሪያው ነው ።

የኢትዮጵያ ህዝቦች ግድቡን የሚነካ ቢመጣ “ሀብታችን ነው” ብለው እንዲቋቋሙ ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በሁሉም አቅጣጫ ብሄራዊ መግባባት በመፍጠር ወደ አንድነት መምጣት አለበት። ግብፆችም ይህን እንዳይጠቀሙና የውጭ ጫና ጉዳት እንዳይመጣ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ።

ፕሮፌሰር መረራ ግብፅ በጎረቤት አገራት በኩል ተጽዕኖ ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት መንገድ ስለያዘ ችግር የለውም ። ኤርትራ ከግብጽ በተሻለ ጥቅሟ ከኢትዮጵያ ጋር የተሳሰረ ነው። በላይኞቹ አገራትና በጎረቤቶቻችን በኩል ትብብሩን ማጠናከር ለፖለቲካ ይጠቅማል። ሆኖም በግድቡ ተጠቃሚነት ዙሪያ የኢትዮጵያን ያህል ተጠቃሚ ስላልሆኑ ተጽዕኗቸው ብዙም አይደለም። ዓለም አቀፍ ጫና ቢከሰትና ግብጾች ኃይል ለመጠቀም ቢፈልጉ ለመቋቋም እንደሚጠቅሙም ያስረዳሉ።

የሱዳንና የግብጽ ግንኙነት በተለያየ መንገድ የተሳሰረ መሆኑን የሚያነሱት ፕሮፌሰር መረራ ፤ ሱዳን ከሁለቱም አገራት ጋር በሚደረገው የጋራ ድርድር ሁሉንም በሚጠቅም መልኩ በመስራት ግንኙነቱ እየተሻሻለ እንዲመጣ እንደምታግዝ አመላክተዋል።

ፕሮፌሰር መረራ ፤ ኢትዮጵያ ዓባይ ወንዝ እያላት ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ስትራብ ነበር። ግብጽ ኢትዮጵያውያን እየተራቡ ውሃውን እንዝናናበት የሚሉት ፖለቲካ ገደብ እንዳለው ባይረዱም ኢትዮጵያ ማስረዳት እንደማያቅታት ያስገነዝባሉ።

‹‹እነርሱ ብቻ ሳይሆኑም እኛም የተራበ ህዝብ አለን። የሚሻለው በጋራ አረንጓዴ በማድረግ ሚዛኑን የጠበቀ ውሃ እንዲኖር መስራት ነው። ግብጾች የግል ህልማቸውን ቀንሰው የጋራ ህልም እንዲኖረን ኢትዮጵያ በብዙ አቅጣጫ መንቀሳቀስ አለባት። የሰውን ሀብት የመውሰድ ሳይሆን የራሷን ሀብት የመጠቀም መብት እንዳለት ዲፕሎማቶችም መስራት አለባቸው። ኢትዮጵያውያን እየተራቡ ግብጾች ይዝናኑበት የሚል ውሳኔ ተገቢ አይደለም›› ብለዋል።

የምስራቅ ናይል አህጉራዊ የቴክኒክ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ፤ በግላቸው በሰጡት አስተያየት ‹‹ ግብጽ የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ ወደ አረብ ሊግ፣ አፍሪካ ህብረት፣ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትና የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት እንወስዳለን በማለት ትዝታለች። ጉዳዩን ቢወስዱት ግን መፍትሄ ከእነርሱ አያገኙም።

የአፍሪካ ህብረት ግድቡ በተጀመረ ወቅት አገራት በቅኝ ግዛት ስምምነቶችና ህጎች ይገዙ ማለት ተገቢ አለመሆኑን አሳውቋል። ግብጽ የአረብ ሊግ አባል ስለሆነች ድጋፍ ሊሰጣት ይችል ይሆናል። ድጋፍ ቢያገኙም መፍትሄ የለውም። መፍትሄው አገራቱ በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግረው ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ሥራ ቢያከናውኑ ነው ››በማለት በሶስተኛ አካል የሚመጣ መፍትሄ እንደማይኖር ይናገራሉ።

እንደ አቶ ፈቅአህመድ ገለፃ፤ ኢትዮጵያ በግድቡ ግንባታ ላይ የህዝብ ድጋፍንና ብሄራዊ መግባባትን መልሶ ማጠናከርና በአገር ውስጥ መግባባት እንዲኖር መስራት ያስፈልጋታል፡፡ በአገር ውስጥ ጠንካራ ድጋፍ ካለ ከውጭ የሚመጣውን ጫና በቀላሉ መቋቋም ይቻላል።

በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መርህ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ለሚመለከታቸው አካላት ግልጽ ማድረግ ይገባል። በተለይም ግብጽ የምትሄድበትን መንገድ በመረዳት ሳይንሳዊ መረጃዎችን አስቀድሞ በመልቀቅ እንቅስቃሴዎቹን የማዳከምና የማዳፈን ሥራዎች በሰፊው መሰራት አለበት።

አብዛኞቹ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ከኢትዮጵያ ሀይል ስለሚፈልጉ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ከላይኛው የተፋሰሱ አገራት ጋር የተጀመሩ ሥራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል። ይህ ድጋፍ እንዲቀጥልና የናይል ስምምንት ተፈርሞ ዓለም አቀፍ ህግ እንዲሆን መሰራት አለበት፡፡

አቶ ፈቅአህመድ የግብጽ ፕሬዚዳንት ‹‹የአረብ አብዮት ባይከሰት ኢትዮጵያ ግድቡን አትገነባም ነበር” የሚል ንግግር አድርገዋል። ያደረጉት ንግግር ግን በተሳሳተ መረጃ ላይ የተመሰረተና የግብጽን ወጣትና ዓለም አቀፍ ማህበረሰብን ለማደናገር ነው ይላሉ።

‹‹የታላቁ ህዳሴ ገድብና የግብጽ አብዮት አይገናኝም። የግድቡ ግንባታ ስምምነት የተፈረመው ከግብጽ አብዮት ሁለት ወር ቀደም ብሎ እ.አ.አ ታህሳስ 31 ቀን 2010 ነው። ግድቡ በህዳሴ እቅድ ሆኖ የገባው ከስምንት ወር በፊት ነው። አብዮቱና የግድቡ ግንባታ በፍጹም የማይገናኝም›› በማለት አቶ ፈቅአህመድ ያስረዳሉ።

አቶ ፈቅአህመድ እንዳብራሩት የግብጽ አብዮት ተነሳም አልተነሳም የመብት ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ በድንበሯ ውስጥ ያለውን ውሃ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት አላት። የግብጽ አብዮት ኖረም አልኖረም ኢትዮጵያ ግድቡን ለመስራት የማንም ፍቃድ አያስፈልጋትም። ይህን ዓለም አቀፍ ህግም ይደግፋል። የሚጣልባት አንድ ግዴታ የታችኛው አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት ላለማድረስ ጥንቃቄ ማድረግ ነው።

የግብፁ ፕሬዚዳንት ንግግሩን ያደረጉት ለፖለቲካ ፍጆታ ነው። በአስተዳደራቸው፣ በፍትህ፣ በመልካም አስተዳደርና በኢኮኖሚ በየጊዜው የሚነሳውን ጥያቄ ለማዘናጋት ነው። “አብዮት ማካሄድ ዋጋ አስከፍሎናል” ያሉት ምናልባትም ወጣቱን ለማስጠንቀቅ ያደረጉት ነው። ከዚህ ካለፈም በግድቡ አሞላል ድርድር ላይ ጫና ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ አቶ ፈቅአህመድ ያመላክታሉ።

ግብጽ የግድቡን ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት፣ በአረብ ሊግና በተባበሩት መንግሥታት እንዲሁም ከጎረቤት አገራት ጋር በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ ውይይት በማድረግ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረገች ትገኛለች።

አዲስ ዘመን መስከረም 7/2012

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *