በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው የተገነቡ ት/ቤቶች ለማስተማርያነት ዝግጂ ሆኑ

(አብመድ) በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት አማካኝነት ከሚገነቡት ትምህርት ቤቶች አራቱ ለ2012 የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

የቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን ፈንታ ለአማራ ብዙኃን መገናኛ ድርጅት እንደገለጹት ከትምህርት ቤቶቹ መካከል አራቱ ለማስተማር ዝግጁ ሆነዋል፡፡ ለማስተማር ዝግጁ ከሆኑት መካከል በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ አስተዳድር ላይ የሚገኘው የሎዛ ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚገኝበት አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡

የሎዛ ማርያም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመንገድ ችግር ምክንያት ሙሉ ለሙሉ ሥራው ባይጠናቀቅም ለሥራ ዝግጁ እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡ ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ ክፍሎች እንደተዘጋጁ እና ቀሪ ሥራዎች ከትምህርቱ ጎን ለጎን እንደሚሠሩም ነው የተገለፀው፡፡

ከሎዛ ማርያም ትምህርት ቤት በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት የሊበን ጭቋላ የጉጂ እና የጃኮ ትምህርት ቤቶችም ለማስተማር ዝግጁ የተደረጉ ናቸው፡፡ ከአራቱ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ አዲስ አበባ ላይ ቁስቋም ትምህርት ቤት በሚል የተሠራው ፕሮጀክት ግንባታው መጠናቀቁን እና ትምህርት ቤቱ ተቀይሮ ለሕጻናት ማሳደጊያ እንዲሆን መወሰኑን አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡

ሰበታ ላይ የሚታደሰው የዐይነ ስውራን ትምህርት ቤትም ሥራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል ነው ያሉት፡፡ በመሆኑም በቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጽሕፈት ቤት ከሚገነቡት አዳዲስ 19 ትምህርት ቤቶች እና አንድ የዐይነ ስውራን ትምህርት ቤት እድሳት ውስጥ ስድስቱ ወደ ሥራ ይገባሉ፡፡

ቀሪዎቹ ደግሞ በ2012 ዓ.ም ሙሉ ለሙሉ ግንባታቸው ተጠናቅቆ በ2013 የትምህርት ዘመን ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሏል፡፡ በአማራ ክልል ከሚገነቡት የደባርቅ እና የዋግ ኽምራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እንዳልጀመሩ አቶ ሙሉቀን ነግረውናል፡፡

የደባርቁ በዝናብ ብዛት የዋግኽምራው ደግሞ የመስሪያ በቂ ጊዜ አለን በሚል እንደዘገዩ ተገልጧል፡፡ ደቡብ ወሎ ዞን የሚገነባው ትምህርት ቤትም በዝናብ ምክንያት እንደዘገዬ የገለጹት ዳይሬክተሩ በ2012 ዓ.ም አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም ለአገልግሎት ክፍት የሚሆኑት አራቱ ትምህርት ቤቶች እያንዳንዳቸው በ20 ሚሊዮን ብር ወጪ ነው የተገነቡት ተብሏል፡፡

ቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች ደግሞ እያንዳንዳቸው 13 ነጥብ 75 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግባቸው አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ፕሮጀክቶች ከመንግሥት በጀት ውጪ በድጋፍ የሚሠሩ ናቸው፡፡ በሀገሪቱ በምግብ እጥረት ብቻ ሳይሆን በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እጥረትም ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው ያሉት አቶ ሙሉቀን ጽሕፈት ቤቱ በተገኘው ገንዘብ የሚችለውን ያህል እየሠራ እንደሆነና ይህም ግን በቂ አለመሆኑን አስረድተዋል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *