Press "Enter" to skip to content

በምዕራብ ኦሮሚያ የጉሊሶ ከተማ ከንቲባ ግድያ የነዋሪውን ስጋት አባብሷል

ምዕራብ ወለጋ የምትገኘው የጉሊሶ ከተማ ከንቲባ አቶ አበበ ተካልኝ በመኖሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ በታጣቂዎች ተገደሉ።

ከተማዋን ላለፉት ጥቂት ወራት ያስተዳደሩት የከንቲባው ሥርዓተ ቀብር ትናንት መፈጸሙም ተነግሯል።

አቶ አበበ ዕሁድ ምሽት ላይ ከመኖሪያ ቤታቸው ውጪ በታጣቂዎች መገደላቸውን የጉሊሶ ወረዳ የአስተዳደር እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋ ሊካሳ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

“ደጃፋቸው ላይ በሁለት ጥይት ግንባራቸውን ተመትተው ነው የተገደሉት” ሲሉ የጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ከንቲባውን ደጃፋቸው ላይ ከገደሉ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ዘልቀው በመግባት “ለስብሰባ የተዘጋጀ ጽሑፍ እና የአካባቢውን ባለስልጣናት ስም ዝርዝርን የያዘ ላፕቶፕ ኮምፒዩተር ይዘው ሄዱ” ሲሉ አቶ ተስፋ ጨምረው ተናግረዋል።

ከንቲባውን ገድለው ላፕቶፕ ዘርፈው ሄዱ የተባሉት ታጣቂዎች በቁጥር ወደ ስድስት እንደሚጠጉ የሟች የቤተሰብ አባላት ለመንግሥት የጸጥታ አካል መናገራቸውም ተገልጿል።

ግድያው እንዴት ተፈጸመ?ጥቃቱ በተፈጸመበት ምሽት የሁለት ልጆች አባት የነበሩት ከንቲባ አበበ ተካልኝ እሁድ ምሽት ላይ ከልጆቻቸው ጋር ቴሌቪዥን እየተመለከቱ ላፕቶፓቸው ላይ እየጻፉ ነበር።
አራት ሰዓት ገደማ ላይ ከንቲባውን የሚፈልግ ሰው ከውጪ እንደተጣራና 10 ዓመት የማይሞለው ልጃቸው ወደ ውጪ ሊወጣ ሲል አባት ልጅን ከልክለው እንደወጡ ደጃፋቸው ላይ በሁለት ጥይት ግንባራቸውን ተመትተው መገደላቸውን የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ተስፋ ለቢቢሲ አስረድተዋል። ከዚህ ቀደምም በምዕራብ ኦሮሚያ በነዋሪች ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች በተጨማሪ፤ የአካባቢው ባለስልጣናት የታጣቂዎች ኢላማ ሆነው ቆይተዋል። ከጥቂት ወራት የቄለም ወለጋ ዞን የደህንንት እና የኦዲፒ ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ግለሰብ ተገድለዋል።

በተመሳሳይ የደምቢዶሎ ዩኒቨርስቲ ፕረዝዳንት በታጣቂዎች ታግተው የነበረ ሲሆን የዚያው የደንቢ ዶሎ ከተማ ከንቲባም ቀደም ሲል በጥይት ተመተው በህይወት መትረፍ ችለዋል።

የተያዘ አለ?

ይህ ግድያ ከተፈጸመው በኋላ እስካሁን በቁጥጥር ሥር የዋለ ተጠርጣሪ እንደሌለ የሚናገሩት አቶ ተስፋ ፖሊስ የጥቃቱን ፈጻሚዎች ለመያዝ የክትትልና የማጣራት ሥራ እያከናወነ እንደሆነ ተናግረዋል።

በታጣቂዎች የተገደሉት ከንቲባ ሚስት ከክስተቱ በኋላ ለጸጥታ አካላት ተናገረዋል ብለው አቶ ተስፋ ሊካስ እንደጠቀሱት፤ ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች የሲቪል ልብስ ለብሰው እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህም የገጠሩም ሆነ የከተማ ነዋሪ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ውስጥ ስለገባ፤ ”ነጋዴው ወደ ሌላ ከተማ እየሸሸ ነው። አርሶ አደሩም ከገጠር ወደ ከተማ እየሸሸ ነው” በማለት ነዋሪዎች የገቡበትን የደህንነት ስጋት ቀደም ሲል ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ከግድያው በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ የመንግሥት ሰራተኞች እጅጉን ተደናግጠዋል ሲሉ የጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው በአካባቢው የተፈጠረውን ስጋት ተናግረዋል።
“ከግድያው በኋላ የመንግሥት ሰራተኞች ተደጋግጠዋል። ግድያው በእኛ ላይ ሊፈጸም ይችላል የሚል ስጋት ስላደረባቸው ትናንት (ሰኞ) ወደ ሥራ አልገቡም።”የዚያው አካባቢ ተወላጅ የነበሩት ከንቲባው አቶ አበበ ተካልኝ በታጣቂዎቹ የተገደሉበት ምንክንያት እስካሁን ግልጽ አይደለም። የአስተዳደር እና ጸጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ይህን ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰቦች ወደ ጫካ መሸሻቸውን ይናገራሉ። ኃላፊው “በአካባቢው የሚንቀሳቀሱና እራሳቸውን የኦነግ ሠራዊት እየሉ የሚጠሩት ታጣቂዎች ይህን ግድያ የፈጸሙት ናቸው ብለን እናምናለን” ብለዋል።

አቶ ተካልኝ ከመገደላቸው ከሁለት ቀናት በፊት (ቅዳሜ) ከምሽት በቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሚ ከተማ ሁለት ሰዎች በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል።

“ቅዳሜ ምሽት ተኩስ ነበር። በዚያ ተኩስ ሳቢያ ነው ሁለቱ ነዋሪዎች የተገደሉት። እነሱን የገደለው አካል የቱ እንደሆነ ደግሞ መለየት አልቻልንም” በማለት ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን የማንጠቅስ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ነግረውን ነበር።

በምዕራብ ኦሮሚያ ይህን መሰሉ በነዋሪዎችና በመንግሥት ኃላፊዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችና ግድያ ሲፈጸም ወራት የተቆጠሩ ሲሆን ለጥቃቱ በይፋ ኃላፊነት የሚወስድም ሆነ ተጠያቂ የሆነ አካል አልተገኘም። ከአንድ ዓመት በፊትም በዚሁ ጉሊሶ ከተማ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ እና አዋሽ ባንክ በታጣቂዎች መዘረፋቸው ይታወሳል። በወቅቱ መንግሥት የኦነግ ሠራዊት አባላት ዘረፊያውን መፈጸማቸውን አሳውቆ ነበር።

BBC

Be First to Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *