Thu. Feb 27th, 2020

Yeahun

Ethiopian News

ቤተ መንግስቱ እንኳን ሊናፍቀኝ በዚያ ሳልፍ እንኳን ምንም ስሜት አይሰማኝም – የቀድሞ ቀዳማዊት እመቤት አዜብ መስፍን

ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሕወሓት ነባር ታጋይና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ባለቤት ናቸው። ቀዳማዊ እመቤት በነበሩበት ወቅት የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ማኅበር (ትእምት ወይም ኤፈርት) መሪ ነበሩ። ወ/ሮ አዜብ፤ የባለቤታቸው መታሰቢያ የሆነው የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን መስራችና የቦርድ ሰብሳቢም ናቸው።

ቀዳማዊ እመቤት በነበሩበት ወቅት፤ በአዕምሮ ህሙማን ዙሪያ የሠሩትን ሥራ በጣም እንደሚኮሩበት ይናገራሉ። በተለያየ ዘርፍ ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ያከናወኗቸው በርካታ ሥራዎች ስለመኖራቸውም ያስታውሳሉ። በኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን የተቋቋመው “የጉልት ማዕከል” የተባለውን ሃሳብ ከማመንጨት ጀምሮ እስከመጨረሻው መሳተፋቸውን እንደ አብነት ያነሳሉ። [“የጉልት ማዕከል” በጎዳና የንግድ ሥራ የተሠማሩ ሴቶች የሚደገፉበት ፕሮጀክት ነው።]

ታዲያ በዚህ ጊዜ ዋናውና መደበኛ ሥራቸው በፓርቲው የሚሰጣቸውን ሥራ መሥራት ነበር። “ራሴን የምወቅስበት ሥራ ሳልሠራ እና ጥሩ ሥራ ሰርቼ ከፓርቲው መውጣቴን እኮራበታለሁ፤ ሰው የፈለገውን ቢል” ይላሉ።
ድህነትን በመታገል ረገድ በርካታ ሥራዎችን እንዳከናወኑም ይናገራሉ። “ለሕዝብ ይጠቅማሉ ብዬ የተንቀሳቀስኩባቸው ሥራዎች ጥሩ ናቸው ብዬ አምንባቸዋለሁ” ሲሉ ያክላሉ።

ባለቤታቸው፤ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩ ባሳለፍነው ነሐሴ ወር ሰባት ዓመት ሞልቷቸዋል።

ለመሆኑ የቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን ባለፉት ዓመታት ምን ሲሠሩ ቆዩ? አሁንስ በምን ሥራ ላይ ነው ያሉት?

አዲስ ዓመትን አስመልክተን ከብዙሃን መገናኛ የጠፉትን ስንፈልግ፣ ስናስፈልግ ካገኘናቸውና ለቃለ መጠይቅ ፈቃደኛ ከሆኑት ከወ/ሮ አዜብ ጋር ጥቂት ተጨዋውተናል

የት ነው የሚኖሩት? ተቀማጭነትዎ የት ነው? ብዙ ሰዎች አዲስ አበባ የለችም ይላሉ። ግን አዲስ አበባ ነው ያለሁት- አንዳንዴ ገባ ወጣ ከማለቴ ውጭ።

ባለቤትዎን፣ የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር መለስን በሞት ካጡ በኋላ ቤተ መንግሥት የሄዱበት አጋጣሚ አለ?

ብዙ ጊዜ አልሄድም። የፓርቲው ሥራ አስፈፃሚ በነበርኩበት ጊዜ አንድ ሁለት ቀን የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፈት ቤት ሄጃለሁ። ያው ስብሰባው እዚያው ግቢ ውስጥ ስለነበር። ከዛ ውጭ ግን አልሄድኩም፤ መሄድም አልፈልግም።

በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ አስተዳደር ጊዜ ማለት ነው? አዎ! በቅርቡ አንድ ጊዜ የሄድኩ ይመስለኛል። በስብሰባዎች ምክንያት ስሄድ ነበር፤ ነገር ግን ብዙም አልሄድኩበትም።

ቤተ መንግሥቱ ከልጆችዎ፣ ከቤተሰብዎ ጋር ለረዥም ዓመታት የኖሩበት ነውና አይናፍቅዎትም? እ. . . [ዝምታ] በዚያ ሳልፍ እንኳን ምንም ስሜት አይሰማኝም። ምክንያቱም አወጣጤ ላይ. . . መለስን ቀብሬ ነው የወጣሁት። እና ደግሞ ቤተ መንግሥትን እንደ ታጋዮች ነው የኖርንበት። የሥራ ድርሻ ተሰጥቶን ነው የኖርንበት።

ከቤተ መንግሥት ስንወጣ መለስን ቀብሬ እወጣለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ሁለታችን አብረን የምንወጣበትና እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ነፃ ሆነን ተንቀሳቅሰን የምንኖርበትን ጊዜ እመኝ ነበር። እኔ ብንቀሳቀስም፤ መለስ ግን የመንቀሳቀስ እድል አላገኘም ነበር።

እዚያው እንደታሰረ፣ እዚያው ቀብሬው መውጣቴ ይሰማኛል [ሳግ በተናነቀው ድምፅ]. . . ከቤተ መንግሥት ይልቅ ሥላሴ [ቤተ ክርስቲያን] ስገባ በጣም ይሰማኛል። እና. . . ቤተ መንግሥትን ሳይ፤ መለስን ቀብሬ የተመለስኩበትን ሰዓት ብቻ ነው የማስታውሰው። አስክሬኑን ይዤ የወጣሁበትን ደቂቃዎች ብቻ ነው የማስታውሰው። ሌላው በሙሉ ለምን እንደሆነ አይገባኝም. . . ትዝ አይለኝም።

ሙሉውን መረጃ እዚህ ይመልከቱ

0Shares