ከየካቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት እንዲበተኑ የተደረጉት መምህራን ያለምንም መፍትሄ እየተንገላቱ ነው።

የካቲት 12 መሰናዶ ትምህርት ቤት ወደ ሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ተቀይሯል በሚል ከስራቸው እንዲበተኑ የተደረጉት መምህራን ያለምንም መፍትሄ እየተንገላቱ መሆናቸውን ገለጹ።

መምህራኑ ለኢትዮ 360 እንዳደረሱት መረጃ መሰናዶ ትምህርት ቤቱ ወደ አዳሪ ትምህርት ቤትነት መቀየሩን የሰሙት እረፍት ላይ እንዳሉ በመገናኛ ብዙሃን በተሰራጨ ዘገባ መሆኑን ይገልጻሉ።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ችግር ሊተክሉ በመጡበት እግር መንገዳቸውን መሰናዶ ትምህርት ቤቱ ወደ ሴቶች አዳሪ ትምህርት መቀየሩን ያበሰሩት።

ይሄንን ተከትሎም 108 የሚሆኑ የመሰናዶ ትምህርት ቤቱ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም ከ500 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች በወጡበት በዛው እንዲቀሩ ተደርገዋል ይላሉ መምህራኑ።
እንዲህ አይነቱ ውሳኔ በማንና መቼ እንደተወሰነ ባላወቅንበትና እኛንም ሆነ ወላጆችን ብሎም ማህበረሰቡን ማወያየት ባልተቻለበት ሁኔታ እንደዚህ አይነት ውሳኔ ላይ መደረሱ ያሳዝናል ብለዋል።
መሰናዶ ትምህርት ቤቱ በክፍለ ከተማ ውስጥ ያለ ቢሆንም ክፍለ ከተማው ግን ወደ ሴቶች አዳሪ ትምህርት ስለመቀየሩ ምንም አይነት መረጃ የሌለው መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ እንዲወሳሰብ አድርጎታል ባይ ናቸው።

በመሰናዶ ትምህርት ቤት ውስጥ የነበሩት አብዛኞቹ መምህራን ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውና ለአዳሪ ትምህርት ቤቱ የሚመጥኑ ቢሆኑም ማንም ግን ሊያስጠጋቸው አልቻለም ይላሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አዳሪ ትምህርት ቤቱን መተው ጎብኝተዋል፣ነገር ግን ማምህራኑም ሆኑ ተማሪዎቹ የት ደረሱ ብለው አለመጠየቃቸው አሳዝኖናል ሲሉም ይከሳሉ።–በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ተጠያቂ ናቸው በማለትም ጭምር።

መምህራኑ እንደሚሉት በዚህ አዳሪ ትምህርት የሚመደቡት ተማሪዎችም ሆኑ መምህራን ከየት እንደሚመጡ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም ይላሉ።እኛ ለምን አናስተምርም ላሉት ጥያቄ ብትፈልጉ ተወዳድራችሁ መግባት ትችላላችሁ የሚል ገፊ ምላሽ እንደተሰጣቸው በመግለጽ።

አዳሪ ትምህርት ቤቱ በህዝብ ገንዘብ የሚተዳደር ሆኖ ሳለ በዚህ አገልግሎት ውስጥ ግን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለው ጥቂቶች ናቸው።–ለዛውም ከየት እንደሚመጡ ገና ያልታወቁ ሲሉ ይጠቅሳሉ።

መምህራኑ ጉዳያቸውን ለእንባ ጠባቂ፣ለሰብአዊ መብት ኮሚሽንና ለሚመለከታቸው አካላት ቢያቀርቡም እስካሁም ምላሽ የሰጣቸው አካል እንደሌለ ይናገራሉ።

ወደ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ለአቤቱታ ቢሄዱም በቢሮው ምክትል ሃላፊ ከስድብ ጋ ተባረው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

እንደ መምህራኑ አባባል ከሆነ ጉዳዩን እየዘወሩት ያሉት ምክትል ከንቲባው ናቸው።ስለዚህ እሳቸው ለሁሉም አካል የሚሰጡት መመሪያ በሁሉም ቦታ ጉዳያችን ጆሮ እንዳያገኝ አድርጎታል ይላሉ።
አሁን ላይ እንደ ሃገር እየተፈጸሙት ያሉት ሁኔታዎች መንግስት የለም የሚያስብሉና እንደ ምሁራን ምን እየተፈጸመ እንዳለ የምንጠይቅበት ጊዜ ላይ ደርሰናል ሲሉ ለኢትዮ 360 ተናግረዋል።
መምህራኑ አሁን ላይ ለእንባ ጠባቂ ተቋም ክሳቸውን አቅርበው ምላሹን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።ነገር ግን እንደ ምሁራን በሃገር ውስጥ እየተከናወነ ስላለው ነገር እስከመጨረሻው መጠየቃችንን አናቆምም ሲሉ ለኢትዮ 360 ተናግረዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የገላን ቁጥር አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም የወንዶች አዳሪ ትምህርት ቤት ይሆናል በሚል ተማሪዎቹና መምህራኑ እንዲበቱ መደረጉንም ለኢትዮ 360 የደረሰው መረጃ አመልክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *